ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

አይሁድ በኢየሱስ ላይ መዶለታቸው

1. ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ፣ ደቀ መዛሙርቱን፣

2. “ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካ እንደሚሆን ታውቃላችሁ፤ የሰው ልጅም ሊሰቀል አልፎ ይሰጣል” አላቸው።

3. ከዚህ በኋላ የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች ቀያፋ በተባለ ሊቀ ካህን ግቢ ውስጥ ተሰብስበው፤

4. በረቀቀ መንገድ ኢየሱስን ለማስያዝና ለማስገደል ተማከሩ።

5. ነገር ግን፣ “በሕዝቡ መካከል ረብሻ እንዳይነሣ በበዓል ቀን አይሁን” በማለት ተስማሙ።

ኢየሱስን ሽቶ የቀባችው ሴት

6. ኢየሱስ በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ፣

7. አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ አንድ ብልቃጥ የአልባስጥሮስ ሽቶ ይዛ ወደ እርሱ ቀረበች፤ በማእድ ላይ ተቀምጦ ሳለም በራሱ ላይ አፈሰሰችው።

8. ደቀ መዛሙርቱ ይህንን በተመለከቱ ጊዜ ተቈጥተው እንዲህ አሉ፤ “ይህ ሁሉ ብክነት ለምንድ ነው?

9. ሽቶው በብዙ ዋጋ ተሽጦ ገንዘቡን ለድኾች መስጠት ሲቻል!”

10. ኢየሱስ ይህን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “ይህችን ሴት ለምን ታስቸግሯታላችሁ? መልካም ነገር አድርጋልኛለች፤

11. ድኾች ምንጊዜም ከእናንተ ጋር ናቸው፤ እኔ ግን ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር አልሆንም።

12. ሽቶውን በሰውነቴ ላይ በማፍሰሷ፣ እኔን ለቀብር ለማዘጋጀት ነው፤

13. እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ወንጌል በሚሰበክበት በዓለም ዙሪያ ሁሉ፣ በየትኛውም ስፍራ እርሷ ያደረገችው በመታሰቢያነት ይነገርላታል።”

ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ተስማማ

14. ከዚህ በኋላ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የነበረውና የአስቆሮቱ ይሁዳ የተባለው ወደ ካህናት አለቆች ሄዶ፣

15. “እርሱን አሳልፌ ብሰጣችሁ እናንተስ ምን ትሰጡኛላችሁ?” አላቸው። እነርሱም ሠላሳ ጥሬ ብር ቈጥረው ሰጡት።

16. ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይሁዳ፣ ኢየሱስን አሳልፎ የሚሰጥበትን አመቺ ጊዜ ይፈልግ ነበር።

የጌታ ራት

17. በቂጣ በዓል የመጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “ፋሲካን እንድትበላ የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት።

18. እርሱም፣ “ወደ ከተማ ሄዳችሁ እገሌ የተባለውን ሰው፣ ‘መምህር ጊዜዬ ተቃርቦአልና ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን በቤትህ አከብራለሁ ብሏል’ በሉት” አላቸው።

19. ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ ባዘዛቸው መሠረት የፋሲካን ራት አዘጋጁ።

20. በመሸም ጊዜ ኢየሱስ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር በማእድ ተቀመጠ፤

21. በመብላት ላይ ሳሉም፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አላቸው።

22. እነርሱም እጅግ አዝነው፣ ተራ በተራ፣ “ጌታ ሆይ፤ እኔ እሆን ይሆን?” አሉት።

23. እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “አሳልፎ የሚሰጠኝ ከእኔ ጋር እጁን ከወጭቱ ውስጥ ያጠለቀው ነው፤

24. የሰው ልጅ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈው ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ለዚያ ሰው ሳይወለድ ቢቀር ይሻለው ነበር።”

25. አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም፣ “መምህር ሆይ፣ እኔ እሆንን?” አለው።እርሱም፣ “አንተ አልህ” አለው።

26. እየበሉ ሳሉ፣ ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ በመስጠት፣ “እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ሥጋዬ ነው” አላቸው።

27. ከዚያም ጽዋውን አንሥቶ አመሰገነ፤ ለደቀ መዛሙርቱም በመስጠት እንዲህ አላቸው፤ “ሁላችሁም ከዚህ ጠጡ፤

28. ስለ ብዙዎች የኀጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው።

29. እላችኋለሁ፤ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋር በአዲስ መልክ እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ፣ ከእንግዲህ ከዚህ የወይን ፍሬ አልጠጣም።”

30. መዝሙር ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ።

የጴጥሮስ ክህደት አስቀድሞ መነገሩ

31. ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “ሁላችሁም በዚህች ሌሊት በእኔ ተሰናክላችሁ ትሄዳላችሁ፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና፤ “ ‘እረኛውን እመታለሁ፤ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ።’

32. ነገር ግን ከተነሣሁ በኋላ ቀድሜአችሁ ወደ ገሊላ እሄዳለሁ።”

33. ጴጥሮስም መልሶ፣ “ሌሎች በሙሉ ባንተ ምክንያት ቢሰናከሉ እንኳ እኔ በፍጹም አልሰናከልም!” አለው።

34. ኢየሱስም፣ “እውነት እልሃለሁ፤ በዛሬዋ ሌሊት ዶሮ ከመጮኹ በፊት ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው።

35. ጴጥሮስ ግን “ከአንተ ጋር መሞት ቢያስፈልግ እንኳ ከቶ አልክድህም!” አለው። ሌሎቹም ደቀ መዛሙርት በሙሉ እንደዚሁ አሉ።

የኢየሱስ ጸሎት በጌቴሴማኒ

36. ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄደ፤ እነርሱንም፣ “ወደዚያ ሄጄ በምጸልይበት ጊዜ እናንተ እዚህ ተቀመጡ” አላቸው።

37. ከእርሱም ጋር ጴጥሮስንና ሁለቱን የዘብዴዎስ ልጆች ይዞ ሄዶ ይተክዝና ይጨነቅ ጀመር፤

38. ከዚያም፣ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዝናለች፤ ከእኔ ጋር በመትጋት እዚሁ ቈዩ” አላቸው።

39. ጥቂት ዕልፍ ብሎ በግንባሩ በመደፋት፣ “አባቴ ሆይ፤ ቢቻል ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ፤ ነገር ግን እኔ እንደምፈልገው ሳይሆን አንተ እንደምትፈልገው ይሁን” ብሎ ጸለየ።

40. ከዚያም ተመልሶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሲመጣ፣ ተኝተው አገኛቸው፤ ጴጥሮስንም እንዲህ አለው፤ “እንግዲህ፤ ከእኔ ጋር ለአንድ ሰዓት እንኳ መትጋት አቃታችሁን?

41. ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጕና ጸልዩ፤ መንፈስ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው።”

42. እንደ ገና ለሁለተኛ ጊዜ ሄዶ፣ “አባት ሆይ፤ ይህ ሳልጠጣው የማያልፍ ጽዋ ከሆነ፣ ፈቃድህ ይፈጸም” ብሎ ጸለየ።

43. እንደ ገናም በመጣ ጊዜ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ስለ ነበር ተኝተው አገኛቸው።

44. ትቶአቸውም እንደ ገና በመሄድ ለሦስተኛ ጊዜ ቀደም ብሎ የጸለየውን ጸሎት ደገመ።

45. ከዚያም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሶ እንዲህ አላቸው፤ “አሁንም ዐርፋችሁ ተኝታችኋል? እነሆ፣ ሰዓቱ ቀርቦአል፤ የሰው ልጅ በኀጢአተኞች እጅ ዐልፎ ይሰጣል፤

46. ተነሡ እንሂድ፤ አሳልፎ የሚሰጠኝም እየመጣ ነው።”

የኢየሱስ መያዝ

47. በመናገር ላይ እያለ፣ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፤ ከካህናት አለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሌዎች ዘንድ የተላኩ ሰይፍና ዱላ የያዙ ብዙ ሰዎችም አብረውት ነበሩ።

48. ይሁዳም፣ “እኔ የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት” ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ስለ ነበር፣

49. በቀጥታ ወደ ኢየሱስ ሄዶ፣ “መምህር ሆይ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን” በማለት ሳመው።

50. ኢየሱስም፣ “ወዳጄ ሆይ፤ የመጣህበትን ፈጽም” አለው።በዚህ ጊዜ ሰዎቹ ቀርበው ኢየሱስን ያዙት፤ አሰሩትም።

51. ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ እጁን ዘርግቶ ሰይፉን መዘዘና የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መትቶ ጆሮውን ቈረጠው።

52. ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “በል ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ፤ ሰይፍን የሚመዝዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ።

53. ካስፈለገ አባቴን ብለምነው ከዐሥራ ሁለት ክፍለ ሰራዊት የሚበልጡ መላእክት የማይሰድልኝ ይመስልሃል?

54. ይህ ቢሆን ደግሞ ቅዱሳት መጻሕፍት ይሆናል ያሉት ነገር እንዴት ይፈጸማል?”

55. በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፤ “ወንበዴ እንደሚይዝ ሰው ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ ልትይዙኝ መጣችሁ? በየዕለቱ በቤተ መቅደስ ተቀምጬ ሳስተምር አልያዛችሁኝም ነበር፤

56. ነገር ግን ይህ ሁሉ የሆነው ነቢያት በቅዱሳት መጻሕፍት የተናገሩት ይፈጸም ዘንድ ነው።” በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ጥለውት ሸሹ።

ኢየሱስ በአይሁድ ሸንጎ ፊት

57. በዚህ ጊዜ ኢየሱስን የያዙት ሰዎች፣ የኦሪት የሕግ መምህራንና የሕዝብ ሽማግሌዎች ተሰብስበው ወደነበሩበት፣ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወሰዱት።

58. ነገር ግን ጴጥሮስ ከርቀት ሆኖ እስከ ሊቀ ካህናቱ ቅጥር ግቢ ይከተለው ነበር፤ ወደ ውስጥ ገብቶም የሁኔታውን መጨረሻ ለማየት ከጠባቂዎች ጋር ተቀመጠ።

59. በዚህ ጊዜ የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሸንጎ በሙሉ ኢየሱስን ለማስገደል የሐሰት ማስረጃ ይፈልጉ ነበር፤

60. ብዙ የሐሰት ምስክሮች ቢቀርቡም በቂ ማስረጃ አላገኙም፤ በኋላ ግን ሁለት ሰዎች ቀርበው፣

61. “ይህ ሰው፣ ‘የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አፍርሼ፣ በሦስት ቀን ውስጥ መልሼ ልሠራው እችላለሁ’ ብሎአል” በማለት ተናገሩ።

62. በዚህ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ተነሥቶ በመቆም፣ “እነዚህ ሰዎች ለሚመሰክሩብህ ሁሉ ምንም መልስ አትሰጥምን?” አለው።

63. ኢየሱስ ግን ዝም አለ።ሊቀ ካህናቱም፣ “በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ፤ አንተ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆንህ ንገረን” አለው።

64. ኢየሱስም፣ “አንተው ራስህ ብለኸዋል፤ ነገር ግን ለሁላችሁም ልንገራችሁ፤ ወደ ፊት የሰው ልጅ በኀያሉ ቀኝ ተቀምጦ በሰማይ ደመና ሲመጣ ታዩታላችሁ” አለው።

65. በዚህ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ልብሱን ቀዶ፣ “በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ተናግሮአል፤ ከዚህ ሌላ ምን ምስክርነት ያስፈልገናል? በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል መናገሩን እናንተው ራሳችሁ ሰምታችኋአል፤

66. ምን ይመስላችኋል?” አላቸው።እነርሱም፣ “ሞት ይገባዋል!” ብለው መለሱ።

67. በዚህ ጊዜ ፊቱ ላይ እየተፉ በጡጫ መቱት፤ ሌሎቹም በጥፊ እየመቱት፣

68. “ክርስቶስ ሆይ፤ ማነው የመታህ? እስቲ ትንቢት ንገረን!” አሉት።

ጴጥሮስ ኢየሱስን ካደ

69. ከዚህ በኋላ ጴጥሮስ በሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ ተቀምጦ ሳለ አንዲት የቤት ሠራተኛ ወደ እርሱ ቀርባ፣ “አንተም ከገሊላው ኢየሱስ ጋር ነበርህ” አለችው።

70. እርሱ ግን፣ “ምን እንደምትናገሪ አላውቅም” በማለት በሁላቸውም ፊት ካደ።

71. ከግቢው መውጫ ወደ ሆነው በር ሲያመራ ሌላዋ ሠራተኛ ተመልክታው፣ በዚያ ለነበሩት ሰዎች፣ “ይህ ሰው ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበር” አለች።

72. እርሱም በመሐላ ቃል፣ “ሰውየውን አላውቀውም!” ሲል ዳግመኛ ካደ።

73. ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ በዚያ ቆመው የነበሩት ሰዎች ቀርበው ጴጥሮስን፣ “አነጋገርህ ስለሚያጋልጥህ፣ በርግጥ አንተም ከእነርሱ አንዱ ነህ!” አሉት።

74. እርሱም እየማለና እየተገዘተ፣ “እኔ ሰውየውን አላውቀውም!” አላቸው።ወዲያውም ዶሮ ጮኸ።

75. በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ፣ “ዶሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ብሎ ኢየሱስ የተናገረው ቃል ትዝ አለው፤ ጴጥሮስም ወደ ውጭ ወጥቶ መራራ ልቅሶ አለቀሰ።