ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 32 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ሰናክሬም በኢየሩሳሌም ላይ ዛተ

1. ሕዝቅያስ እንዲህ ባለ ታማኝነት ነገሮችን ሁሉ ካከናወነ በኋላ፣ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም መጥቶ ይሁዳን ወረረ። ድል አድርጎ የራሱ ሊያደርጋቸው በማሰብም የተመሸጉትን ከተሞች ከበበ።

2. ሕዝቅያስም ሰናክሬም መምጣቱንና ኢየሩሳሌምንም ለመውጋት ማሰቡን ባወቀ ጊዜ፣

3. ከከተማዪቱ ውጭ ያሉት የውሃ ምንጮች እንዲዘጉ ከሹማምቱና ከጦር አለቆቹ ጋር ተማከረ፤ እነርሱም ረዱት።

4. ብዙ ሰዎችም ተሰብስበው “የአሦር ነገሥታት መጥተው ስለ ምን ብዙ ውሃ ያገኛሉ?” በማለት ምንጮቹን ሁሉና በምድር ውስጥ ለውስጥ ይተላለፍ የነበረውን ውሃ ዘጉ።

5. ከዚህ በኋላም ንጉሡ ጠንክሮ በመሥራት፣ ከቅጥሩ የፈራረሱትን ሁሉ ጠገነ፤ በላዩም ማማ ሠራበት፤ በውጭ በኩልም ሌላ ቅጥር በመገንባት የዳዊትን ከተማ ድጋፍ እርከን አጠናከረ፤ እንደዚሁም ብዙ የጦር መሣሪያዎችንና ጋሻዎችን ሠራ።

6. የጦር መኮንኖችንም በሕዝቡ ላይ ሾሞ በከተማዪቱ በር አደባባይ ላይ በፊቱ ከሰበሰበ በኋላ እንዲህ ሲል አበረታታቸው፤

7. “በርቱ፤ጠንክሩ፤ ከእኛ ጋር ያለው ከእርሱ ጋር ካለው ስለሚበልጥ፣ የአሦርን ንጉሥና አብሮት ያለውን ብዙ ሰራዊት አትፍሩ፤ አትደንግጡም።

8. ከእነርሱ ጋር ያለው የሥጋ ክንድ ሲሆን፣ ከእኛ ጋር ያለው ግን የሚረዳንና ጠላታችንን የሚዋጋልን አምላካችን እግዚአብሔር ነው።” ሕዝቡም የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ በተናገረው ቃል ተበረታታ።

9. ከዚህ በኋላ ሰናክሬም ከሰራዊቱ ሁሉ ጋር ለኪሶን ከቦ ሳለ፣ የሚከተለውን መልእክት በጦር መኮንኖቹ አማካይነት፣ ለሕዝቅያስና ከእርሱ ጋር በኢየሩሳሌም ለነበሩት ለይሁዳ ሕዝብ ላከ፤

10. “የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም የሚለው ይህ ነው፤ በተከበበችው በኢየሩሳሌም እስከዚህ የቈያችሁት በማን ተማምናችሁ ነው?

11. ሕዝቅያስ፣ ‘አምላካችን እግዚአብሔር ከአሦር ንጉሥ እጅ ያድነናል’ ማለቱስ በራብና በጥማት እንድትሞቱ ሊያስታችሁ አይደለምን?

12. ለይሁዳና ለኢየሩሳሌም፣ ‘በአንድ መሠዊያ ፊት ስገዱ፤ በላዩም መሥዋዕት አቃጥሉ’ በማለት የራሱን አምላክ የኰረብታ መስገጃ ስፍራዎችንና መሠዊያዎችን ያስወገደስ ሕዝቅያስ አይደለምን?

13. “እኔና አባቶቼ በሌሎች አገሮች ሕዝቦች ሁሉ ላይ ያደረግነውን አታውቁምን? ታዲያ የእነዚያ መንግሥታት አማልክት ምድራቸውን ከእጄ ለማዳን ችለዋልን?

14. አባቶቼ ካጠፏቸው ከእነዚህ የመንግሥታት አማልክት ሁሉ፣ ሕዝቡን ከእጄ ሊያድን የቻለ ከእነዚህ አምላክ የትኛው ነው? ታዲያ አምላካችሁ እንዴት ከእጄ ሊያድናችሁ ይችላል?

15. አሁንም ሕዝቅያስ በዚህ ዐይነት አያታልላችሁ፤ አያስታችሁም። የየትኛውም አገር ሕዝብ ወይም መንግሥት አምላክ ሕዝቡን ከእጄ ወይም ከአባቶቼ እጅ መታደግ የቻለ ስለሌለ አትመኑት። የእናንተ አምላክማ ከእጄ ያድናችሁ ዘንድ ምንኛ ያንስ!”

16. የሰናክሬም ሹማምትም በእግዚአብሔር አምላክና በባሪያው በሕዝቅያስ ላይ ከዚህ የከፋ ብዙ ነገር ተናገሩ።

17. ንጉሡም እንደዚሁ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን በመሳደብ፣ “የሌሎቹ አገሮች ሕዝቦች አማልክት፣ ከእጄ እንዳልታደጉ ሁሉ፣ የሕዝቅያስም አምላክ ሕዝቡን ከእጄ ሊታደግ አይችልም” ሲል በእርሱ ላይ ደብዳቤ ጻፈ።

18. ከዚያም በማስደንገጥና በማስፈራራት ከተማዪቱን ለመያዝ ሲሉ በቅጥሩ ላይ ወደተቀመጠው ወደ ኢየሩሳሌም ሕዝብ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በዕብራይስጥ ቋንቋ ጮኹ፤

19. የሰው እጅ በሠራቸው በሌሎች የምድር አሕዛብ አማልክት ላይ እንደ ተናገሩት ሁሉ፣ በኢየሩሳሌም አምላክ ላይም ተናገሩ።

20. ንጉሥ ሕዝቅያስና የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስም ስለዚህ ጒዳይ በጸሎት ወደ ሰማይ ጮኹ።

21. እግዚአብሔርም መልአክ ልኮ በአሦር ንጉሥ ሰፈር ተዋጊዎችን፣ መሪዎችንና የጦር መኮንኖችን እንዲያጠፋቸው አደረገ። ስለዚህ ንጉሡ በውርደት ወደ ገዛ አገሩ ተመለሰ። ወደ አምላኩ ቤተ ጣዖት እንደ ገባም፣ የገዛ ወንዶች ልጆቹ በሰይፍ ገደሉት።

22. እግዚአብሔርም ሕዝቅያስንና የኢየሩሳሌምን ሕዝብ ከአሦር ንጉሥ ከሰናክሬምና ከሌሎችም እጅ ሁሉ አዳናቸው፤ በዙሪያቸው ካሉትም ሁሉ ጠበቃቸው፤

23. ብዙዎችም ለእግዚአብሔር መባ ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ ለይሁዳ ንጉሥ ለሕዝቅያስም ውድ የሆኑ ገጸ በረከቶች አመጡለት፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም በአሕዛብ ሁሉ ፊት ከፍ ከፍ አለ።

የሕዝቅያስ ዕብሪት፣ ያከናወናቸው ተግባሮችና ሞቱ

24. በዚያ ጊዜ ሕዝቅያስ ታሞ ሊሞት ተቃርቦ ነበር፤ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ፤ እርሱም መለሰለት፤ ምልክትም ሰጠው።

25. የሕዝቅያስ ልብ ግን ታበየ እንጂ ስለ ተደረገለት በጎ ነገር ተገቢ ምላሽ አልሰጠም፤ በዚህ ምክንያት የእግዚአብሔር ቊጣ በእርሱ፣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ወረደ።

26. ይሁን እንጂ ሕዝቅያስና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ስለ ልባቸው ትዕቢት ራሳቸውን አዋረዱ፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር ቍጣ በዘመነ መንግሥቱ አልመጣባቸውም።

27. ሕዝቅያስ እጅግ ብዙ ሀብትና ክብር ነበረው፤ ከዚህ የተነሣም ለብሩ፣ ለወርቁ፣ ለከበሩት ዕንቁዎቹ፣ ለቅመማ ቅመሞቹ፣ ለጋሻዎቹና ለተለያዩ ውድ ዕቃዎቹ ሁሉ ግምጃ ቤቶችን ሠራ።

28. እንደዚሁም ለእህሉ፣ ለወይን ጠጁና ለዘይቱ ማከማቻ የሚሆኑ ግምጃ ቤቶች ለተለያዩ እንስሳት በረት ለበግና ለፍየል መንጋም በረት ሠራ።

29. እግዚአብሔር ታላቅ ብልጽግና ስለ ሰጠው፤ ብዙ የበግና የፍየል፣ የእንስሳትም መንጋ ሰበሰበ፤ መንደሮችንም ሠራ።

30. የላይኛውን የግዮንን ምንጭ መውጫ ገድቦ፣ ውሃውን በቦይ ቍልቍል ወደ ምዕራቡ የዳዊት ከተማ እንዲወርድ ያደረገም ይኸው ሕዝቅያስ ነበር፤ ሥራውም ሁሉ ተከናወነለት።

31. ነገር ግን በምድሪቱ ላይ ስለ ተፈጸመው ታምራዊ ምልክት እንዲጠይቁት፣ የባቢሎን ገዦች መልእክተኞችን በላኩ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ሊፈትነውና በልቡ ያለውን ሁሉ ሊያውቅ ስለ ፈለገ ተወው።

32. በሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራና ቸርነቱ በአሞጽ ልጅ በነቢዩ በኢሳይያስ ራእይ፣ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል።

33. ሕዝቅያስም እንደ አባቶቹ ሁሉ አንቀላፋ፤ የዳዊት ዘሮች መካነ መቃብር በሆነው ኰረብታም ተቀበረ። በሞተም ጊዜ ይሁዳ ሁሉና የኢየሩሳሌም ሕዝብ በሙሉ አከበሩት። ልጁ ምናሴም በእርሱ ፈንታ ነገሠ።