ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 7 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የቤተ መቅደሱ መመረቅ

1. ሰሎሞን ጸሎቱን በፈጸመ ጊዜ እሳት ከሰማይ ወርዶ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሌላውንም መሥዋዕት በላ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ቤተ መቅደሱን ሞላው።

2. የእግዚአብሔር ክብር የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ስለ ሞላው ካህናቱ ወደዚያ መግባት አልቻሉም።

3. እስራኤላውያንም ሁሉ እሳቱ ሲወርድ፣ የእግዚአብሔርንም ክብር ከቤተ መቅደሱ በላይ ሲያዩ፣ በመተላለፊያው ወለል ላይ ተንበረከኩ፤ በግንባራቸውም ወደ መሬት ተደፍተው ሰገዱ፤ እንዲህ እያሉም ለእግዚአብሔር ምስጋና አቀረቡ፤“እርሱ ቸር ነውና፤ፍቅሩም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”እያሉም እግዚአብሔርን አመሰገኑ።

4. ከዚህ በኋላ ንጉሡና ሕዝቡ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት መሥዋዕት አቀረቡ።

5. ንጉሥ ሰሎሞንም ሃያ ሁለት ሺህ በሬ፣ መቶ ሃያ ሺህ በግና ፍየል ሠዋ፤ ንጉሡና ሕዝቡም ሁሉ በዚህ ሁኔታ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቀደሱ።

6. ካህናቱም እንደ ሌዋውያኑ፣ ንጉሥ ዳዊት እግዚአብሔር እንዲወደስበት የሠራውንና “ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” በማለት እግዚአብሔርን ባመሰገነ ጊዜ የተቀመጠበትን የእግዚአብሔርን የዜማ መሣሪያ ይዘው በተመደበላቸው ስፍራ ቆሙ። ካህናቱ በሌዋውያኑ ትይዩ ሆነው መለከቶቻቸውን ሲነፉም እስራኤላውያን ሁሉ ቆመው ነበር።

7. ሰሎሞን የሠራው የናስ መሠዊያ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፣ የእህሉን ቊርባንና ስቡን መያዝ ስላልቻሉ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ፊት ለፊት ያለውን የመካከለኛውን አደባባይ ክፍል ቀድሰው፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕቱን ስብ በዚያ አቃጠለ።

8. በዚያን ጊዜ ሰሎሞን ከእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ጋር ለሰባት ቀን በዓሉን አከበረ፤ ሕዝቡም ከሐማት መግቢያ እስከ ግብፅ ወንዝ ድረስ ካለው ምድር የመጣ እጅግ ታላቅ ጉባኤ ነበር።

9. መሠዊያውን ለሰባት ቀን ስለ ቀደሱና የሰባት ቀን በዓል በተጨማሪ ስላከበሩ፣ በስምንተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አደረጉ።

10. ሰሎሞንም በሰባተኛው ወር፣ በሃያ ሦስተኛው ቀን ወደየቤታቸው እንዲሄዱ ሕዝቡን አሰናበተ፤ ሕዝቡም እግዚአብሔር ለዳዊትና ለሰሎሞን እንዲሁም ለሕዝቡ ለእስራኤል ስላደረገው በጎ ነገር ሁሉ በልባቸው ደስ እያላቸውና ሐሤት እያደረጉ ሄዱ።

እግዚአብሔር ለሰሎሞን ተገለጠለት

11. ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና የቤተ መንግሥቱን ሥራ ጨረሰ፤ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና ለራሱ ቤተ መንግሥት ያደርግ ዘንድ በልቡ ያሰበውን ሁሉ ካከናወነ በኋላ፣

12. እግዚአብሔር በሌሊት ተገልጦለት እንዲህ አለው፤“ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ ይህንንም ስፍራ መሥዋዕት የሚቀርብበት ቤተ መቅደስ እንዲሆን ለራሴ መርጬዋለሁ።

13. “ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማያትን በምዘጋበት ጊዜ ወይም ምድሪቱን እንዲበላ አንበጣ በማዝበት ጊዜ፣ ወይም በሕዝቤ ላይ ቸነፈር በምሰድበት ጊዜ፣

14. በስሜ የተጠራው ሕዝቤ ራሱን አዋርዶ ቢጸልይ፣ ፊቴን ቢፈልግና ከክፉ መንገዱ ቢመለስ፣ ከሰማይ እሰማዋለሁ፤ ኀጢአቱን ይቅር እላለሁ፤ ምድሩንም እፈውሳለሁ።

15. አሁንም በዚህ ስፍራ ወደሚጸለየው ጸሎት ዓይኖቼ ይገለጣሉ፤ ጆሮዎቼም ያዳምጣሉ።

16. ስሜ ለዘላለም በዚያ ይኖር ዘንድ ይህን ቤተ መቅደስ መርጫለሁ፤ ቀድሸዋለሁም። ዓይኖቼም ልቤም ዘወትር በዚያ ይሆናሉ።

17. “አንተም ደግሞ አባትህ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ በፊቴ ብትሄድ፣ ያዘዝሁህን ሁሉ ብትፈጽም፣ ሥርዐቶቼንና ሕግጋቴን ብትጠብቅ፣

18. ለአባትህ ለዳዊት፣ ‘ከዘርህ እስራኤልን የሚገዛ አታጣም’ ብዬ በገባሁለት ቃል ኪዳን መሠረት የመንግሥትህን ዙፋን አጸናለሁ።

19. “እናንተ ግን እኔን ከመከተል ተመልሳችሁ የሰጠኋችሁን ሥርዐቴንና ትእዛዜን ብትተው፣ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታገለግሉና ብታመልኩ፣

20. በዚያን ጊዜ እስራኤልን ከሰጠኋቸው ምድሬ እነቅላቸዋለሁ፤ ለስሜ የቀደስሁትን ይህን ቤተ መቅደስ እተዋለሁ፤ በሕዝቦችም ሁሉ ዘንድ መተረቻና መዘባበቻ አደርገዋለሁ።

21. ይህ ቤተ መቅደስ አሁን እጅግ የሚያስደንቅ ቢሆንም በአጠገቡ የሚያልፉ ሁሉ በመገረም፤ ‘እግዚአብሔር በዚህች ምድርና በዚህ ቤተ መቅደስ ላይ እንዲህ ያለውን ነገር ያመጣው ከቶ ለምን ይሆን?’ ይላሉ፤

22. ሕዝቡም፣ ‘ይህን ሁሉ ጥፋት ያመጣባቸው፣ ከግብፅ ምድር ያወጣቸውን የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ትተው ሌሎችን አማልክት ስለ ተከተሉ፣ ስላመለኳቸውና ስላገለገሏቸው ነው’ ብለው ይመልሳሉ።”