ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ጳውሎስም ወደ ሸንጎው ትኵር ብሎ በመመልከት፣ “ወንድሞች ሆይ፤ እኔ እስከዚች ቀን ድረስ በእግዚአብሔር ፊት በንጹሕ ሕሊና ተመላልሻለሁ” አለ።

2. በዚህ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ በጳውሎስ አጠገብ የቆሙትን ሰዎች አፉን እንዲመቱት አዘዘ።

3. ጳውሎስም፣ “አንተ በኖራ የተለሰንህ ግድግዳ! እግዚአብሔር ደግሞ አንተን ይመታሃል፤ በሕጉ መሠረት ልትፈርድብኝ ተቀምጠህ ሳለህ፣ ያለ ሕግ ስላ ስመታኸኝ አንተ ራስህ ሕጉን ጥሰሃል” አለው።

4. ጳውሎስ አጠገብ ቆመው የነበሩትም፣ “የእግዚአብሔርን ሊቀ ካህናት ደፍረህ ትሰድባለህን?” አሉት።

5. ጳውሎስም፣ “ወንድሞች ሆይ፤ ሊቀ ካህናት መሆኑን ባለማወቄ ነው፤ ‘በሕዝብህ አለቃ ላይ ክፉ አትናገር’ ተብሎ ተጽፎአልና” አላቸው።

6. ጳውሎስም ሕዝቡ፣ ከፊሎቹ ሰዱቃውያን፣ ከፊሎቹ ፈሪሳውያን መሆናቸውን ስላወቀ፣ “ወንድሞቼ ሆይ፤ እኔ ከፈሪሳዊ የተወለድሁ ፈሪሳዊ ነኝ፣ ለፍርድ የቀረብሁትም የሙታንን ትንሣኤ ተስፋ በማድረጌ ነው” ሲል በሸንጎው ፊት ጮኸ።

7. ይህንንም በተናገረ ጊዜ፣ በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን መካከል ጠብ ተነሣ፤ ሸንጎውም ለሁለት ተከፈለ።

8. ሰዱቃውያን የሙታን ትንሣኤ የለም፤ መላእክትም መናፍስትም የሉም የሚሉ ሲሆኑ፣ ፈሪሳውያን ግን በእነዚህ ሁሉ መኖር የሚያምኑ ነበሩ።

9. ታላቅ ሁከትም ሆነ፤ ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ አንዳንድ የኦሪት ሕግ መምህራንም ተነሥተው፣ “በዚህ ሰው ላይ ምንም ጥፋት አላገኘንበትም፤ መንፈስ ወይም መልአክ ተናግሮትስ እንደሆነ ምን ይታወቃል?” በማለት አጥብቀው ተከራከሩ።

10. ጠቡ ከማየሉ የተነሣም አዛዡ ጳውሎስን እንዳይገነጣጥሉት ፈራ፤ ስለዚህ ወታደሮቹ ወርደው ከመካከላቸው ነጥቀው ወደ ጦሩ ሰፈር እንዲያስገቡት አዘዘ።

11. በሚቀጥለውም ሌሊት ጌታ በአጠገቡ ቆሞ፣ “ጳውሎስ ሆይ፤ አይዞህ! በኢየሩሳሌም እንደ መሰከርህልኝ፣ በሮምም ደግሞ ልትመሰክርልኝ ይገባሃል” አለው።

ጳውሎስን ለመግደል የተደረገ ሤራ

12. በነጋም ጊዜ፣ አይሁድ ተሰብስበው በማሤር ጳውሎስን እስኪገድሉ ድረስ እህል ውሃ ላለመቅመስ ተማማሉ። በዚህ ሤራ

13. የተማማሉትም ከአርባ በላይ ነበሩ።

14. እነርሱም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ሽማግሌዎች ሄደው እንዲህ አሉ፤ “ጳውሎስን ሳንገድል እህል ላለመቅመስ ጽኑ መሐላ አድርገናል።

15. እንግዲህ እናንተ ከሸንጎው ጋር ሆናችሁ፣ ስለ ጒዳዩ ትክክለኛ የሆነ ተጨማሪ መረጃ ከእርሱ እንደምትፈልጉ አስመስላችሁ ጳውሎስን ወደ እናንተ እንዲሰደው የጦር አዛዡን ለምኑት፤ እኛም ገና ወደዚህ ሳይደርስ ልንገድለው ዝግጁ ነን።”

16. ነገር ግን የጳውሎስ የእኅት ልጅ ስለ ሤራው በመስማቱ፣ ወደ ጦሩ ሰፈር ገብቶ ሁኔታውን ለጳውሎስ ነገረው።

17. ጳውሎስም ከመቶ አለቆቹ አንዱን ጠርቶ፣ “ይህ ልጅ ለጦር አዛዡ የሚነግረው ነገር ስላለ ወደ እርሱ ውሰደው” አለው።

18. እርሱም ወደ ጦር አዛዡ ወሰደው።የመቶ አለቃውም፣ “እስረኛው ጳውሎስ ጠርቶኝ፣ ይህ ጒልማሳ የሚነግርህ ነገር ስላለው ወደ አንተ እንዳቀርበው ለመነኝ” አለው።

19. አዛዡም የጒልማሳውን እጅ ይዞ ለብቻው ገለል በማድረግ፣ “ልትነግረኝ የምትፈልገው ምንድን ነው?” አለው።

20. ልጁም እንዲህ አለው፤ “አይሁድ ስለ እርሱ ትክክለኛ የሆነ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የፈለጉ በመምሰል፣ ጳውሎስን ነገ ሸንጎው ፊት እንድታቀርብላቸው ሊለምኑህ ተስማምተዋል።

21. ስለዚህ እሺ አትበላቸው፤ ምክንያቱም ከመካከላቸው ከአርባ በላይ የሚሆኑት ሊገድሉት አድፍጠው እየጠበቁት ነው፤ ደግሞም እስኪገድሉት ድረስ እህል ውሃ ላለመቅመስ ተማምለዋል፤ አሁንም ተዘጋጅተው የአንተን መልስ እየተጠባበቁ ነው።”

22. የጦር አዛዡም፣ “ይህን ለእኔ የገለጥህልኝን ነገር ለማንም እንዳትናገር” ብሎ ጒልማሳውን አስጠንቅቆ አሰናበተው።

ጳውሎስ ወደ ቂሳርያ ተላከ

23. ከዚያም ከመቶ አለቆቹ ሁለቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ከምሽቱ ሦስት ሰዓት፣ ወደ ቂሳርያ የሚሄዱ ሁለት መቶ ወታደሮች፣ ሰባ ፈረሰኞችና ሁለት መቶ ባለ ጦር ጭፍራ አዘጋጁ፤

24. ደግሞም ጳውሎስ ተቀምጦበት ወደ አገረ ገዡ ወደ ፊልክስ በደኅና የሚደርስበት ከብት ይዘጋጅ።”

25. ደብዳቤም ጻፈ፤ እንዲህ የሚል፦

26. ከቀላውዴዎስ ሉስዩስ፤ለክቡር አገረ ገዥ ለፊልክስ፤ሰላም ለአንተ ይሁን።

27. አይሁድ ይህን ሰው ይዘው ሊገድሉት ነበር፤ ነገር ግን የሮም ዜጋ መሆኑን ስላወቅሁ፣ ከወታደሮቼ ጋር ደርሼ አተረፍሁት።

28. ለምን ሊከሱት እንደ ፈለጉ ለማወቅም፣ ወደ ሸንጎአቸው አቀረብሁት።

29. የተከሰሰውም ሕጋቸውን በተመለከተ እንጂ ለሞት ወይም ለእስራት የሚያበቃ እንዳልሆነ ተረድቻለሁ።

30. አይሁድ ግን በዚህ ሰው ላይ ማሤራቸውን በተረዳሁ ጊዜ፣ ወዲያው ወደ አንተ ላክሁት፤ ከሳሾቹም ከእርሱ ጋር ያላቸውን ክርክር ለአንተ እንዲያቀርቡ አዘዝኋቸው።

31. ስለዚህ ወታደሮቹ በታዘዙት መሠረት፣ ጳውሎስን ይዘው በሌሊት እስከ አንቲጳጥሪስ ድረስ ወሰዱት።

32. በማግስቱ፣ ፈረሰኞቹ ብቻ እንዲያደርሱት አድርገው፣ ሌሎቹ ወደ ጦር ሰፈር ተመለሱ።

33. ፈረሰኞቹም ቂሳርያ በደረሱ ጊዜ፣ ደብዳቤውን ለአገረ ገዡው ሰጡት፤ ጳውሎስንም አስረከቡት።

34. አገረ ገዡም ደብዳቤውን ካነበበ በኋላ፣ ጳውሎስን ከየትኛው አውራጃ እንደ መጣ ጠየቀው፤ የኪልቅያ ሰው መሆኑን ባወቀ ጊዜ፣

35. “የአንተን ጒዳይ ከሳሾችህ ሲቀርቡ አያለሁ” አለው። ከዚያም ጳውሎስ በሄሮድስ ግቢ ውስጥ እንዲጠበቅ አዘዘ።