ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የአሳ የመጨረሻ ዓመታት

1. አሳ በነገሠ በሠላሳ ስድስተኛው ዓመት፣ የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ በይሁዳ ላይ ዘምቶ፣ ከእስራኤል ንጉሥ ከአሳ ግዛት ማንም እንዳይወጣ፣ ወደዚያም ማንም እንደይገባ ለመከልከል ራማን መሸገ።

2. አሳም ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና ከራሱም ቤተ መንግሥት ግምጃ ቤቶች ብርና ወርቅ ወስዶ በደማስቆ ተቀምጦ ይገዛ ለነበረው ለሶርያ ንጉሥ ለወልደ አዴር ላከ፤

3. ከዚያም “ቀድሞ በአባቴና በአባትህ መካከል እንደ ነበረው ሁሉ፣ ዛሬም በእኔና በአንተ መካከል የስምምነት ውል ይኑረን፤ እነሆ፤ ብርና ወርቅ ልኬልሃለሁ፤ ከእኔ ተመልሶ ይሄድ ዘንድ ከባኦስ ጋር ያደረግኸውን የስምምነት ውል አፍርስ” አለው።

4. ወልደአዴር የንጉሥ አሳን ሐሳብ ተቀበለ፤ የጦር አዛዦቹንም በእስራኤል ከተሞች ላይ አዘመተ። እነርሱ ዒዮንን፣ ዳንን፣ አቤልማ ይምንና የንፍታሌምን የዕቃ ግምጃ ቤት ከተሞች ሁሉ ድል አድርገው ያዙ።

5. ባኦስ ይህን በሰማ ጊዜ ራማን መገንባቱን አቆመ፤ ሥራውንም አቋረጠ።

6. ንጉሥ አሳም የይሁዳን ሰዎች ሁሉ አመጣቸው፤ እነርሱም ባኦስ ይሠራበት የነበረውን ድንጋይና እንጨት ወሰዱ፤ አሳም ጌባንና ምጽጳን ሠራባት።

7. በዚያን ጊዜም ባለ ራእዩ አናኒ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ መጥቶ እንዲህ አለው፤ “በአምላክህ በእግዚአብሔር ሳይሆን በሶርያ ንጉሥ ስለ ታመንህ፣ የሶርያ ንጉሥ ሰራዊት ከእጅህ አምልጦአል።

8. ኢትዮጵያውያንና ሊቢያውያን ብዙ ቊጥር ካላቸው ሠረገላዎቻቸውና ፈረሶቻቸው ጋር ኀያል ሰራዊት አልነበሩምን? ይሁን እንጂ በእግዚአብሔር ስለ ታመንህ በእጅህ አሳልፎ ሰጠህ፤

9. በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን ለማበርታት የእግዚአብሔር ዐይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉና። የሞኝነት ሥራ ስለ ሠራህ ከእንግዲህ ወዲያ ጦርነት አይለይህም።

10. ከዚህ የተነሣም አሳ ባለ ራእዩን ተቈጣው፤ በጣም ስለ ተናደደም እስር ቤት አስገባው። በዚያን ጊዜም አሳ አንዳንድ ሰዎችን ክፉኛ አስጨነቃቸው።

11. በአሳ ዘመነ መንግሥት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የተከናወነው ሥራ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መዛግብት ተጽፎአል።

12. አሳ በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት እግሮቹን ክፉኛ ታመመ፤ ሕመሙ ቢጸናበትም እንኳ፣ በዚያ ሁሉ ሕመም የባለ መድኃኒቶችን እንጂ የእግዚአብሔርን ርዳታ አልፈለገም።

13. አሳም በነገሠ በአርባ አንደኛው ዓመት ሞተ፤ እንደ አባቶቹም ሁሉ አንቀላፋ።

14. በዳዊት ከተማ ከዐለት አስፈልፍሎ ለራሱ ባሠራውም መቃብር ቀበሩት። በቅመማ ቅመምና በልዩ ልዩ ጣፋጭ ሽቱዎች በተሞላ ቃሬዛ ላይ አኖሩት፤ ስለ ክብሩም ትልቅ እሳት አነደዱ።