ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 4 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የኢየሱስ መፈተን

1. ከዚህ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስን በዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው።

2. አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ ተራበ።

3. ፈታኙም ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፣ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ እነዚህን ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ እዘዝ” አለው።

4. ኢየሱስም፣ “ ‘ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፎአል” ሲል መለሰለት።

5. ቀጥሎም ዲያብሎስ ኢየሱስን ወደ ቅድስት ከተማ በመውሰድ ከቤተ መቅደሱም ዐናት ላይ አውጥቶ፣

6. “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ ራስህን ወደ መሬት ወርውር፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና፤“ ‘እግርህ በድንጋይ እንዳይሰናከል፣በእጃቸው ያነሡህ ዘንድ፣መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል።’ ”

7. ኢየሱስም፣ “እንደዚሁም በመጻሕፍት፣ ‘እግዚአብሔር አምላክህን አትፈታተነው’ ተብሎ ተጽፎአል” በማለት መለሰለት።

8. እንደ ገናም ዲያብሎስ ኢየሱስን እጅግ ከፍ ወዳለ ተራራ አወጣው፤ የዓለምንም መንግሥታት ከነክብራቸው አሳየውና፣

9. “ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” አለው።

10. ኢየሱስም፣ “አንተ ሰይጣን ከፊቴ ራቅ! ‘ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ’ ተብሎ ተጽፎአልና” አለው።

11. ከዚያም ዲያብሎስ ትቶት ሄደ፤ መላእክትም መጥተው አገለገሉት።

ኢየሱስ ስብከት መጀመሩ

12. ኢየሱስ የዮሐንስን መታሰር በሰማ ጊዜ ወደ ገሊላ ተመለሰ።

13. የናዝሬትንም ከተማ ትቶ፣ በዛብሎንና በንፍታሌም አካባቢ በባሕሩ አጠገብ በምትገኘው በቅፍርናሆም ከተማ መኖር ጀመረ።

14. በዚህም በነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ፤

15. “የዛብሎን ምድር፣ የንፍታሌም ምድር፣ከዮርዳኖስ ማዶ በባሕር መንገድ አጠገብ፣ያለው የአሕዛብ ገሊላ፣

16. በጨለማ የሚኖር ሕዝብ፣ታላቅ ብርሃን አየ፤በሞት ጥላ ምድር ላለው፣ብርሃን ወጣለት።”

17. ከዚያ ጊዜ አንሥቶ ኢየሱስ፣ “ንስሓ ግቡ፤ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና” እያለ መስበክ ጀመረ።

የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት መጠራት

18. ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲያልፍ፣ ሁለት ወንድማማቾች ማለትም ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንንና ወንድሙን እንድርያስን አያቸው። ዓሣ አጥማጆች ነበሩና መረባቸውን ወደ ባሕሩ ይጥሉ ነበር።

19. ኢየሱስም፣ “ኑ፣ ተከተሉኝ፤ ሰዎችን አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” አላቸው።

20. ወዲያው መረባቸውን ትተው ተከተሉት።

21. አለፍ እንዳለም፣ ሌሎች ሁለት ወንድማማቾች፣ የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን አየ። ከአባታቸው ከዘብዴዎስ ጋር በጀልባ ውስጥ መረባቸውን ያበጁ ነበር። ኢየሱስም ጠራቸው፤

22. ወዲያውኑ ጀልባቸውንም ሆነ አባታቸውን ትተው ተከተሉት።

የበሽተኞች መፈወስ

23. ኢየሱስም በምኵራቦቻቸው እያስተማረ፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ቃል እየሰበከ፣ በሕዝቡ መካከል ማንኛውንም ደዌና ሕመም እየፈወሰ በመላው ገሊላ ይዘዋወር ነበር።

24. ከዚህም የተነሣ ዝናው በመላዋ ሶርያ ተሰማ፤ ሕዝቡም በተለያዩ በሽታዎች የታመሙትን፣ በክፉ ደዌ የሚሠቃዩትን፣ አጋንንት ያደሩባቸውን፣ የሚጥል በሽታ ያለባቸውን፣ ሽባዎችን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤ ፈወሳቸውም።

25. ከዚህም የተነሣ ከገሊላ፣ ከ “ዐሥሩ ከተሞች”፣ ከኢየሩሳሌም፣ ከይሁዳና ከዮርዳኖስ ማዶ የመጡ ብዙ ሰዎች ተከተሉት።