ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው?

1. በዚያ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “በመንግሥተ ሰማይ ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው?” ብለው ጠየቁት።

2. ኢየሱስ አንድ ሕፃን ጠርቶ በመካከላቸው አቆመና እንዲህ አላቸው፤

3. “እውነት እላችኋለሁ፣ ካልተለወጣችሁ እንደ ሕፃናት ካልሆናችሁ ፈጽሞ ወደ መንግሥተ ሰማይ አትገቡም።

4. ስለዚህ በመንግሥተ ሰማይ ከሁሉ የሚበልጥ እንደዚህ ሕፃን ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ነው።

5. “እንደዚህ ያለውንም ሕፃን በስሜ የሚቀበል እኔን ይቀበላል።

6. ነገር ግን በእኔ ከሚያምኑት ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሰው፣ ከባድ የወፍጮ ድንጋይ በዐንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር ተጥሎ ቢሰጥም ይሻለዋል።

7. ይህች ዓለም የመሰናክል ምክንያት በመሆኗ ወዮላት! መሰናክል መምጣቱ አይቀርምና፤ ነገር ግን የመሰናክሉ ምክንያት ለሚሆነው ሰው ወዮለት።

8. እጅህ ወይም እግርህ ለመሰናክል ምክንያት ቢሆንብህ፣ ቈርጠህ ጣለው፤ ሁለት እጅ ወይም ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ዘለዓለም እሳት ከምትጣል፣ አንካሳ ወይም ሽባ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል።

9. እንዲሁም ዐይንህ ለመሰናክል ምክንያት ቢሆንብህ፣ አውጥተህ ጣለው፤ ሁለት ዐይን ኖሮህ ወደ ገሃነመ እሳት ከምትጣል፣ አንድ ዐይን ኖሮህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል።

የጠፋው በግ ምሳሌ

10. “ከእነዚህ ከታናናሾች መካከል አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ እላችኋለሁና፤ በሰማይ ያሉት መላእክታቸው በሰማይ ያለውን የአባቴን ፊት ሁል ጊዜ ያያሉ፤

11. የሰው ልጅ የጠፉትን ለማዳን መጥቶአልና።

12. “እስቲ ንገሩኝ፤ አንድ ሰው መቶ በጎች ቢኖሩትና ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋበት ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ላይ ትቶ የጠፋውን ለመፈለግ አይሄድምን?

13. እውነት እላችኋለሁ፣ የጠፋውን በግ ሲያገኝ፣ ካልጠፉት ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ በዚያ በተገኘው ደስ ይለዋል።

14. እንደዚሁም ከእነዚህ ከታናናሾቹ መካከል አንዱ እንኳ እንዲጠፋ በሰማያት ያለው አባታችሁ ፈቃድ አይደለም።

ስለ መቀያየም

15. “ወንድምህ ቢበድልህ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻ ሆናችሁ ጥፋቱን ንገረው። ቢሰማህ፣ ወንድምህን እንደ ገና የራስህ ታደርገዋለህ።

16. ባይሰማህ ግን ቃል ሁሉ በሁለት ወይም በሦስት ምስክሮች ፊት ስለሚጸና፣ አንድ ወይም ሁለት ሰው ይዘህ አነጋግረው።

17. እነርሱን ባይሰማ ለቤተ ክርስቲያን ንገር፤ ቤተ ክርስቲያንንም ባይሰማ እንደ አሕዛብና እንደ ቀረጥ ሰብሳቢ ቊጠረው።

18. “እውነት እላችኋለሁ፤ በምድር ያሰራችሁት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድርም የፈታችሁት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል።

19. “ደግሞም እውነት እላችኋለሁ፤ በምድር ላይ ሁለት ሆናችሁ ስለ ምንም ነገር በመስማማት ብትጠይቁ በሰማይ ያለው አባቴ ያደርግላችኋል፤

20. ሁለት ወይም ሦስት ሆነው በስሜ በሚሰበሰቡበት መካከል በዚያ እገኛለሁና።”

ይቅርታ ስለ ማድረግ

21. በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፣ “ጌታ ሆይ፤ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው? እስከ ሰባት ጊዜ ነውን?” አለው።

22. ኢየሱስም “እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ ብቻ አልልህም” አለው።

23. “ስለዚህ መንግሥተ ሰማይ፣ በአገልጋዮቹ እጅ የነበረውን ሂሳብ ለመተሳሰብ የፈለገን ንጉሥ ትመስላለች።

24. ሂሳቡን ማጣራት እንደ ጀመረም ዐሥር ሺህ ታላንት ዕዳ ያለበትን አንድ አገልጋይ አቀረቡለት።

25. አገልጋዩም ያለበትን ዕዳ መክፈል ስላቃተው እርሱ ራሱ፣ ሚስቱ፣ ልጆቹና ንብረቱ ሁሉ ተሽጠው ዕዳው እንዲከፈል ጌታው አዘዘ።

26. “በዚህ ጊዜ አገልጋዩ እግሩ ላይ ወድቆ፣ ‘ታገሰኝ፣ ያለብኝን ዕዳ ሁሉ እከፍልሃለሁ’ ሲል ለመነው።

27. ጌታውም አዘነለትና ማረው፤ ዕዳውንም ትቶለት አሰናበተው።

28. “ያ አገልጋይ ከጌታው ፊት እንደ ወጣ አንድ መቶ ዲናር የእርሱ ዕዳ ያለበትን አገልጋይ ባልንጀራውን አግኝቶ እንቅ አድርጎ በመያዝ፣ ‘ያለብህን ዕዳ ክፈለኝ!’ አለው።

29. “ባልንጀራው አገልጋይም ከፊቱ ወድቆ፣ ‘ታገሠኝ እከፍልሃለሁ’ ብሎ ለመነው።

30. “ነገር ግን ሊታገሠው ፈቃደኛ ስላልነበረ፣ ያለበትን ዕዳ እስኪከፍለው ድረስ ወህኒ ቤት አስገባው።

31. የሆነውን ነገር ያዩ ሌሎች አገልጋዮችም በጣም አዘኑ፤ ሄደውም ሁኔታውን በሙሉ ለጌታቸው ነገሩት።

32. “በዚህ ጊዜ ጌታው አገልጋዩን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ ‘አንተ ክፉ አገልጋይ፤ ስለ ለመንኸኝ ያን ሁሉ ዕዳ ተውሁልህ፤

33. እኔ እንደ ማርሁህ አንተም ባልንጀራህን ልትምረው አይገባህም ነበርን?’

34. በቍጣም ያለበትን ዕዳ ከፍሎ እስኪጨርስ ድረስ ለአሳሪዎች አሳልፎ ሰጠው።

35. “ስለዚህ እያንዳንዳችሁ ወንድሞቻችሁን ከልባችሁ ይቅር ካላላችሁ፣ የሰማዩ አባቴም እንደዚሁ ያደርግባችኋል።”