ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 36 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የአገሩም ሰዎች የኢዮስያስን ልጅ ኢዮአሐዝን ወስደው በአባቱ ፈንታ በኢየሩሳሌም አነገሡት።

የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአሐዝ

2. ኢዮአሐዝ በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ሃያ ሦስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሦስት ወር ገዛ።

3. ከዚያም የግብፅ ንጉሥ በኢየሩሳሌም ካለው ዙፋኑ አወረደው፣ በአገሩም ላይ አንድ መቶ መክሊት ብርና አንድ መክሊት ወርቅ ግብር ጣለበት።

4. የግብፅም ንጉሥ የኢዮአሐዝን ወንድም ኤልያቄምን በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነገሠው፤ ስሙንም ለውጦ ኢዮአቄም አለው። ኒካዑም የኤልያቄምን ወንድም ኢዮአሐዝን ይዞ ወደ ግብፅ ወሰደው።

የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም

5. ኢዮአቄም በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ሃያ አምስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ አንድ ዓመት ገዛ። በአምላኩም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ።

6. የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በእርሱ ላይ ዘመተ፤ ወደ ባቢሎንም ይወስደው ዘንድ በናስ ሰንሰለት አሰረው።

7. እንደዚሁም ናቡከደነፆር የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ዕቃ ወስዶ፣ ባቢሎን ባለው በራሱ ቤተ ጣዖት አኖረው።

8. በኢዮአቄም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ተግባሩ የፈጸመው አስጸያፊ ድርጊትና በእርሱ ላይ የተገኘበት ሁሉ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል። ልጁ ዮአኪንም በእርሱ ፈንታ ነገሠ።

የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን

9. ዮአኪን በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ዐሥራ ስምንት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሦስት ወር ከዐሥር ቀን ገዛ፤ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ።

10. በጸደይም ወራት ንጉሡ ናቡከደነፆር ልኮ በእግዚአብሔ ቤተ መቅደስ ውስጥ ከፍተኛ ዋጋ ካላቸው ዕቃዎች ጋር ወደ ባቢሎን ወሰደው። የዮአኪንንም አጎት ሴዴቅያስን በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነገሠው።

የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ

11. ሴዴቅያስ በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ሃያ አንድ ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ አንድ ዓመት ገዛ።

12. እርሱም በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ፤ የእግዚአብሔርን ቃል በተናገረው በነቢዩ በኤርምያስ ፊትም ራሱን ዝቅ አላደረገም።

13. እንደዚሁም በእግዚአብሔር ስም አምሎት በነበረው በንጉሥ ናቡከደነፆር ላይ ዐመፀ፤ አንገቱን አደነደነ፤ ልቡንም አጠነከረ እንጂ ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር አልተመለሰም።

14. ከዚህም ላይ የካህናቱና የሕዝቡ መሪዎች ሁሉ፣ አስጸያፊ የሆኑትን የአሕዛብን ልማዶች በመከተልና በኢየሩሳሌም የተቀደሰውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በማርከስ፣ ባለ መታመናቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሱ ሄዱ።

የኢየሩሳሌም መውደቅ

15. የአባቶቻቸው አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡና ለማደሪያው ስላዘነ፣ መልእክተኞቹን ይልክ ነበር፤

16. እነርሱ ግን የእግዚአብሔር ቊጣ በሕዝቡ ላይ እስኪነሣሣና ፈውስም እስከማይገኝላቸው ድረስ በእግዚአብሔር መልእክተኞች ላይ ተሳለቁ፤ ቃሉን ናቁ፤ ነቢያቱንም አቃለሉ።

17. ስለዚህ የባቢሎናውያንን ንጉሥ አመጣባቸው፤ እርሱም ወጣቶቻቸውን በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሰይፍ ፈጀ፤ ወጣቱንም ሆነ ወጣቲቱን፣ ሽማግሌውንም ሆነ በዕድሜ የገፋውን አላስቀረም፤ እግዚአብሔር ሁሉንም ለናቡከደናፆር አሳልፎ ሰጠው።

18. እርሱም ትልልቁንም ሆነ ትንንሹን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ዕቃ በሙሉ፣ እንዲሁም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሀብት፣ የንጉሡንና የሹማምቱን ሀብት ሁሉ ወደ ባቢሎን አጋዘ።

19. የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በእሳት አቃጠሉ፤ የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች አፈረሱ፤ ቤተ መንግሥቶቹን በሙሉ አቃጠሉ፤ በዚያ የነበረውንም የከበረ ዕቃ በሙሉ አጠፉ።

20. ከሰይፍ የተረፉትን ቅሬታዎች በምርኮ ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው፤ እስከ ፋርስ መንግሥት መነሣትም ድረስ የእርሱና የልጆቹ አገልጋዮች ሆኑ።

21. ምድሪቱም የሰንበት ዕረፍት አገኘች፤ በኤርምያስ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ፣ ሰባው ዓመት እስኪያበቃ ድረስ፣ ባድማ በነበረችበት ዘመን ሁሉ ዐረፈች።

22. በኤርምያስ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ፣ በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ ዘመነ መንግሥት መጀመሪያ ዓመት፣ በግዛቱ ሁሉ ዐዋጅ እንዲያስነግርና ይህም እንዲጻፍ እግዚአብሔር የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አነሣሣ፤ እርሱም እንዲህ አለ፤

23. “የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል፤“ ‘የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳ በምትገኘው በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ እሠራለት ዘንድ አዝዞኛል፤ ከሕዝቡ በመካከላችሁ የሚገኝ ማናቸውም ሰው፣ እግዚአብሔር አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፤ እርሱም ወደዚያው ይውጣ።’ ”