ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የሳባ ንግሥት ሰሎሞንን ጐበኘች

1. የሳባ ንግሥት የሰሎሞንን ዝና በሰማች ጊዜ አስቸጋሪ በሆኑ ጥያቄዎች ልትፈትነው ወደ ኢየሩሳሌም መጣች። ቅመማ ቅመም፣ እጅግ ብዙ ወርቅና የከበሩ ድንጋዮችን በግመሎች አስጭና ከታላቅ ጓዝ ጋር ደረሰች፤ ወደ ሰሎሞንም ቀርባ በልቧ ያለውን ሁሉ አጫወተችው።

2. ሰሎሞንም የጠየቀችውን ሁሉ መለሰላት፤ ሊመልስላት የተሳነው አንዳች ነገር አልነበረም።

3. የሳባ ንግሥት የሰሎሞንን ጥበብና የሠራውን ቤተ መንግሥት፣

4. በገበታው ላይ የሚቀርበውን መብል፣ የሹማምቱን አቀማመጥ፣ አስተናባሪዎቹንና አለባበሳቸውን፣ ጠጅ አሳላፊዎቹንና አለባበሳቸውን እንዲሁም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ያቀረባቸውን የሚቃጠሉ መሥዋዕቶች ባየች ጊዜ እጅግ ተደነቀች።

5. ንጉሡንም እንዲህ አለችው፤ “ስለ ሥራህና ስለ ጥበብህ በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት ሁሉ እውነት ነው።

6. ነገር ግን መጥቼ በዓይኔ እስካየሁ ጊዜ ድረስ የነገሩኝን አላመንሁም ነበር፤ በርግጥም የጥበብህ እኩሌታ እንኳ አልተነገረኝም፤ እኔ ከሰማሁት ዝና እጅግ ትልቃለህ።

7. ሰዎችህ ምንኛ ታድለዋል! ዘወትር በፊትህ ቆመው ጥበብህን የሚሰሙ ሹማምትህስ ምንኛ ታድለዋል!

8. ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ንጉሥ ሆነህ እንድትገዛ፣ በአንተ ደስ የተሰኘውና በዙፋኑ ላይ ያስቀመጠህ አምላክህ እግዚአብሔር ቡሩክ ይሁን፤ አምላክህ ለእስራኤል ካለው ፍቅርና ለዘላለም ሊያጸናቸው ካለው ፍላጎት የተነሣ፣ ፍትሕና ጽድቅ እንዲሰፍን ታደርግ ዘንድ አንተን በላያቸው ላይ አንግሦሃልና።”

9. ከዚያም ለንጉሡ አንድ መቶ ሃያ መክሊት ወርቅ፣ እጅግ ብዙ ቅመማ ቅመምና የከበሩ ድንጋዮች ሰጠችው፤ የሳባ ንግሥት ለንጉሥ ሰሎሞን እንደሰጠችው ዐይነት ቅመማ ቅመም ያለ ከቶ አልነበረም።

10. የኪራም ሰዎችና የሰሎሞን ሰዎች ወርቅ ከኦፊር እንደዚሁም ሰንደልና የከበሩ ድንጋዮች አመጡ።

11. ንጉሡም የሰንደሉን እንጨት ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና ለቤተ መንግሥቱ ደረጃ መሥሪያ እንደዚሁም ለመዘምራኑ የመሰንቆና የበገና መሥሪያ አደረገው፤ ይህን የመሰለ ነገር በይሁዳ ምድር ከቶ አልታየም።

12. ንጉሥ ሰሎሞን ለሳባ ንግሥት የፈለገችውንና የጠየቀችውን ሁሉ ሰጣት፤ ስጦታውም እርስዋ ካመጣችለት በላይ ነበር። ከዚያም ከአጃቢዎቿ ጋር ወደ አገሯ ተመለሰች።

የሰሎሞን ብልጽግና

13. ሰሎሞን በየዓመቱ የሚቀበለው ወርቅ ክብደቱ ስድስት መቶ ሥልሳ ስድስት መክሊት ነበር።

14. ይህም ከታላላቅና ከተራ ነጋዴዎች ከሚገባው ቀረጥ ሌላ ነበር፤ እንዲሁም መላው የዐረብ ነገሥታትና የገዛ ምድሩ አገረ ገዦች ለሰሎሞን ወርቅና ብር ያመጡለት ነበር።

15. ንጉሥ ሰሎሞን ሁለት መቶ ከጥፍጥፍ ወርቅ የተሠራ ታላላቅ ጋሻዎች አበጀ፤ በእያንዳንዱም ጋሻ የገባው ጥፍጥፍ ወርቅ ስድስት መቶ ሰቅል ነበር።

16. እንዲሁም ሦስት መቶ ትንንሽ ጋሻዎች በጥፍጥፍ ወርቅ ሠራ፤ በእነዚህም በእያንዳንዳቸው የገባው ጥፍጥፍ ወርቅ ሦስት መቶ ሰቅል ነበር። ንጉሡም ጋሻዎቹን “የሊባኖስ ደን” በተባለው ቤተ መንግሥት ውስጥ አኖራቸው።

17. ከዚያም ንጉሡ በዝሆን ጥርስ ያጌጠና በንጹሕ ወርቅ የተለበጠ ትልቅ ዙፋን ሠራ።

18. ዙፋኑ ስድስት መውጫ መውረጃ ደረጃዎች ሲኖሩት፣ ከዙፋኑ ጋር የተያያዘ ከወርቅ የተሠራ የእግር መርገጫ ነበረው። መቀመጫውም ግራና ቀኙ መደገፊያ ያለው ሆኖም ከመደገፊያዎቹም አጠገብ አንዳንድ አንበሳ ቆሞ ነበር።

19. እንዲሁም በስድስቱ ደረጃዎች ዳርና ዳር ላይ አንዳንድ አንበሳ፣ ባጠቃላይ አሥራ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር፤ ይህን የመሰለ ዙፋን በየትኛውም አገር ተሠርቶ አያውቅም።

20. ንጉሥ ሰሎሞን የሚጠጣባቸው ዕቃዎች በሙሉ ከወርቅ የተሠሩ ነበሩ፤ “የሊባኖስ ደንቃ ተብሎ በሚጠራው ቤተ መንግሥት ውስጥ የነበሩትም ዕቃዎች ሁሉ ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ ነበሩ፤ በሰሎሞን ዘመን ብር ዋጋ እንደሌለው ስለሚቈጠር ከብር የተሠራ አንድም ነገር አልነበረም።

21. ንጉሡ በኪራም ሰዎች የሚነዱ የንግድ መርከቦች ነበሩት፤ እነዚህም በየሦስት ዓመቱ አንድ ጊዜ ወርቅ፣ ብር፣ የዝሆን ጥርስ፣ ጦጣዎችና ዝንጀሮዎች እየያዙ ይመለሱ ነበር።

22. ንጉሥ ሰሎሞን በሀብትም ሆነ በጥበብ ከምድር ነገሥታት ሁሉ የበለጠ ነበር።

23. የምድር ነገሥታት ሁሉ እግዚአብሔር በልቡ ያኖረውን ጥበብ ለመስማት ከሰሎሞን ጋር መገናኘት ይፈልጉ ነበር።

24. በየዓመቱ ወደ እርሱ የሚመጡትም ሁሉ የብርና የወርቅ ዕቃ፣ የልብስ፣ የጦር መሣሪያና የቅመማ ቅመም እንደዚሁም የፈረስና የበቅሎ ገጸ በረከት ያመጡለት ነበር።

25. ሰሎሞን አራት ሺ የፈረሶችና የሠረገሎች ጋጥ ነበረው፤ እንዲሁም በሚኖርበት በኢየሩሳሌምና በሰረገላ ከተሞች አሥራ ሁለት ሺህ ፈረሶች ነበሩት።

26. እርሱም ከኤፍራጥስ ወንዝ እስከ ፍልስጥኤም ምድርና እስከ ግብፅ ዳርቻ ድረስ ባሉት ነገሥታት ሁሉ ላይ ገዛ።

27. ንጉሡ በኢየሩሳሌም ብሩን እንደ ማንኛውም ድንጋይ፣ የዝግባውንም ዕንጨት ብዛት በየኰረብታው ግርጌ እንደሚበቅል ሾላ አደረገው።

28. ለሰሎሞን ከግብፅና ከሌሎች አገሮች ሁሉ ፈረሶች ያመጡለት ነበር።

የሰሎሞን መሞት

29. ሰሎሞን በዘመነ መንግሥቱ የሠራው ሌላው ነገር በነቢዩ በናታን ታሪክና በሴሎናዊው በአሒያ ትንቢት እንዲሁም ባለ ራእዩ አዶ ስለ ናባጥ ልጅ ስለ ኢዮርብዓም ባየው ራእይ ውስጥ የተጻፈ አይደለምን?

30. ሰሎሞን በኢየሩሳሌም ተቀምጦ በእስራኤል ሁሉ ላይ አርባ ዓመት ነገሠ።

31. ከዚያም እንደ አባቶቹ አንቀላፋ፤ በአባቱም በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁም ሮብዓም በእርሱ ፋንታ ነገሠ።