ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 33 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የይሁዳ ንጉሥ ምናሴ

1. ምናሴ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም አምሳ አምስት ዓመት ገዛ።

2. እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ፊት አሳዶ ያስወጣቸውን ሕዝቦች አስጸያፊ ልማድ በመከተልም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ።

3. አባቱ ሕዝቅያስ ያጠፋቸውን የኰረብታ መስገጃ ስፍራዎች መልሶ ሠራ፤ ለበአሊም መሠዊያዎችን አቆመ፤ የአሼራንም ዐምዶች ሠራ፤ ለሰማይ ከዋክብት ሰራዊትም ሰገደ፤ አመለካቸውም።

4. እግዚአብሔር፣ “ስሜ ለዘላለም በኢየሩሳሌም ይኖራል” ባለበት በእግዚአብሔር ቤተ መቀደስ መሠዊያዎችን ሠራ።

5. በሁለቱም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባዮች ላይ፣ ለሁሉም የሰማይ ከዋክብት ሰራዊት መሠዊያዎችን ሠራ።

6. በሄኖም ልጅ ሸለቆ ወንዶች ልጆቹን በእሳት ሠዋ፤ አስማት፣ መተትና ጥንቈላ አደረገ፤ ሙታን ጠሪዎችንና መናፍስት ሳቢዎችን ጠየቀ። ለቊጣ ያነሣሣው ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ክፉ ነገር አደረገ።

7. ያበጀውን የተጠረበ ምስል ወስዶም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አኖረ፤ ስለዚህም ቤተ መቅደስ እግዚአብሔር ለዳዊትና ለልጁ ለሰሎሞን እንዲህ ብሎ ነበር፤ “በዚህ ቤተ መቅደስና ከእስራኤል ነገድ ሁሉ በመረጥኋት በኢየሩሳሌም ስሜን ለዘላለም አኖራለሁ፤

8. በሙሴ አማካይነት ያዘዝኋቸውን ሕግጋቴን፣ ደንቦቼንና ሥርዐቶቼን ሁሉ በጥንቃቄ ይፈጽሙ እንጂ፣ ለቀድሞ አባቶቻችሁ ከሰጠኋቸው ምድር የእስራኤላውያን እግር ከእንግዲህ ለቆ እንዲወጣ አላደርግም።”

9. ምናሴ ግን እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ፊት ካጠፋቸው አሕዛብ የባሰ ክፉ ድርጊት ይፈጽሙ ዘንድ፣ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሕዝብ አሳተ።

10. እግዚአብሔር ለምናሴና ለሕዝቡ ተናገረ፤ እነርሱ ግን መስማት አልፈለጉም።

11. ስለዚህ እግዚአብሔር የአሦርን ንጉሥ ሰራዊት አዛዦች አመጣባቸው፤ እነርሱም በምናሴ አፍንጫ መንጠቆ አገቡበት፤ በናስ ሰንሰለት አስረውም ወደ ባቢሎን ወሰዱት።

12. በተጨነቀም ጊዜ የአምላኩን የእግዚአብሔርን በጎነት ፈለገ፤ በአባቶቹም አምላክ ፊት ራሱን እጅግ አዋረደ።

13. ወደ እርሱም በጸለየ ጊዜ፣ በጭንቀት ልመናው ራርቶለት እግዚአብሔር ጸሎቱን ሰማው። ስለዚህ ወደ ኢየሩሳሌም፣ ወደ መንግሥቱም መለሰው፤ ምናሴም እግዚአብሔር አምላክ መሆኑን ዐወቀ።

14. ከዚህ በኋላ በሸለቆው ውስጥ ከሚገኘው ከግዮን ምንጭ ምዕራብ አንሥቶ እስከ ዓሣ በር መግቢያ ድረስ ያለውን የዳዊትን ከተማ የውጭውን ቅጥር፣ የዖፊልን ኰረብታ እንዲከብ በማድረግ፣ ይበልጥ ከፍ አድርጎ እንደ ገና ሠራው። በተመሸጉትም የይሁዳ ከተሞች ሁሉ የጦር አዛዦችን አኖረ።

15. እንግዶች አማልክትንና ጣዖታቱን ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አስወገደ፤ በቤተ መቅደሱ ኰረብታና በኢየሩሳሌም የሠራቸውንም መሠዊያዎች ሁሉ አራቀ፤ ከከተማዪቱም ውጭ ጣላቸው።

16. ከዚያም የእግዚአብሔርን መሠዊያ ዐደሰ፤ በላዩም የኅብረት መሥዋዕትና የምስጋና መሥዋዕት አቀረበ፤ ይሁዳም የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን እንዲያገለግሉ አዘዘ።

17. ሕዝቡ ግን በኰረብታ መስገጃ ስፍራዎች መሠዋቱን ቢቀጥልም፣ የሚሠዋው ግን ለአንዱ አምላክ ለእግዚአብሔር ብቻ ነበር።

18. በምናሴ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ተግባር፣ ወደ አምላኩ ያቀረበው ጸሎቱና ባለ ራእዮች በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስም የነገሩት ቃል በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎአል።

19. ጸሎቱና እግዚአብሔር ራርቶ ልመናውን እንዴት እንደ ተቀበለው፣ ኀጢአቱ ሁሉና ታማኝነቱን ማጒደሉ፣ እንደዚሁም ራሱን ከማዋረዱ በፊት ያሠራቸው የኰረብታ መስገጃ ስፍራዎች፣ ያቆማቸው የአሼራ ምስል ዐምዶችና ጣዖታት ሁሉ በባለ ራእዮች መዛግብት ተጽፈዋል።

20. ምናሴም እንደ አባቶቹ ሁሉ አንቀላፋ፤ በቤተ መንግሥቱም ተቀበረ። ልጁም አሞን በእርሱ ፈንታ ነገሠ።

የይሁዳ ንጉሥ አሞን

21. አሞን በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሃያ ሁለት ዓመት ነበር፤ እርሱም በኢየሩሳሌም ተቀምጦ ሁለት ዓመት ገዛ።

22. አባቱ ምናሴ እንዳደረገው ሁሉ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ፤ አሞንም ምናሴ ያሠራቸውን ጣዖታት ሁሉ አመለከ፤ መሥዋዕትም አቀረበላቸው።

23. አሞን በእግዚአብሔር ፊት ራሱን እንዳዋረደ እንደ አባቱ እንደ ምናሴ ራሱን አላዋረደም፤ ነገር ግን በበደል ላይ በደል እየጨመረ ሄደ።

24. የአሞን ሹማምት በእርሱ ላይ አሢረው በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ገደሉት።

25. ከዚያም ያገሩ ሕዝብ በንጉሡ አሞን ላይ ያሤሩትን ሁሉ ገደሉ፤ ልጁን ኢዮስያስንም በእርሱ ፈንታ አነገሡት።