ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ይሁዳ ራሱን ሰቀለ

1. ጠዋት በማለዳ ላይ፣ የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች ሁሉ ኢየሱስ ስለሚገደልበት ሁኔታ ተመካከሩ፤

2. ካሰሩትም በኋላ ወስደው ለገዥው ለጲላጦስ አሳልፈው ሰጡት።

3. አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም ኢየሱስ እንደ ተፈረደበት ባየ ጊዜ ተጸጸተ፤ የወሰደውን ሠላሳ ጥሬ ብር ለካህናት አለቆችና ለሕዝቡ ሽማግሌዎች መልሶ በመስጠት፣

4. “ንጹሕ ሰው አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ” አለ።እነርሱም፣ “ታዲያ እኛ ምን አገባን፤ የራስህ ጕዳይ ነው!” አሉት።

5. ስለዚህ ይሁዳ ብሩን በቤተ መቅደስ ውስጥ ወርውሮ ወጣ፤ ሄዶም ራሱን ሰቅሎ ሞተ።

6. የካህናት አለቆች ብሩን አንሥተው፣ “የደም ዋጋ ስለ ሆነ ወደ መባ ልንጨምረው አይፈቀድም” አሉ፤

7. ተመካክረውም ለእንግዶች የመቃብር ስፍራ እንዲሆን በገንዘቡ የሸክላ ሠሪውን ቦታ ገዙበት።

8. ስለዚህም ያ ቦታ እስከ ዛሬ ድረስ “የደም መሬት” ተብሎ ይጠራል።

9. በዚህም በነቢዩ ኤርምያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ተፈጸመ፤ “ለእርሱ ዋጋ ይሆን ዘንድ የእስራኤል ልጆች የገመቱትን ሠላሳ ጥሬ ብር ተቀበሉ፤

10. እግዚአብሔርም ባዘዘኝ መሠረት ለሸክላ ሠሪው ቦታ ከፈሉ።”

ኢየሱስ በጲላጦስ ፊት

11. በዚህ ጊዜ ኢየሱስ አገረ ገዥው ፊት ቀረበ፤ አገረ ገዥውም፣ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” በማለት ጠየቀው።ኢየሱስም፣ “አንተው እንዳልኸው ነው” ሲል መለሰለት።

12. የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች ሲከሱት ግን ምንም መልስ አልሰጠም።

13. በዚህ ጊዜ ጲላጦስ፣ “ስንት ነገር አቅርበው እንደሚከሱህ አትሰማምን?” አለው።

14. እርሱ ግን አገረ ገዥው እስኪገረም ድረስ ለቀረበበት ክስ አንዲት ቃል እንኳ አልመለሰም።

15. አገረ ገዥው ሕዝቡ በበዓሉ እንዲፈታላቸው የሚጠይቁትን አንድ እስረኛ የመፍታት ልማድ ነበረው።

16. በዚያን ጊዜ በዐመፅ የታወቀ በርባን የሚባል እስረኛ ነበር።

17. ሕዝቡ እንደተሰበሰቡ ጲላጦስ፣ “ከበርባንና ክርስቶስ ከሚባለው ከኢየሱስ፣ ማንን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው፤

18. ጲላጦስም በቅናት አሳልፈው እንደሰጡት ያውቅ ነበርና።

19. በፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጦ ሳለ ሚስቱ፣ “በእርሱ ምክንያት ዛሬ በሕልም ብዙ ስለተሠቃየሁ፣ በዚያ ንጹሕ ሰው ላይ ምንም ነገር እንዳታደርግ” የሚል መልእክት ላከችበት።

20. ነገር ግን የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች በርባን እንዲፈታላቸው ኢየሱስ ግን እንዲገደል ይለምኑ ዘንድ ሕዝቡን ያግባቡ ነበር።

21. አገረ ገዥውም፣ “ከሁለቱ ማንን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” በማለት ጠየቀ።እነርሱም፤ “በርባንን!” በማለት መለሱ።

22. ጲላጦስም፣ “ታዲያ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስንስ ምን ላድርገው?” አላቸው።ሁሉም፣ “ይሰቀል!” አሉ።

23. ጲላጦስም፣ “ለምን? ምን ክፉ ነገር አድርጎአል?” በማለት ጠየቃቸው።እነርሱ ግን አብዝተው እየጮኹ፣ “ይሰቀል!” አሉ።

24. ጲላጦስ ሁኔታው ሽብር ከማስነሣት በስተቀር ምንም ፋይዳ የሌለው መሆኑን ተመልክቶ፣ “እኔ ከዚህ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ፤ ከእንግዲህ ኀላፊነቱ የራሳችሁ ነው” በማለት ውሃ አስመጥቶ በሕዝቡ ፊት እጆቹን ታጠበ።

25. ሕዝቡም በሙሉ፣ “ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን!” ብለው መለሱ።

26. በዚህ ጊዜ በርባንን ፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን ካስገረፈው በኋላ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው።

ኢየሱስ በሮማውያን ወታደሮች እጅ

27. ከዚያም የአገረ ገዥው ወታደሮች ኢየሱስን ወደ ገዥው ግቢ ወሰዱት፤ ሰራዊቱንም ሁሉ በዙሪያው አሰባሰቡ።

28. ልብሱን ገፈው ቀይ ልብስ አጠለቁለት፤

29. እሾኽ ጐንጕነው አክሊል በመሥራት ራሱ ላይ ደፉበት፤ የሸምበቆ በትር በቀኝ እጁ በማስያዝ በፊቱ ተንበርክከው፣ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን” በማለት አሾፉበት፤

30. ተፉበትም፤ የሸምበቆ በትሩን ከእጁ ወስደው ራሱ ላይ በሸምበቆው ደግመው ደጋግመው መቱት፤

31. ካሾፉበት በኋላም ቀዩን ልብስ ገፈው የራሱን መጐናጸፊያ አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ይዘውት ሄዱ።

የኢየሱስ መሰቀል

32. ይዘውትም ሲሄዱ ስምዖን ተብሎ የሚጠራ የቀሬና ሰው አገኙ፤ መስቀሉንም እንዲሸከም አስገደዱት።

33. ትርጕሙ፣ “የራስ ቅል ስፍራ” ከሆነው ጎልጎታ ከተባለው ቦታ ሲደርሱ፣

34. ከሐሞት ጋር የተቀላቀለ የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ሰጡት፤ እርሱ ግን ቀምሶ ሊጠጣው አልፈቀደም።

35. ከሰቀሉትም በኋላ ዕጣ ጥለው ልብሱን ተካፈሉ፤

36. በዚያም ተቀምጠው ይጠብቁት ነበር። ከራስጌውም፣

37. “ይህ የአይሁድ ንጉሥ ኢየሱስ ነው” የሚል የክስ ጽሑፍ አኖሩ።

38. ሁለት ወንበዴዎች አንዱ በቀኙ፣ አንዱ በግራው አብረውት ተሰቅለው ነበር።

39. መንገድ ዐላፊዎችም በኀይል እየተሳደቡና ራሳቸውን እየነቀነቁ፣

40. “ቤተ መቅደስን አፍርሰህ በሦስት ቀን ውስጥ የምትሠራው፤ እስቲ ራስህን አድን! የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ በል ከመስቀል ውረድ!” ይሉት ነበር።

41. የካህናት አለቆችም ከኦሪት ሕግ መምህራንና ከሽማግሌዎች ጋር ሆነው እያሾፉበት እንዲህ ይሉ ነበር፤

42. “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ማዳን አይችልም! የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ አሁን ከመስቀል ይውረድ፤ እኛም እናምንበታለን።

43. በእግዚአብሔር ታምኖአል፤ ‘የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ’ ይል ስለ ነበር እስቲ ከወደደው አሁን ያድነው!”

44. ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዴዎችም እንደዚሁ የስድብ ናዳ ያወርዱበት ነበር።

የኢየሱስ መሞት

45. ከቀኑ ስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ።

46. በዘጠኝ ሰዓት ገደማ፣ ኢየሱስ ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “ኤሎሄ! ኤሎሄ! ላማ ሰበቅታኒ?” እያለ ጮኸ፤ ትርጕሙም “አምላኬ፤ አምላኬ፤ ለምን ተውኸኝ?” ማለት ነው።

47. በዚያ ቆመው ከነበሩት አንዳንዶቹ ጩኸቱን ሲሰሙ፣ “ኤልያስን እየተጣራ ነው!” አሉ።

48. ወዲያውም ከእነርሱ አንዱ ሮጦ ሰፍነግ በመውሰድ የኮመጠጠ ወይን ጠጅ ውስጥ ነከረው፤ ሰፍነጉንም በሸምበቆ ዘንግ ጫፍ ላይ በማድረግ እንዲጠጣው ለኢየሱስ አቀረበለት።

49. የቀሩት ግን፣ “ተዉት፤ እስቲ ኤልያስ መጥቶ ሲያድነው እናያለን!” አሉ።

50. ኢየሱስ እንደ ገና ከፍ ባለ ድምፅ ጮኸ፤ መንፈሱንም አሳልፎ ሰጠ።

51. በዚያን ጊዜ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ለሁለት ተቀደደ፤ ምድር ተናወጠች፤ ዐለቶችም ተሰነጣጠቁ፤

52. መቃብሮች ተከፈቱ፤ አንቀላፍተው የነበሩትም ብዙዎች ቅዱሳን ተነሡ፤

53. ከመቃብርም በመውጣት ከኢየሱስ ትንሣኤ በኋላ ወደ ቅድስት ከተማ ገብተው ለብዙዎች ታዩ።

54. የመቶ አለቃውና አብረውት ኢየሱስን ይጠብቁት የነበሩት የመሬት መናወጡንና የሆነውን ነገር ሁሉ ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተው፤ ይህስ፣ “በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበር!” አሉ።

55. ከገሊላ የመጡና ኢየሱስን በሚያስፈልገው ነገር ለማገልገል የተከተሉት ብዙ ሴቶች ሁኔታውን ከርቀት እየተመለከቱ በአካባቢው ነበሩ።

56. ከእነርሱም መካከል ማርያም መግደላዊት፣ ማርያም የያዕቆብና የዮሴፍ እናት እንዲሁም የዘብዴዎስ ልጆች እናት ነበሩ።

የኢየሱስ መቀበር

57. ምሽት ላይ ዮሴፍ የሚባል ሀብታም ሰው ከአርማትያስ መጣ፤ እርሱ ራሱም የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበረ።

58. ጲላጦስ ፊት ቀርቦ የኢየሱስን በድን ለመነው፤ ጲላጦስም እንዲሰጠው አዘዘ።

59. ዮሴፍም በድኑን ወስዶ በንጹሕ የበፍታ ጨርቅ ከፈነው፤

60. ለራሱ ከዐለት አስፈልፍሎ ባዘጋጀው መቃብር ውስጥ አኖረው፤ ከዚያም ትልቅ ድንጋይ አንከባሎ የመቃብሩን በር ዘግቶ ሄደ።

61. በዚህ ጊዜ ማርያም መግደላዊትና ሌላዋ ማርያም ከመቃብሩ ትይዩ ተቀምጠው ነበር።

የመቃብሩ ጥበቃ

62. በማግሥቱ፣ ከሰንበት ዝግጅት በኋላ ባለው ቀን፣ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ጲላጦስ ፊት ቀርበው እንዲህ አሉት፤

63. “ክቡር ሆይ፤ ያ አሳች በሕይወት ሳለ፣ ‘ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ’ ያለው ትዝ ብሎናል፤

64. ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ አስከሬኑን ሰርቀው ለሕዝቡ፣ ‘ከሙታን ተነሥቶአል’ ብለው እንዳያስወሩ መቃብሩ እስከ ሦስተኛው ቀን ድረስ እንዲጠበቅ ትእዛዝ ስጥልን፤ አለዚያ የኋለኛው ስሕተት ከፊተኛው የባሰ ይሆናል!”

65. ጲላጦስም፣ “ጠባቂዎች አሏችሁ፤ ሄዳችሁ በምታውቁት መንገድ አስጠብቁ” አላቸው።

66. እነርሱም ሄደው መቃብሩን በማኅተም አሽገው ጠባቂ አቆሙበት።