ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

መጥምቁ ዮሐንስ ወደ ኢየሱስ የላከው ጥያቄ

1. ኢየሱስ ለዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ትእዛዙን ሰጥቶ ከጨረሰ በኋላ ለማስተማርና ለመስበክ ወደ ገሊላ ከተሞች ሄደ።

2. ዮሐንስ በእስር ቤት ሆኖ ክርስቶስ በማድረግ ላይ ያለውን ነገር በሰማ ጊዜ፣ ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ልኮ፣

3. “ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀው አንተ ነህ? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ሲል ጠየቀ።

4. ኢየሱስም፣ እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ “ሄዳችሁ የምትሰሙትንና የምታዩትን ለዮሐንስ ንገሩት፤

5. ዕውሮች ያያሉ፤ አንካሶች ይራመዳሉ፤ ለምጻሞች ይነጻሉ፤ ደንቆሮዎች ይሰማሉ፤ ሙታን ይነሣሉ፤ ለድኾችም የምሥራች እየተሰበከ ነው፤

6. በእኔ የማይሰናከልም ብፁዕ ነው።”

7. የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ከሄዱ በኋላ፣ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “ወደ ምድረ በዳ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ሸምበቆ በነፋስ ሲወዛወዝ?

8. ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ባማረ ልብስ ያጌጠ ሰው? ባማረ ልብስ ያጌጡ በነገሥታት ቤት አሉላችሁ።

9. ታዲያ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይ ልታዩ? አዎን፤ ከነቢይም የሚበልጥ ነው።

10. እንዲህ ተብሎ የተጻፈለት እርሱ ነው፤ “ ‘በፊትህ መንገድህን ያዘጋጅልህ ዘንድ፣ ከአንተ አስቀድሜ መልእክተኛዬን እልካለሁ።’

11. እውነት እላችኋለሁ፤ ከሴት ከተወለዱት መካከል እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ያለ አልተነሣም፤ ሆኖም በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል።

12. ከመጥምቁ ዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ መንግሥተ ሰማይ በብዙ ትገፋለች፤ የሚያገኟትም ብርቱዎች ናቸው፤

13. ነቢያትም፣ የሙሴ ሕግም ሁሉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናግረዋልና።

14. እንግዲህ ልትቀበሉት ከፈቀዳችሁ ይመጣል የተባለው ኤልያስ እርሱ ነው።

15. ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ።

16. “ይህን ትውልድ በምን ልመስለው? በገበያ ተቀምጠው ጓደኞቻቸውን እንዲህ እያሉ የሚጣሩ ልጆችን ይመስላሉ፤

17. “ ‘ዋሽንት ነፋንላችሁ፤ አልጨፈራችሁም፤ ሙሾ አወረድንላችሁ፤ አላለቀሳችሁም’

18. ዮሐንስ ከመብልና ከመጠጥ ተቈጥቦ በመምጣቱ፣ ‘ጋኔን አለበት’ ይሉታልና።

19. የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፤ እነርሱም፣ ‘በልቶ የማይጠግብ፣ ጠጪ እንዲሁም የቀረጥ ሰብሳቢዎችና የኀጢአተኞች ወዳጅ’ አሉት። ጥበብ ግን በሥራዋ ጸደቀች።”

ንስሓ ስላልገቡ ከተሞች የተነገረ ወዮታ

20. ከዚያም ኢየሱስ ብዙውን ታምራት ያደረገባቸው ከተሞች ንስሓ ባለመግባታቸው እንዲህ ሲል ወቀሳቸው፤

21. “ወዮልሽ ኮራዚን፤ ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ፤ በእናንተ የተደረገው ታምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን ኖሮ፣ ገና ዱሮ ማቅ ለብሰው፣ ዐመድ ነስንሰው ንስሓ በገቡ ነበር።

22. ስለዚህ እላችኋለሁ፤ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ቅጣቱ ይቀልላቸዋል።

23. አንቺም ቅፍርናሆም ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ ማለት ፈለግሽ? ነገር ግን ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ፤ በአንቺ የተደረገው ታምራት በሰዶም ቢደረግ ኖሮ፣ እስከ ዛሬ በቆየች ነበር።

24. ስለዚህ እልሻለሁ፤ በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ ቅጣቱ ለሰዶም ይቀልላታል።”

ክርስቶስ የሚሰጠው ዕረፍት

25. በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፤ ይህን ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ፤

26. አዎን አባት ሆይ፤ ይህ በፊትህ በጎ ፈቃድህ ሆኖ ተገኝቶአልና።

27. “ሁሉ ነገር ከአባቴ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ ሌላ ወልድን የሚያውቅ የለም፤ ከወልድና ወልድ ራሱ ፈቅዶ ከሚገልጥላቸው ሌላ አብን የሚያውቅ የለም።

28. “እናንት ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ።

29. ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤

30. ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀላል ነውና።”