ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ይህ ሁሉ ከተፈጸመ በኋላ፣ በዚያ የነበሩት እስራኤላውያን ወደ ይሁዳ ከተሞች ወጥተው፣ የማምለኪያ ድንጋዮችን ሰባበሩ፤ የአሼራ ምስል ዐምዶች ቈረጡ፤ እንዲሁም በመላው ይሁዳና በብንያም፣ በኤፍሬምና በምናሴ የነበሩትን የኰረብታ መስገጃዎችና መሠዊያዎች አጠፉ፤ እስራኤላውያን እነዚህን ሁሉ ካጠፉ በኋላ ወደየከተሞቻቸውና ወደየርስታቸው ተመለሱ።

ለካህናት የተደረገ ስጦታ

2. ሕዝቅያስ ካህናቱና ሌዋውያኑ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት እንዲያቀርቡ፣ እንዲያገለግሉና እንዲያመሰግኑ እንዲሁም በእግዚአብሔር ማደሪያ ደጆች ውዳሴውን እንዲዘምሩ፣ ካህናትንም ሆኑ ሌዋውያንን እያንዳንዳቸውን እንደየተግባራቸው በየክፍሉ መደባቸው።

3. በእግዚአብሔር ሕግ እንደ ተጻፈው ንጉሡ ጠዋትና ማታ እንደዚሁም በየሰንበቱ፣ በየወሩ መባቻውና በተወሰኑ በዓላት፣ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ከራሱ ንብረት ሰጠ።

4. ካህናቱና ሌዋውያኑም ሙሉ ጊዜአቸውን ለእግዚአብሔር ሕግ አገልግሎት ማዋል ይችሉ ዘንድ፣ በኢየሩሳሌም የሚኖረው ሕዝብ ተገቢውን ድርሻ እንዲሰጣቸው አዘዘ።

5. ትእዛዙ እንደ ወጣ እስራኤላውያን ወዲያውኑ የእህሉንና የአዲሱን ወይን ጠጅ፣ የዘይቱንና የማሩን እንዲሁም የዕርሻውን ፍሬ ሁሉ በኵራት በልግሥና ሰጡ፤ ካላቸው ከማንኛውም ነገር ሁሉ ላይ እጅግ ብዙ የሆነ ዐሥራት አውጥተው አመጡ።

6. በይሁዳ ከተሞች ይኖሩ የነበሩት የእስራኤልና የይሁዳ ሰዎችም ከከብቶቻቸው፣ ከበግና ከፍየል መንጎቻቸውና ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር ከለዩአቸው የተቀደሱ ነገሮች ዐሥራት አውጥተው አመጡ፤ ከመሩትም።

7. ይህንም በሦስተኛው ወር ጀምረው፣ በሰባተኛው ወር አጠናቀቁ።

8. ሕዝቅያስና ሹማምቱም መጥተው ክምሩን ባዩ ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ ሕዝቡን እስራኤልንም ባረኩ።

9. ሕዝቅያስም ካህናቱንና ሌዋውያኑን ስለ ክምሩ ጠየቃቸው፤

10. ከሳዶቅ ቤተ ሰብ የሆነው ሊቀ ካህናቱ ዓዛርያስም፣ “ሕዝቡ ስጦታውን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ማምጣት ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ በቂ ምግብ አግኝተናል፤ ብዙም ተርፎናል፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን ስለባረከም ይህን ያህል ብዛት ያለው ሊተርፍ ችሎአል” አለ።

11. ሕዝቅያስም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ጎተራ እንዲያዘጋጁ አዘዛቸው፤ እነርሱም አዘጋጁ።

12. ከዚያም ስጦታውን፣ ዐሥራቱንና የተቀደሱ ስጦታዎቹን በታማኝነት አምጥተው አስገቡ። ሌዋዊው ኮናንያ የእነዚሁ ዕቃዎች ኀላፊ ሲሆን ወንድሙ ስሜኢ ደግሞ በማዕረግ ሁለተኛ ነበር።

13. ይሒዒል፣ ዓዛዝያ፣ ናሖት፣ አሣሄል፣ ይሬሞት፣ ዮዛባት፣ ኤሊኤል፣ ሰማኪያ፣ መሐትና በናያስ በንጉሡ ሕዝቅያስና በእግዚአብሔር ቤት ኀላፊ በዓዛርያስ ተሹመው በኮናንያና በወንድሙ በሰሜኢ ሥር ሆነው ተቈጣጣሪዎች ነበሩ።

14. የምሥራቁ በር ጠባቂ የሆነው የሌዋዊው የይምና ልጅ፣ ቆሬ ደግሞ በበጎ ፈቃድ፣ ለእግዚአብሔር በቀረበው ስጦታ ላይ የእግዚአብሔርን መባና የተቀደሱትንም ነገሮች ለማከፋፈል፣ ኀላፊ ነበረ።

15. ዔድን፣ ሚንያሚን፣ ኢያሱ፣ ሸማያ፣ አማርያና ሴኬንያ በካህናቱ ከተሞች ተገኝተው፣ ለካህናት ወገኖቻቸው ለታላላቆቹም ሆነ ለታናናሾቹ፣ እንደየምድባቸው፣ በማከፋፈሉ ረገድ በታማኝነት ረዱት።

16. በተጨማሪም፣ ስማቸው በትውልድ መዝገቡ ውስጥ የነበረና የየዕለቱ ልዩ ልዩ ተግባራቸውን እንደየኀላፊነታቸው መጠንና እንደየምድብ ሥራቸው ለማከናወን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መግባት ለሚችሉት፣ ዕድሜአቸው ሦስት ዓመትና ከዚያም በላይ ለሆናቸው ወንዶች ልጆች እንደዚሁ አከፋፈሉ።

17. በትውልድ መዝገብ በየቤተ ሰባቸው ተቈጥረው ለገቡት ካህናት፣ ዕድሜአቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ለሆናቸው ሌዋውያን እንደየኀላፊነታቸው መጠንና እንደየምድብ ሥራቸው አካፈሏቸው።

18. በዚህ የትውልድ መዝገብ ላይ የተዘረዘሩትን መላውን የማኅበረሰቡን ሕፃናት፣ ሚስቶችን፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ጨመሯቸው፤ ራሳቸውን በመቀደስ ታማኞች ነበሩና።

19. በከተሞቻቸው ዙሪያ ባሉት የዕርሻ ቦታዎች፣ ወይም በሌሎች ከተሞች ሁሉ ለሚኖሩት ለካህናቱ ለአሮን ዘሮች፣ በመካከላቸው ላሉት ወንዶችና በሌዋውያን የትውልድ መዝገብ ለተመዘገቡት ሁሉ እንዲያከፋፍሉ በየስማቸው የተጻፉ ሰዎች ነበሩ።

20. ሕዝቅያስ በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት መልካም፣ ቅንና ታማኝ ሆኖ በመገኘት በመላው ይሁዳ የፈጸመው ተግባር ይህ ነው።

21. የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በማገልገልም ሆነ፣ ለእግዚአብሔር ሕግና ትእዛዝ በመገዛት አንጻር ያደረገውን ሁሉ በፍጹም ልቡ አምላኩን በመፈለግ አከናወነ፤ ተሳካለትም።