ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ሺሻቅ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ

1. ሮብዓም መንግሥቱን ከመሠረተና ካጸና በኋላ እርሱና እስራኤል ሁሉ የእግዚአብሔርን ሕግ ተዉ።

2. እግዚአብሔርን ከመበደላቸው የተነሣም፣ ሮብዓም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብፅ ንጉሥ ሺሻቅ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ።

3. ከግብፅ አብረውት የመጡትን ዐሥራ ሁለት ሺህ ሠረገላዎች፣ ስድሳ ሺ ፈረሰኞችና ስፍር ቊጥር የሌላቸውን የሊብያ፣ የሱኪምና የኢትዮጵያ ወታደሮችን ይዞ፣

4. የተመሸጉትን የይሁዳ ከተሞች በቁጥጥሩ ሥር በማድረግ እስከ ኢየሩሳሌም ዘለቀ።

5. ከዚህ በኋላ ነቢዩ ሸማያ ወደ ሮብዓምና ሺሻቅን ፈርተው በኢየሩሳሌም ወደ ተሰበሰቡት ወደ እስራኤል መሪዎች መጥቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እናንተ ትታችሁኛል፤ ስለዚህ እኔም በሺሻቅ እጅ ትቼአችኋለሁ’ ” አላቸው።

6. የእስራኤል መሪዎችና ንጉሡ ራሳቸውን በማዋረድ፣ “እግዚአብሔር ጻድቅ ነው” አሉ።

7. እግዚአብሔርም ራሳቸውን እንዳዋረዱ ባየ ጊዜ፣ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ ሸማያ መጣ፤ “ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ስላዋረዱ እታደጋቸዋለሁ እንጂ አላጠፋቸውም፤ ቊጣዬም በሺሻቅ እጅ በኢየሩሳሌም ላይ አይፈስስም።

8. ይሁን እንጂ እኔን በማገልገልና የሌሎችን አገሮች ነገሥታት በማገልገል መካከል ያለውን ልዩነት ያውቁ ዘንድ፣ ለእርሱ ይገዛሉ።”

9. የግብፅ ንጉሥ ሺሻቅ ኢየሩሳሌምን በወረረ ጊዜ፣ የቤተ መቅደሱን ንብረትና የቤተ መንግሥቱን ንብረት ዘርፎ ወሰደ፤ ሰሎሞን ያሠራው የወርቅ ጋሻ ሳይቀር፣ እንዳለ ሁሉንም አጋዘው።

10. ንጉሥ ሮብዓምም በተወሰዱት ፈንታ የናስ ጋሻዎች ሠርቶ፤ የቤተ መንግሥቱን ቅጥር በሮች ለሚጠብቁ የዘብ አለቆች በኀላፊነት ሰጠ።

11. ንጉሡ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በሚሄድበት ጊዜ ሁሉ፣ ዘበኞቹ ጋሻዎቹን አንግበው ያጅቡት ነበር፤ ከዚያም በኋላ ጋሻዎቹን ወደ ዘበኞች ክፍል ይመልሱ ነበር።

12. ሮብዓም ራሱን ዝቅ አድርጎ ስላዋረደ የእግዚአብሔር ቊጣ ከእርሱ ተመለሰ፤ ፈጽሞም አላጠፋውም፤ በይሁዳም ደግሞ በጥቂቱም ቢሆን መልካም ነገር ተገኝቶ ነበር።

13. ንጉሥ ሮብዓም በሚገባ ተደላድሎ በኢየሩሳሌም በንጉሥነቱ ቀጠለ፣ ሲነግሥ ዕድሜው አርባ አንድ ዓመት ነበር፤ እግዚአብሔር ስሙን በዚያ ለማኖር ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ በመረጣት በኢየሩሳሌም ከተማ ተቀምጦም፣ ዐሥራ ሰባት ዓመት ገዛ፤ እናቱም ናዕማ የምትባል አሞናዊት ነበረች።

14. እግዚአብሔርን ይሻ ዘንድ ልቡን ስላላዘጋጀ ክፉ ነገር አደረገ።

15. ሮብዓም በዘመነ መንግሥቱ ያከናወናቸው ተግባሮች ሁሉ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ ነቢዩ ሸማያ በጻፈው የታሪክ መዝገብና በባለ ራእዩ አዶ በዘገበው የትውልድ ሐረግ ታሪክ የሚገኝ አይደለምን? በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከል የማያቋርጥ ጦርነት ነበር።

16. ሮብዓም እንደ አባቶቹ ሁሉ አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ፤ ልጁ አብያም በእርሱ ፈንታ ነገሠ።