ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የዐሥሩ ልጃገረዶች ምሳሌ

1. “በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማይ መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ ዐሥር ልጃገረዶችን ትመስላለች።

2. ከእነርሱም አምስቱ ልጃገረዶች ዝንጉዎች፣ አምስቱ ደግሞ አስተዋዮች ነበሩ፤

3. ዝንጉዎቹ መብራት ይዘው መጠባበቂያ ዘይት አልያዙም ነበር።

4. አስተዋዮቹ ግን ከመብራታቸው ጋር መጠባበቂያ ዘይት በማሰሮ ይዘው ነበር።

5. ሙሽራው በዘገየ ጊዜ፣ ሁሉም እንቅልፍ ተጫጫናቸውና ተኙ።

6. “እኩለ ሌሊት ላይ፣ ‘ሙሽራው እየመጣ ነው፤ ወጥታችሁ ተቀበሉት!’ የሚል ጥሪ ተሰማ።

7. “በዚህ ጊዜ ልጃገረዶቹ ሁሉ ተነሥተው መብራቶቻቸውን እየተረኰሱ መዘጋጀት ያዙ።

8. ዝንጉዎቹ አስተዋዮቹን፣ ‘መብራታችን ሊጠፋብን ስለ ሆነ፣ ከዘይታችሁ ስጡን’ አሏቸው።

9. “አስተዋዮቹ ልጃገረዶች ግን መልሰው፣ ‘ያለን ዘይት ለእኛም ለእናንተም ላይበቃ ስለሚችል፣ ሄዳችሁ ከሻጮች ለራሳችሁ ግዙ’ አሏቸው።

10. “ዘይት ሊገዙ እንደሄዱ፣ ሙሽራው መጣ፤ ተዘጋጅተው የነበሩት ልጃገረዶችም ወደ ሰርጉ ግብዣ አብረውት ገቡ፤ በሩም ተዘጋ።

11. “ዘግየት ብለው ሌሎቹ ልጃገረዶች መጥተው፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤ በሩን ክፈትልን’ አሉ።

12. “እርሱ ግን መልሶ፣ ‘እውነት እላችኋለሁ፣ አላውቃችሁም’ አላቸው።

13. “እንግዲህ ቀኑን ወይም ሰዓቱን ስለማታውቁ ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ።

የሰነፉ አገልጋይ ምሳሌ

14. “የእግዚአብሔር መንግሥት አገልጋዮቹን ጠርቶ ያለውን ንብረት በዐደራ በመስጠት ወደ ሌላ አገር ሊሄድ የተነሣ አንድ ሰውን ትመስላለች፤

15. ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው በመደልደል ለአንዱ አምስት ታላንት፣ ለሌላው ሁለት፣ ለሌላው ደግሞ አንድ ታላንት ሰጥቶ ጒዞውን ቀጠለ።

16. አምስት ታላንት የተቀበለው ሰውዬ ወዲያው በገንዘቡ ንግድ ጀምሮ አምስት ታላንት አተረፈ፤

17. እንዲሁም ሁለት ታላንት የተቀበለው ሁለት አተረፈ፤

18. አንድ ታላንት የተቀበለው ግን መሬት ቈፍሮ የጌታውን ገንዘብ ደበቀ።

19. “የአገልጋዮቹም ጌታ ከብዙ ጊዜ በኋላ ከሄደበት ተመልሶ የሰጣቸውን ገንዘብ ተሳሰበ።

20. አምስት ታላንት የተቀበለውም፣ ሌላ አምስት ተጨማሪ ታላንት ይዞ በመቅረብ፣ ‘ጌታ ሆይ! አምስት ታላንት ዐደራ ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸውልህ አምስት ተጨማሪ ታላንት አትርፌአለሁ’ አለው።

21. “ጌታውም፣ ‘ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ አገልጋይ፤ በትንሽ ነገር ላይ ታማኝ ስለ ሆንህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው።

22. “እንዲሁም ሁለት ታላንት የተቀበለው አገልጋይ ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ሁለት ታላንት ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸው ሁለት ተጨማሪ ታላንት አትርፌአለሁ’ አለው።

23. “ጌታውም፣ ‘ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ አገልጋይ፤ በትንሽ ነገር ላይ ታማኝ ስለ ሆንህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው።

24. “አንድ ታላንት የተቀበለው አገልጋይ ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን ዐውቃለሁ፤

25. ስለዚህ ፈራሁህ፤ ሄጄም መሬት ቈፍሬ ታላንትህን ጕድጓድ ውስጥ ደበቅሁት፤ ገንዘብህ ይኸውልህ’ አለው።

26. “ጌታውም መልሶ፣ ‘አንተ ክፉ፣ ሰነፍ አገልጋይ፤ ካልዘራሁበት የማጭድ፣ ካልበተንሁበትም የምሰበስብ መሆኔን ታውቅ ኖሮአል?

27. ታዲያ፣ በምመለስበት ጊዜ ገንዘቤን ከነወለዱ እንዳገኘው ለለዋጮች መስጠት ይገባህ ነበር።

28. “ ‘በሉ እንግዲህ ታላንቱን ወስዳችሁ ዐሥር ታላንት ላለው ስጡ፤

29. ላለው ይጨመርለታል፤ የተትረፈረፈም ይኖረዋል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።

30. ይህን የማይረባ አገልጋይ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጥታችሁ ጣሉት’ አለ።

የመጨረሻው ፍርድ

31. “የሰው ልጅ ከመላአክቱ ሁሉ ጋር በክብሩ ሲመጣ፣ በክብሩ ዙፋን ላይ ይቀመጣል፤

32. ሕዝቦች ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እርሱም፣ እረኛ በጎችን ከፍየሎች እንደሚለይ፣ ሕዝቡን አንዱን ከሌላው ይለያል፤

33. በጎቹን በቀኙ፣ ፍየሎቹን ግን በግራው ያቆማቸዋል።

34. “በዚያን ጊዜ ንጉሡ በቀኙ በኩል ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል፤ ‘እናንት አባቴ የባረካችሁ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ፤

35. ምክንያቱም ተርቤ አብልታችሁኛል፤ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል፤ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛል፤

36. ታርዤ አልብሳችሁኛል፤ ታምሜ አስታምማችሁኛል፤ ታስሬ ጠይቃችሁኛል።’

37. “ጻድቃንም መልሰው እንዲህ ይሉታል፤ ‘ጌታ ሆይ፤ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህ? ወይም ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ?

38. እንግዳ ሆነህ አይተን መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ?

39. እንዲሁም ታመህ ወይም ታስረህ አይተን መቼ ጠየቅንህ?’

40. “ንጉሡም መልሶ፣ ‘እውነት እላችኋለሁ፣ ከእነዚህ አነስተኛ ከሆኑት ወንድሞቼ ለአንዱ ያደረጋችሁት፣ ለእኔ እንዳደረጋችሁት ነው’ ይላቸዋል።

41. “ከዚያም በግራው በኩል ላሉት ደግሞ እንዲህ ይላቸዋል፤ ‘እናንተ የተረገማችሁ፤ ለዲያብሎስና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀው የዘላለም እሳት ከእኔ ተለይታችሁ ሂዱ፤

42. ምክንያቱም ተርቤ አላበላችሁኝም፤ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝም፤

43. እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝም፤ ታርዤ አላለበሳችሁኝም፤ ታምሜና ታስሬ አልጠየቃችሁኝም።’

44. “እነርሱም መልሰው፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ተርበህ ወይም ተጠምተህ፣ እንግዳ ሆነህ ወይም ታርዘህ፣ ታመህ ወይም ታስረህ ዐይተን መቼ አልደረስንልህም’ ይሉታል።

45. “በዚያን ጊዜ እርሱም መልሶ፣ ‘እውነት እላችኋለሁ፣ ከእነዚህ አነስተኛ ከሆኑት ወንድሞቼ ለአንዱ አለማድረጋችሁ፣ ለእኔ እንዳላደረጋችሁት ነው’ ይላቸዋል።

46. “እነዚህም ወደ ዘላለም ፍርድ፣ ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።”