ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ሕዝቅያስ ቤተ መቅደሱን አነጻ

1. ሕዝቅያስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሃያ አምስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ገዛ። እናቱም አቡ የተባለች፤ የዘካርያስ ልጅ ነበረች።

2. አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ።

3. በዘመነ መንግሥቱ በመጀመሪያው ዓመት፣ በመጀመሪያው ወር የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በሮች ከፈተ፤ አደሳቸው።

4. ካህናቱንና ሌዋውያኑን አስገብቶ በምሥራቅ በኩል ባለው አደባባይ ላይ በመሰብሰብ፣

5. እንዲህ አላቸው፤ “እናንት ሌዋውያን፤ ስሙኝ! ራሳችሁን አሁኑኑ ቀድሱ፤ የአባቶቻችሁን አምላክ የእግዚአብሔርንም ቤተ መቅደስ ቀድሱ። ርኩስ ነገርንም ሁሉ ከመቅደሱ አስወግዱ።

6. አባቶቻችን ታማኞች አልነበሩም፣ በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸሙ፤ ተውትም። ከእግዚአብሔር ማደሪያ ፊታቸውን መለሱ፤ ጀርባቸውንም አዞሩበት።

7. የሰበሰቡንም በሮች ዘጉ፤ መብራቶቹንም አጠፉ። ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ዕጣን አላጠኑም፤ በመቅደሱም የሚቃጠል መሥዋዕት አላቀረቡም።

8. ስለዚህ የእግዚአብሔር ቊጣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ወርዶአል፤ እናንተ በገዛ ዓይናችሁ እንደምታዩት ለድንጋጤ፣ ለመደነቂያና ለመዘበቻ አሳልፎ ሰጣቸው።

9. በዚህ ምክንያት አባቶቻችን በሰይፍ ወደቁ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን፣ ሚስቶቻችንም ተማረኩ።

10. አሁንም አስፈሪ ቊጣው ከእኛ እንዲመለስ፣ ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ለመግባት አስቤአለሁ።

11. ልጆቼ ሆይ፤ እንግዲህ ቸል አትበሉ፤ በፊቱ እንድትቆሙና እንድታገለግሉት፣ በፊቱም አገልጋዮቹ እንድትሆኑና ዕጣን እንድ ታጥኑለት እግዚአብሔር መርጦአችኋልና።”

12. ከዚያም እነዚሁ ሌዋውያን በሥራው ላይ ተሰማሩ፤ ከቀዓት ዘሮች የአማሢ ልጅ መሐትና የዓዛርያስ ልጅ ኢዮኤል፤ከሜራሪ ዘሮች፣የአብዲ ልጅ ቂስና የይሃሌልኤል ልጅ ዓዛርያስ፤ከጌድሶን ዘሮች፣የዛማት ልጅ ዮአክና የዮአክ ልጅ ዔድን፤

13. ከኤሊጻፋን ዘሮች፣ሺምሪና ይዒኤል፤ከአሳፍ ዘሮች፣ዘካርያስና መታንያ፤

14. ከኤማን ዘሮች፣ይሒኤልና ሰሜኢ፣ከኤዶታም ዘሮች፣ሸማያና ዑዝኤል።

15. ወንድሞቻቸውን ከሰበሰቡና ራሳቸውን ከቀደሱ በኋላ፣ ንጉሡ የእግዚአብሔርን ቃል ተከትሎ ባዘዘው መሠረት የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለማንጻት ገቡ።

16. ካህናቱ የእግዚአብሔርን መቅደስ ለማንጻት ወደ ውስጡ ገቡ። በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ያገኙትንም ማናቸውንም የረከሰ ነገር ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባይ አወጡት። ሌዋውያኑም ተሸክመው በመውሰድ በቄድሮን ሸለቆ ውስጥ ጣሉት።

17. ማንጻቱንም በመጀመሪያው ወር፣ በመጀመሪያው ቀን ጀምረው በዚያኑ ወር በስምንተኛው ቀን እስከ መቅደስ ሰበሰብ ደረሱ፤ በሚቀጥሉትም ስምንት ቀናት የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቀደሱ፤ የመቀደሱም ሥራ በመጀመሪያው ወር በዐሥራ ስድስተኛው ቀን ተጠናቀቀ።

18. ከዚያም ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ ገብተው እንዲህ አሉ፤ “የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በሙሉ፣ የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን መሠዊያ ከነዕቃዎቹ ሁሉ፣ ኀብስተ ገጹ የሚቀመጥበትን ጠረጴዛ፣ ከነዕቃዎቹ አንጽተናል።

19. ንጉሥ አካዝ ነግሦ ሳለ ታማኝነቱን ትቶ፣ ከቦታቸው ያነሣቸውን ዕቃዎች ሁሉ አዘጋጅተን ቀድሰናቸዋል፤ እነሆ፤ ዕቃዎቹ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሠዊያ ፊት ለፊት ናቸው።”

20. በማግስቱም ጧት በማለዳ፣ ንጉሥ ሕዝቅያስ የከተማዪቱን ሹማምት በአንድነት ሰብስቦ፣ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወጣ፤

21. እነርሱም ስለ መንግሥቱ፣ ስለ መቅደሱና ስለ ይሁዳ ሰባት ወይፈኖች፣ ሰባት አውራ በጎች፣ ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶችና ሰባት ተባዕት የፍየል ጠቦቶች ለኀጢአት መሥዋዕት አቀረቧቸው፤ ንጉሡም እነዚህን በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ እንዲያቀርቡ የአሮንን ዘሮች ካህናቱን አዘዘ።

22. ካህናቱም ወይፈኖቹን ዐርደው ደሙን በመውሰድ በመሠዊያው ላይ ረጩት፤ አውራ በጎቹንም ዐርደው ደሙን በመሠዊያው ላይ ረጩት፤ እንደዚሁም ጠቦቶቹን ዐርደው ደሙን በመሠዊያው ላይ ረጩት።

23. ለኀጢአት መሥዋዕት የሚሆኑትን ፍየሎች በንጉሡና በጉባኤው ፊት አቀረቡ፤ እነርሱም እጆቻቸውን ጫኑባቸው።

24. ንጉሡ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኀጢአት መሥዋዕት ስለ እስራኤል ሁሉ እንዲቀርብ አዞ ስለ ነበር፣ ካህናቱ ፍየሎቹን ዐርደው ስለ እስራኤል ሁሉ ማስተስረያ እንዲሆን የኀጢአት መሥዋዕት በማድረግ ደሙን በመሠዊያው ላይ አቀረቡ።

25. ንጉሥ ሕዝቅያስም በዳዊት፣ በንጉሡ ባለ ራእይ በጋድና በነቢዩ በናታን በተሰጠው መመሪያ መሠረት ሌዋውያኑን ጸናጽል፣ በገናና መሰንቆ አስይዞ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መደባቸው፤ ይህም በነቢያት አማካይነት ከእግዚአብሔር የተሰጠ ትእዛዝ ነበር።

26. ስለዚህ ሌዋውያኑ የዳዊትን የዜማ ዕቃዎች፣ ካህናቱም መለከቶቻቸውን ይዘው ዝግጁ በመሆን ቆሙ።

27. ከዚህ በኋላ ሕዝቅያስ የሚቃጠለው መሥዋዕት በመሠዊያው ላይ እንዲቀርብ አዘዘ። መሥዋዕቱ ማረግ በጀመረ ጊዜም፣ በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት የዜማ ዕቃዎችና በመለከት የታጀበ ዝማሬም ጀመረ።

28. መዘምራኑ በሚዘም ሩበትና መለከተኞቹም በሚነፉበት ጊዜም መላው ጉባኤ አጎንብሰው ሰገዱ፤ የሚቃጠለው መሥዋዕት እስኪጠናቀቅ ድረስም ይህ ሁሉ ቀጠለ።

29. መሥዋዕቱ ሁሉ ቀርቦ ካበቃ በኋላ፣ ንጉሡና አብረውት የነበሩት ሁሉ ተንበርክከው ሰገዱ።

30. ንጉሥ ሕዝቅያስና ሹማምቱ፣ ሌዋውያኑ በዳዊትና በባለ ራእዩ በአሳፍ ቃል እግዚአብሔርን እንዲያመሰግኑ አዘዙ። እነርሱም ውዳሴውን በደስታ ዘመሩ፤ ራሳቸውንም አጎንብሰው ሰገዱ።

31. ከዚያም ሕዝቅያስ፣ “እነሆ፤ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር ቀድሳችኋል፤ አሁንም ቅረቡ፤ መሥዋዕትና የምስጋና ስጦታ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አምጡ” አላቸው። ስለዚህ ጉባኤው መሥዋዕትና የምስጋና ስጦታ አመጡ፤ ልባቸው የፈቀደ ሁሉም የሚቃጠል መሥዋዕት አመጡ።

32. ጉባኤውም ያመጣው የሚቃጠለው መሥዋዕት ብዛት ሰባ ወይፈኖች፣ መቶ አውራ በጎችና ሁለት መቶ ተባዕት የበግ ጠቦቶች ናቸው፤ ሁሉም የሚቃጠል መሥዋዕት ሆነው ለእግዚአብሔር የሚቀርቡ ነበሩ።

33. ለመሥዋዕት የተቀደሱት እንስሳት ባጠቃላይ ስድስት መቶ ወይፈን፣ ሦስት ሺህ በጎችና ፍየሎች ነበሩ።

34. ይሁን እንጂ ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ቈዳ ሁሉ ለመግፈፍ ቊጥራቸው እጅግ ጥቂት ነበር፤ ስለዚህ ወገኖቻቸው የሆኑት ሌዋውያን ሥራው እስኪያልቅና ሌሎች ካህናት እስኪቀደሱ ድረስ ረዷቸው፤ ሌዋውያኑም ራሳቸውን ለመቀደስ ከካህናቱ ይልቅ ጠንቃቆች ነበሩና።

35. ከሚቃጠለው መሥዋዕት ጋር የሚቀርበውን የኅብረት መሥዋዕት ስብና የመጠጡን ቍርባን ጨምሮ የሚቃጠለው መሥዋዕት እጅግ ብዙ ነበር። በዚህ ሁኔታም የእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት እንደ ገና ተደራጀ።

36. ሕዝቅያስና ሕዝቡ ነገሩ ሁሉ እንዲህ በተፋጠነ ሁኔታ እንዲከናወን እግዚአብሔር ስለረዳቸው ሐሴት አደረጉ።