ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 7 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በሌሎች ላይ አለመፍረድ

1. “እንዳይፈረድባችሁ በማንም ሰው ላይ አትፍረዱ፤

2. በምትፈርዱበትም ዐይነት ይፈረድባችኋል፤ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል።

3. “በዐይንህ ውስጥ ያለውን ግንድ ሳትመለከት፣ በወንድምህ ዐይን ያለውን ጕድፍ ለምን ታያለህ?

4. በዐይንህ ውስጥ ግንድ እያለ ወንድምህን፣ ‘ዐይንህ ውስጥ ያለውን ጕድፍ ላውጣልህ’ ማለት እንዴት ትችላለህ?

5. አንተ ግብዝ፤ አስቀድመህ በዐይንህ ውስጥ ያለውን ግንድ አውጣ፤ ከዚያም በወንድምህ ዐይን ውስጥ ያለውን ጕድፍ ለማውጣት አጥርተህ ታያለህ።

6. “በእግራቸው እንዳይረግጡት፣ ተመልሰውም ነክሰው እንዳይቦጫጭቋችሁ፣ የተቀደሰ ነገር ለውሾች አትስጡ፤ ዕንቈቻችሁንም በእሪያ ፊት አትጣሉ።

ለምኑ፤ ፈልጉ፤ አንኳኩ

7. “ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ አንኳኩ፣ በሩም ይከፈትላችኋል።

8. የሚለምን ሁሉ ይሰጠዋል፤ የሚፈልግም ያገኛል፤ ለሚያንኳኳም በሩ ይከፈትለታል።

9. “ከእናንት መካከል ልጁ ዳቦ ቢለምነው፣ ድንጋይ የሚሰጥ አባት አለ?

10. ወይንም ዓሣ ቢለምነው እባብ የሚሰጥ ይኖራልን?

11. ታዲያ እናንት ክፉዎች ሳላችሁ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ፣ የሰማዩ አባታችሁማ ለሚለምኑት መልካም ስጦታን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸውም?

12. ሌሎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር እናንተም አድርጉላቸው፤ ኦሪትም፣ ነቢያትም በዚህ ይጠቃለላሉና።

ጠባቡና ሰፊው በር

13. “በጠባቡ በር ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው መንገድ ትልቅ፣ በሩም ሰፊ ነውና፤ ብዙዎችም በዚያ ይገባሉ።

14. ወደ ሕይወት የሚያደርሰው ግን መንገዱ ቀጭን፣ በሩም ጠባብ ነው፤ የሚገቡበትም ጥቂቶች ብቻ ናቸው።

ሐሰተኛ ነቢያት

15. “በውስጣቸው ነጣቂ ተኵላዎች ሆነው ሳሉ የበግ ለምድ ለብሰው መካከላችሁ በመግባት ከሚያሸምቁ ሐሰተኛ ነቢያት ተጠንቀቁ።

16. ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ፤ ከእሾህ ቍጥቋጦ ወይን፣ ከኵርንችትስ በለስ ይለቀማልን?

17. እንዲሁም ጥሩ ዛፍ ሁሉ ጥሩ ፍሬ፣ መጥፎ ዛፍ ግን መጥፎ ፍሬ ያፈራል።

18. ጥሩ ዛፍ መጥፎ ፍሬ፣ መጥፎም ዛፍ ጥሩ ፍሬ ማፍራት አይችልም።

19. ጥሩ ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል።

20. ስለዚህ በፍሬአቸው ታውቋቸዋላችሁ።

21. “በሰማይ ያለውን ያባቴን ፈቃድ ሳይፈጽም ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማይ አይገባም።

22. በዚያ ቀን ብዙዎች፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህ አጋንንት አላወጣንምን? በስምህስ ብዙ ታምራት አላደረግንምን?’ ይሉኛል።

23. በዚያ ጊዜ፣ ‘ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንት ክፉዎች፤ ከእኔ ራቁ’ ብዬ በግልጽ እነግራቸዋለሁ።

ብልኁና ሞኙ ቤት ሠሪ

24. “እንግዲህ ይህን ቃሌን ሰምቶ በተግባር የሚያውል፣ ቤቱን በዐለት ላይ የሠራን ብልኅ ሰው ይመስላል።

25. ዶፍ ወረደ፤ ጐርፍም ጐረፈ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ያንን ቤት መታው፤ በዐለት መሠረትም ላይ ስለ ተመሠረተ አልወደቀም።

26. ይህን ቃሌን ሰምቶ በተግባር የማያውለው ግን ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራን ሞኝ ሰው ይመስላል።

27. ዶፍ ወረደ፤ ጐርፍም ጐረፈ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ያንን ቤት መታው፤ ቤቱም ወደቀ፤ አወዳደቁም የከፋ ነበር።”

28. ኢየሱስ ማስተማሩን በፈጸመ ጊዜ፣ ሕዝቡ በትምህርቱ ተደነቁ።

29. ምክንያቱም እንደ አይሁድ ሃይማኖት መምህራናቸው ሳይሆን እንደ ባለ ሥልጣን አስተምሮአቸው ስለ ነበር ነው።