ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 5 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የተራራው ስብከት

1. ብዙ ሕዝብ እንደ ተሰበሰበ ባየ ጊዜ፣ ወደ ተራራ ወጣና ተቀመጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ መጡ።

2. እንዲህም እያለ ያስተምራቸው ጀመር፤

3. “በመንፈስ ድኾች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፤ መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ናትና።

4. የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፤ መጽናናትን ያገኛሉና።

5. የዋሆች ብፁዓን ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና።

6. ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፤ ይጠግባሉና።

7. ምሕረት የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፤ ምሕረትን ያገኛሉና።

8. ልባቸው ንጹሕ የሆነ ብፁዓን ናቸው፤ እግዚአብሔርን ያዩታልና።

9. ሰላምን የሚያወርዱ ብፁዓን ናቸው፤ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉና።

10. ስለ ጽድቅ ብለው የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፤ መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ናትና።

11. “ሰዎች በእኔ ምክንያት ቢሰድቧችሁ፣ ቢያሳድዷችሁና ክፉውን ሁሉ በሐሰት ቢያስወሩባችሁ፤ ብፁዓን ናችሁ።

12. በሰማይ የምትቀበሉት ዋጋ ታላቅ ስለ ሆነ ደስ ይበላችሁ፤ ሐሤት አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያት እንደዚሁ አሳደዋቸዋልና።

ጨውና ብርሃን

13. “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው የጨውነት ጣዕሙን ቢያጣ ጣዕሙን መልሶ ሊያገኝ ይችላልን? ወደ ውጪ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ጥቅም አይኖረውም።

14. “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤ በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትደበቅ አትችልም፤

15. ሰዎችም መብራት አብርተው ከዕንቅብ ሥር አያስቀምጡትም፤ በቤት ውስጥ ላሉት ሁሉ እንዲያበራ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጡታል እንጂ።

16. እንደዚሁም ሰዎች መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማይ ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰዎች ፊት ይብራ።

የሕግ ፍጻሜ

17. “ሕግንና የነቢያትን ቃል ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ለመፈጸም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም።

18. እውነት እላችኋለሁ፤ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ ሕግ ሁሉ ይፈጸማል እንጂ ከሕግ አንዲት ፊደል ወይም አንዲት ነጥብ እንኳ አትሻርም።

19. ስለዚህ ማንም ከእነዚህ ትእዛዛት አነስተኛዪቱን እንኳን ቢተላለፍ፣ ሌሎችንም እንዲተላለፉ ቢያስተምር በመንግሥተ ሰማይ ታናሽ ተብሎ ይጠራል፤ ነገር ግን እነዚህን ትእዛዛት እየፈጸመ ሌሎችም እንዲፈጽሙ የሚያስተምር በመንግሥተ ሰማይ ታላቅ ይባላል።

20. ጽድቃችሁ ከፈሪሳውያንና ከኦሪት ሕግ መምህራን ጽድቅ ልቆ ካልተገኘ መንግሥተ ሰማይ መግባት አትችሉም።

ነፍስ መግደል አይገባም

21. “ለቀደሙት ሰዎች፣ ‘አትግደል፤ የገደለ ይፈረድበታል’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል፤

22. እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ወንድሙን ያለ አግባብ የሚቈጣ ይፈረድበታል፤ ማንም ወንድሙን ‘ጅል’ የሚል በሸንጎ ፊት ይጠየቅበታል፤ ‘ደደብ’ የሚለው ደግሞ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይጠብቀዋል።

23. “ስለዚህ መባህን በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር በምታቀርብበት ጊዜ ወንድምህ የተቀየመብህ ነገር መኖሩ ትዝ ቢልህ፣

24. መባህን በዚያው በመሠዊያው ፊት ተወው፤ በመጀመሪያ ሄደህ ከወንድምህ ጋር ተስማማ፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን ለእግዚአብሔር አቅርብ።

25. “የከሰሰህ ባላጋራህ እንዳያስፈርድብህ፣ ዳኛውም ለአሳሪ አሳልፎ እንዳይሰጥህ፣ በወህኒም እንዳትጣል፣ በመንገድ ላይ ሳለህ ከባላጋራህ ጋር ፈጥነህ ተስማማ።

26. እውነት እልሃለሁ፤ ካስፈረደብህ ግን የመጨረሻዋን ሳንቲም እስክትከፍል ድረስ ከዚያ አትወጣም።

ማመንዘር አይገባም

27. “ ‘አታመንዝር’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል።

28. እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ሴትን በምኞት ዓይን የተመለከተ ሁሉ በልቡ ከእርሷ ጋር አመንዝሮአል።

29. ቀኝ ዓይንህ የኀጢአት ሰበብ ቢሆንብህ፣ አውጥተህ ወዲያ ጣለው፤ ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል።

30. ቀኝ እጅህ የኀጢአት ሰበብ ቢሆንብህ ቈርጠህ ወዲያ ጣለው፤ ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል።

31. “ ‘ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ የፍቺ ወረቀት መስጠት አለበት’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል።

32. እኔ ግን እላችኋለሁ፤ በላዩ ላይ ስታመነዝር ካላገኛት በስተቀር፣ ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ እንድታመነዝር ያደርጋታል፤ በዚህ ሁኔታ የተፈታችውን ሴት ያገባም እንዳመነዘረ ይቈጠራል።

ስለ መሐላ

33. “ለቀደሙት ሰዎች፣ ‘በሐሰት አትማል፤ በእግዚአብሔር ፊት የማልኸውንም ጠብቅ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል።

34. እኔ ግን ፈጽሞ አትማሉ እላችኋለሁ፤ በሰማይም ቢሆን አትማሉ፤ የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና፤

35. በምድርም ቢሆን አትማሉ፤ የእግዚአብሔር የእግሩ ማረፊያ ናትና፤ በኢየሩሳሌምም አትማሉ፤ የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና

36. በራስህም ቢሆን አትማል፤ ከጠጕራችሁ መካከል አንዲቷን እንኳ ነጭ ወይም ጥቍር ማድረግ አትችሉምና።

37. ስለዚህ ስትነጋገሩ ቃላችሁ፣ ‘አዎን’ ከሆነ፣ ‘አዎን’፤ አይደለም፣ ከሆነ ‘አይደለም’ ይሁን፤ ከዚህ ውጭ የሆነ ሁሉ ከክፉው የሚመጣ ነውና።

ስለ መበቀል

38. “ ‘ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል።

39. እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ‘ክፉ አድራጊውን ሰው አትቃወሙት’፤ ነገር ግን ቀኝ ጒንጭህን ለሚመታህ ሌላውን ጒንጭህን ደግሞ አዙርለት።

40. አንድ ሰው እጀ ጠባብህን ሊወስድ ቢከስህ ካባህን ጨምረህ ስጠው።

41. አንድ ሰው አንድ ኪሎ ሜትር ተኩል የሚያህል ርቀት እንድትሄድ ቢያስገድድህ ዕጥፉን መንገድ አብረኸው ሂድ።

42. ለሚለምንህ ስጥ፤ ከአንተም ሊበደር የሚሻውን ፊት አትንሣው።

43. “ ‘ወዳጅህን ውደድ፤ ጠላትህን ጥላ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል።

44. እኔ ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ ፤ ለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ እላችኋለሁ።

45. እንደዚህም በማድረጋችሁ በሰማይ ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ፤ እርሱ ፀሓዩን ለክፉዎችና ለደጎች ያወጣል፤ ዝናቡንም ለኀጢአተኞችና ለጻድቃን ያዘንባል።

46. የሚወዷችሁን ብቻ የምትወዱ ከሆነ ምን ዋጋ ታገኛላችሁ? ቀራጮችስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን?

47. ወንድሞቻችሁን ብቻ እጅ የምትነሡ ከሆነ ከሌሎች በምን ትሻላላችሁ? አሕዛብስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን?

48. ስለዚህ የሰማይ አባታችሁ ፍጹም እንደሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ።”