ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ሚካያ በአክዓብ ላይ ትንቢት ተናገረ

1. ኢዮሣፍጥ ታላቅ ሀብትና ክብር ባገኘ ጊዜ ከአክዓብ ጋር በጋብቻ ተሳሰረ።

2. ከጥቂት ዓመታት በኋላም አክዓብን ሊጎበኝ ወደ ሰማርያ ወረደ። አክዓብም ለእርሱና አብሮት ለነበረው ሕዝብ ብዙ በግና በሬ ዐረደ፤ ከዚያም በሬማት ዘገለዓድ ላይ አደጋ እንዲጥል አግባባው።

3. የእስራኤል ንጉሥ አክዓብም የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “ሬማት ዘገለዓድን ለመውጋት አብረኸኝ ትሄዳለህን?” ሲል ጠየቀው። ኢዮሣፍጥም፣ “እኔ እንደ አንተው ነኝ፤ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ ነው፤ በጦርነቱ አብረናችሁ እንሰለፋለን” ሲል መለሰለት።

4. ደግሞም ኢዮሣፍጥ የእስራኤልን ንጉሥ፣ “አስቀድመህ ግን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ጠይቅ” አለው።

5. ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ አራት መቶ ነቢያትን በአንድነት ሰብስቦ፣ “ሬማት ዘገለዓድን ለመውጋት ልሂድን ወይስ ልቅር?” ሲል ጠየቃቸው።እነርሱም፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ሂድ” ብለው መለሱለት።

6. ኢዮሣፍጥ ግን፣ “እንጠይቀው ዘንድ ሌላ የእግዚአብሔር ነቢይ እዚህ የለምን?” አለ።

7. የእስራኤልም ንጉሥ ለኢዮሣፍጥ፣ “መኖሩንማ በእርሱ አማካይነት የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምንጠይቅበት አንድ ሰው አሁንም አለ፤ ነገር ግን ምንጊዜም ቢሆን ስለ እኔ ክፉ እንጂ ደግ ትንቢት ስለማይናገር እጠላዋለሁ፤ እርሱም የይምላ ልጅ ሚካያ ነው” ሲል መለሰ።ኢዮሳፍጥም፣ “ንጉሥ እንዲህ ማለት አይገባውም” አለው።

8. የእስራኤልም ንጉሥ ከሹማምቱ አንዱን ጠርቶ “ሂድና የይምላን ልጅ ሚካያን በፍጥነት አምጣው” አለው።

9. የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ልብሰ መንግሥታቸውን ለብሰው፣ በሰማርያ ቅጥር በር መግቢያ አጠገብ ባለው ዐውድማ ላይ በየዙፋናቸው ተቀምጠው፣ ነቢያቱ ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር።

10. የክንዓና ልጅ ሴዴቅያስም የብረት ቀንዶች ሠርቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሶርያውያን እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ትወጋቸዋለህ” አለ።

11. ሌሎቹ ነቢያት ሁሉ፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና፣ በሬማት ገለዓድ ላይ አደጋ ጣልባት” በማለት ተመሳሳይ ትንቢት ይናገሩ ነበር።

12. ሚካያን ሊጠራ ሄዶ የነበረውም መልእክተኛ፣ “እነሆ፣ ሌሎቹ ነቢያት በአንድ አፍ ሆነው፣ ንጉሡ ድል እንደሚያደርግ እየተነበዩ ነው፤ ያንተም ቃል እንደቃላቸው ይሁን፤ ንጉሡን ደስ የሚያሰኘውን ተናገር” አለው።

13. ሚካያ ግን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! አምላኬ የሚለውን ብቻ እናገራለሁ” አለ።

14. እዚያ በደረሰም ጊዜ ንጉሡ፣ “ሚካያ ሆይ፤ ሬማት ዘገለዓድን ለመውጋት እንሂድ ወይስ ልቅር?” ሲል ጠየቀው።እርሱም መልሶ፣ “ሂዱና ድል አድርጉ፤ በእጃችሁ አልፈው ይሰጣሉና” አለው።

15. ንጉሡም፣ “ከእውነት በቀር ምንም ነገር በእግዚአብሔር ስም እንዳትነግረኝ ስንት ጊዜ አምልሃለሁ?” አለው።

16. ከዚያም ሚካያ “እስራኤል ሁሉ እረኛ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበታትነው አየሁ፤ እግዚአብሔርም፣ ‘እነዚህ ሰዎች ጌታ የላቸውም፤ እያንዳንዱም በሰላም ወደየቤቱ ይመለስ’ ብሎአል” ሲል መለሰ።

17. የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “ስለ እኔ ክፉ ብቻ እንጂ፣ ደግ ትንቢት እንደማ ይናገር አልነገርሁህምን?” አለው።

18. ሚካያም በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ፣ የሰማይም ሰራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ።

19. እግዚአብሔርም፣ ‘የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ በሬማት ገለዓድ ላይ ዘምቶ እዚያው እንዲሞት ማን ያሳስተው?’ አለ።“አንዱ አንድ ሐሳብ፣ ሌላውም ሌላ ሐሳብ አቀረበ።

20. በመጨረሻም አንድ መንፈስ ወደ ፊት ወጥቶ፣ በእግዚአብሔር ፊት በመቆም፣ ‘እኔ አሳስተዋለሁ’ አለ።“እግዚአብሔርም፣ ‘እንዴት አድርገህ?’ ሲል ጠየቀው።

21. “እርሱም፣ ‘እሄድና በነቢያቱ ሁሉ አፍ የሐሰት መንፈስ እሆናለሁ’ አለ።“እግዚአብሔርም፣ ‘እንግዲያውስ ሂደህ አሳስተው፤ ይሳካልሃልም’ አለው።

22. “አሁንም እነሆ፣ እግዚአብሔር በእነዚህ ነቢያትህ አፍ የሐሰት መንፈስ አኖረ፤ እግዚአብሔርም ጥፋት አዞብሃል”።

23. ከዚያም የክንዓናም ልጅ ሴዴቅያስ ወጥቶ ሚካያን በጥፊ መታውና፣ “ለመሆኑ የእግዚአብሔር መንፈስ አንተን ያነጋገረህ፣ በየት በኩል አልፎኝ ነው?” አለው።

24. ሚካያም፣ “ለመሸሸግ ወደ እልፍኝህ በምትሄድበት በዚያ ዕለት ታገኘዋለህ” አለው።

25. ከዚያም የእስራኤል ንጉሥ እንዲህ ሲል አዘዘ፤ “ሚካያን ይዛችሁ ወደ ከተማዪቱ ገዥ ወደ አሞንና ወደ ንጉሡ ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሳችሁ ላኩት፤

26. እነርሱንም፣ ‘ንጉሡ፣ ይህን ሰው እስር ቤት አስገቡት፤ በደህና እስክመለስም ድረስ ከደረቅ ቂጣና ከውሃ በስተቀር ምንም አትስጡት ብሎአል’ በሏቸው።”

27. ሚካያም፣ “አንተ በደኅና ከተመለስክማ እግዚአብሔር በእኔ አልተናገረም ማለት ነው!” አለ፤ ቀጥሎም፣ “እናንተ ሰዎች ሁላችሁ ስሙኝ” አለ።

አክዓብ በሬማት ገለዓድ ተገደለ

28. ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ሬማት ገለዓድ ወጡ።

29. የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “እኔ ልብሴን ለውጬ ወደ ጦርነቱ እገባለሁ፤ አንተ ግን ልብሰ መንግሥትህን ልበስ” አለው። ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ልብሱን ለውጦ ሌላ ሰው መስሎ ወደ ጦርነቱ ገባ።

30. በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ የሠረገላ አዛዦቹን፣ “ከእስራኤል ንጉሥ በቀር፣ ትንሽም ሆነ ትልቅ ከሌላ ከማንም ጋር አትዋጉ” ብሎ አዘዛቸው።

31. የሠረገላው አዛዦችም ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ፣ “የእስራኤል ንጉሥ ይህ ነው” ብለው አሰቡ፤ ሊወጉትም ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥ ግን ጮኸ፤ እግዚአብሔርም ረዳው፤ አምላክም ከእርሱ መለሳቸው፤

32. የሠረገላ አዛዦቹም የእስራኤል ንጉሥ አለመሆኑን በተረዱ ጊዜ እርሱን ከማሳደድ ተመለሱ።

33. ይሁን እንጂ ቀስቱን በነሲብ ቢያስፈነጥረው በጥሩሩ መጋጠሚያዎች መካከል አልፎ የእስራኤልን ንጉሥ ወጋው። ንጉሡም ሠረገላ ነጂውን “ተመለስና ከጦርነቱ አውጣኝ፤ ቈስያለሁና” አለው።

34. ጦርነቱ ቀኑን ሙሉ እንደ ተፋፋመዋለ፤ የእስራኤልም ንጉሥ በሶርያውያን ፊት ለፊት በሠረገላው ላይ እስከ ምሽት ድረስ ተደግፎ ነበር፤ ፀሓይ ስትጠልቅም ሞተ።