ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት መላክ

1. ኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ወደ እርሱ ጠርቶ ርኵሳን መናፍስትን እንዲያወጡ፣ ደዌንና ሕማምን ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣንን ሰጣቸው።

2. የዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ስም የሚከተለው ነው፦ መጀመሪያ ጴጥሮስ የተባለው ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ፣ የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብና ወንድሙ ዮሐንስ፣

3. ፊልጶስና በርተሎሜዎስ፣ ቶማስና ቀረጥ ሰብሳቢው ማቴዎስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብና ታዴዎስ የተባለው ልብድዮስ፣

4. ቀነናዊው ስምዖንና በኋላ ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠው አስቆሮቱ ይሁዳ።

5. እነዚህን ዐሥራ ሁለቱን ኢየሱስ እንዲህ ከሚል ትእዛዝ ጋር ላካቸው፤ “ወደ አሕዛብ አትሂዱ፤ ወደ ሳምራውያንም ከተማ አትግቡ።

6. ይልቁንስ የእስራኤል ቤት ወደሆኑት ወደ ጠፉት በጎች ሂዱ።

7. ሄዳችሁም፣ ‘መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች’ ብላችሁ ስበኩ።

8. በሽተኞችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አስወጡ፤ በነጻ የተቀበላችሁትንም በነጻ ስጡ።

9. በመቀነታችሁ ወርቅም ሆነ ብር ወይም መዳብ አትያዙ።

10. ለመንገዳችሁም ከረጢት፣ ትርፍ እጀ ጠባብ ወይም ጫማ ወይም በትር አትያዙ፤ ለሠራተኛ የዕለት ጕርሱ ይገባዋልና።

11. “ወደ አንድ ከተማ ወይም መንደር ስትገቡ ሊቀበላችሁ ፈቃደኛ የሆነ ሰው ፈልጋችሁ በቤቱ ዕረፉ፤ እስክትወጡም ድረስ በዚያው ቈዩ።

12. ወደ ማንኛውም ሰው ቤት ስትገቡ ሰላምታ አቅርቡ።

13. ቤቱም የሚገባው ሆኖ ከተገኘ፣ ሰላማችሁ ይድረሰው፤ የማይገባው ከሆነ ግን ሰላማችሁ ወደ እናንተ ይመለስላችሁ።

14. ማንም ሰው ሊያስተናግዳችሁ ወይም የምትናገሩትን ሊሰማ ፈቃደኛ ካልሆነ፣ ከቤቱ ወይም ከከተማው ስትወጡ የእግራችሁን ትቢያ አራግፋችሁ ውጡ።

15. እውነት እላችኋለሁ፤ በፍርድ ቀን በዚያች ከተማ ከሚደርሰው ቅጣት ይልቅ በሰዶምና በገሞራ የሚደርሰው ይቀላል።

16. “እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ ስለዚህ እንደ እባብ ብልኆች እንደ ርግብ የዋሃን ሁኑ።

17. “ሰዎች ይዘው ለፍርድ ወደ ሸንጎ ያቀርቧችኋል፤ በምኵራ ቦቻቸውም ይገርፏችኋል፤ ስለዚህ ከእነርሱ ተጠንቀቁ።

18. በእኔ ምክንያት ወደ ገዦችና ወደ ነገሥታት ትወሰዳላችሁ፤ በእነርሱና በአሕዛብም ፊት ምስክር ትሆናላችሁ።

19. በምትያዙበትም ጊዜ ምን እንናገራለን፣ ምንስ እንመልሳለን ብላችሁ አትጨነቁ፤ በዚያን ጊዜ የምትናገሩት ይሰጣችኋል፤

20. በእናንተ የሚናገረው የሰማዩ አባታችሁ መንፈስ እንጂ እናንተ አይደላችሁምና።

21. “ወንድም ወንድሙን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ አባትም ልጁን፤ ልጆች በወላጆቻቸው ላይ ያምፃሉ፤ ያስገድሏቸዋልም።

22. ስለ ስሜ ሰዎች ሁሉ ይጠሏችኋል፤ ነገር ግን እስከ መጨረሻ የሚጸና እርሱ ይድናል።

23. በአንድ ስፍራ ሲያሳድዷችሁ ወደ ሌላ ሽሹ፤ እውነት እላችኋለሁ፣ የእስራኤልን ከተሞች ሳታዳርሱ የሰው ልጅ ይመጣል።

24. “ደቀ መዝሙር ከመምህሩ፣ ሎሌም ከጌታው አይበልጥም፤

25. ደቀ መዝሙር መምህሩን፣ ሎሌም ጌታውን ከመሰለ ይበቃዋል። ባለቤቱን ‘ብዔልዜቡል’ ካሉት ቤተ ሰዎቹንማ እንዴት አብልጠው አይሏቸውም!

26. “ስለዚህ አትፍሯቸው፤ የተሸፈነ መገለጡ፣ የተደበቀ መውጣቱ አይቀርምና።

27. በጨለማ የምነግራችሁን በብርሃን አውሩት፤ በጆሮአችሁ የሰማችሁትን በአደባባይ አውጁት፤

28. ሥጋን መግደል እንጂ ነፍስን መግደል የማይችሉትን አትፍሩ፤ ይልቁንስ ነፍስንና ሥጋን በገሃነም ማጥፋት የሚቻለውን ፍሩ።

29. በአንድ ሳንቲም ከሚሸጡት ሁለት ድንቢጦች አንዲቷ እንኳ ያለ አባታችሁ ፈቃድ ምድር ላይ አትወድቅም።

30. የራስ ጠጕራችሁ እንኳ አንድ ሳይቀር የተቈጠረ ነው።

31. ስለዚህ አትፍሩ፤ ከብዙ ድንቢጦች ይልቅ ዋጋችሁ የከበረ ነው።

32. “በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ፣ እኔም በሰማይ ባለው አባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤

33. ነገር ግን በሰው ፊት የሚክደኝን፣ እኔም በሰማይ ባለው አባቴ ፊት እክደዋለሁ።

34. “እኔ የመጣሁት ሰላምን በምድር ለማስፈን አይምሰላችሁ፤ ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማውረድ አልመጣሁም።

35. እኔ የመጣሁት “ ‘ልጅን ከአባት፣ ሴት ልጅን ከእናቷ ምራትንም ከዐማቷ ለመለያየት ነው፤

36. የሰው ጠላቶቹ፣ የገዛ ቤተ ሰዎቹ ይሆናሉ።’

37. “ከእኔ ይልቅ እናቱን ወይም አባቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባም፤ ከእኔ ይልቅ ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባም።

38. መስቀሉን ተሸክሞ የማይከተለኝ የእኔ ሊሆን አይገባውም።

39. ሕይወቱን ሊያድን የሚፈልግ ያጠፋታል፤ ሕይወቱን ስለ እኔ አሳልፎ የሚሰጥ ግን ያገኛታል።

40. “እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።

41. ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ያገኛል፤ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቅን ዋጋ ያገኛል።

42. ስለዚህ እውነት እላችኋለሁ፣ ማንም ሰው ከእነዚህ ከታናናሾች ለአንዱ ደቀ መዝሙሬ በመሆኑ አንድ ጽዋ ቀዝቃዛ ውሃ ቢሰጠው ዋጋውን አያጣም።”