ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ጳውሎስ በኤፌሶን

1. አጵሎስ በቆሮንቶስ በነበረበት ጊዜ፣ ጳውሎስ በላይኛው አገር ዐልፎ ወደ ኤፌሶን መጣ፤ በዚያም አንዳንድ ደቀ መዛሙርትን አግኝቶ፣

2. “ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀበላችሁን?” አላቸው።እነርሱም፣ “አልተቀበልንም፤ እንዲያውም መንፈስ ቅዱስ መኖሩን እንኳ አልሰማንም” አሉት።

3. ጳውሎስም፣ “ታዲያ፣ በምን ተጠመቃችሁ?” አላቸው።እነርሱም፣ “የዮሐንስን ጥምቀት” አሉት።

4. ጳውሎስም፣ “የዮሐንስ ጥምቀትማ የንስሓ ጥምቀት ነበር፤ ዮሐንስም ራሱ ሰዎች ከእርሱ በኋላ በሚመጣው በኢየሱስ እንዲያምኑ ተናግሮአል” አላቸው።

5. እነርሱም ይህን በሰሙ ጊዜ በጌታ በኢየሱስ ስም ተጠመቁ።

6. ጳውሎስም እጁን በላያቸው በጫነ ጊዜ፣ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው፤ በሌሎች ቋንቋዎች ተናገሩ፤ ትንቢትም ተናገሩ።

7. ሰዎቹም በአጠቃላይ ዐሥራ ሁለት ያህል ነበሩ።

8. ጳውሎስም ወደ ምኵራብ እየገባ፣ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እየተነጋገረና እያሳመናቸው ሦስት ወር ሙሉ ምንም ሳይፈራ ፊት ለፊት ይናገር ነበር።

9. አንዳንዶቹ ግን ግትር በመሆን፣ ለማመን ፈቃደኞች አልነበሩም፤ የጌታንም መንገድ በገሃድ ያጥላሉ ነበር። ስለዚህ ጳውሎስ ትቶአቸው ሄደ፤ ደቀ መዛሙርትንም ለብቻቸው ወስዶ በጢራኖስ የትምህርት አዳራሽ ውስጥ በየዕለቱ ያነጋግራቸው ነበር።

10. ይህን ማድረጉንም ሁለት ዓመት ስለ ቀጠለ፣ በእስያ አውራጃ ይኖሩ የነበሩት የአይሁድና የግሪክ ሰዎች ሁሉ የጌታን ቃል ለመስማት ቻሉ።

11. እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ እጅግ የሚያስደንቅ ታምራትን ያደርግ ነበር፤

12. መሐረብ ወይም ሰውነቱን የነካ ጨርቅ እንኳ ወደ ሕመምተኞች ሲወስዱ በሽታቸው ይለቃቸው ነበር፤ ርኵሳን መናፍስትም ይወጡ ነበር።

13. እየዞሩ አጋንንትን ያስወጡ ከነበሩት አይሁድ አንዳንዶቹ፣ “ጳውሎስ በሚሰብከው በኢየሱስ ስም እንድትወጡ አዛችኋለሁ” እያሉ የጌታን የኢየሱስን ስም ርኵሳን መናፍስት በያዟቸው ሰዎች ላይ ለመጥራት ሞከሩ፤

14. የአይሁዳዊው የካህናቱ አለቃ የአስቄዋ ሰባት ወንዶች ልጆችም ይህንኑ ያደርጉ ነበር።

15. ርኩስ መንፈሱም፣ “ኢየሱስን ዐውቀዋለሁ፤ ጳውሎስንም ዐውቀዋለሁ፤ እናንተ ግን እነማን ናችሁ?” አላቸው።

16. ከዚያም ርኩስ መንፈስ ያደረበት ሰው ዘሎ ያዛቸው፤ በረታባቸውም፤ እጅግ ስላየለባቸውም ቤቱን ጥለው ዕራቁታቸውን ሸሹ።

17. ይህም በኤፌሶን በሚኖሩት፣ በአይሁድና በግሪክ ሰዎች ሁሉ ዘንድ በታወቀ ጊዜ፣ ሁሉም ፍርሀት ያዛቸው፤ በዚህም የጌታ የኢየሱስ ስም ተከበረ።

18. ካመኑትም ሰዎች ብዙዎቹ እየቀረቡ ክፉ ሥራቸውን በግልጥ ተናዘዙ፤

19. ሲጠነቁሉ ከነበሩትም መካከል ብዙዎች መጽሐፋቸውን ሰብስበው በማምጣት በሕዝብ ፊት አቃጠሉ፤ ዋጋቸውም ሲሰላ አምሳ ሺህ ብር ያህል ሆኖ ተገኘ።

20. በዚህ ሁኔታ የጌታ ቃል በኀይል እያደገና እያሸነፈ ሄደ።

21. ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ፣ ጳውሎስ በመቄዶንያና በአካይያ በኩል ዐልፎ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ በመንፈሱ ወስኖ፣ “እዚያ ከደረስሁ በኋላ ሮምን ደግሞ ማየት አለብኝ” አለ።

22. ከረዳቶቹም ሁለቱን፣ ጢሞቴዎስንና ኤርስጦንን፣ ወደ መቄዶንያ ልኮ እርሱ ራሱ ግን በእስያ አውራጃ ጥቂት ቀን ተቀመጠ።

በኤፌሶን የተነሣው ሁከት

23. በዚህ ጊዜ፣ ስለ ጌታ መንገድ ታላቅ ሁከት ተፈጠረ።

24. ድሜጥሮስ የተባለ አንድ የብር አንጥረኛ የአርጤምስን ቤተ መቅደስ ምስሎች ከብር ቀጥቅጦ እየሠራ ለሠራተኞቹ የሚያስገኘው ገቢ ቀላል አልነበረም።

25. እርሱም እነዚህን ሠራተኞችና በተመሳሳይ ሙያ የሚተዳደሩትን ሌሎቹን ሰዎች በአንድነት ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፤ “ሰዎች ሆይ፤ ይህ ሥራ ጥሩ ገቢ እንደሚያስገኝልን ታውቃላችሁ።

26. ይህ ጳውሎስ የተባለ ሰው በኤፌሶን ብቻ ሳይሆን፣ በመላው የእስያ አውራጃ የሚገኘውን በርካታ ሕዝብ እያሳመነ እንዳሳታቸው ይኸው የምታዩትና የምትሰሙት ነገር ነው፤ በሰው እጅ የተሠሩ አማልክት በፍጹም አማልክት እንዳልሆኑ ይናገራልና።

27. የዚህ የሥራችን መልካም ስም ከመጒደፉም በላይ፣ መላው እስያና ዓለም የሚያመልካት የታላቋ አርጤምስ ቤተ መቅደስም ዋጋ ቢስ ይሆናል፤ ደግሞም ገናናው ክብሯ ይዋረዳል።”

28. ሰዎቹም ይህን በሰሙ ጊዜ ክፉኛ ተቈጥተው፣ “የኤፌሶኗ አርጤምስ ታላቅ ናት!” እያሉ ይጮኹ ጀመር።

29. ወዲያውም በከተማው ሁሉ ሁከት ተነሣ፤ ሕዝቡም አንድ ላይ በማበር የመቄዶንያ ተወላጅ የሆኑትንና ከጳውሎስ ጋር ይጓዙ የነበሩትን ጓደኞቹን፣ ጋይዮስንና አርስጥሮኮስን ይዘው ወደ ጨዋታ ማሳያው ስፍራ እየሮጡ ገቡ።

30. ጳውሎስም ወጥቶ ሕዝቡ ፊት ለመቅረብ ፈልጎ ነበር፤ ደቀ መዛሙርት ግን ከለከሉት።

31. ከአውራጃው ባለ ሥልጣኖች አንዳንድ ወዳጆቹ እንኳ፣ ጳውሎስ ወደ ጨዋታ ማሳያው ስፍራ ደፍሮ እንዳይገባ ሰው ልከው ለመኑት።

32. ጉባኤውም ተበጣብጦ፣ አንዱ አንድ ነገር ሲናገር ሌላውም ሌላ እየተናገረ ይጯጯኽ ነበር፤ አብዛኛውም ሰው ለምን እዚያ እንደ ተሰበሰበ እንኳ አያውቅም ነበር።

33. አይሁድም እስክንድሮስን ከሕዝቡ መካከል ገፍተው ወደ ፊት ባወጡት ጊዜ፤ አንዳንዶቹ እንዲናገርላቸው ጮኹ፤ እርሱም ሊከራከርላቸው ፈልጎ ዝም እንዲሉ በምልክት ጠቀሳቸው።

34. ነገር ግን እርሱ አይሁዳዊ መሆኑን ባወቁ ጊዜ ሁሉም በአንድ ድምፅ፣ “የኤፌሶኗ አርጤምስ ታላቅ ናት” እያሉ ሁለት ሰዓት ያህል ጮኹ።

35. የከተማዪቱም ዋና ጸሓፊ ሕዝቡን ጸጥ አሰኝቶ እንዲህ አለ፤ “የኤፌሶን ሰዎች ሆይ፤ የታላቋ የአርጤምስ ቤተ መቅደስና ከሰማይ የወረደው ምስሏ ጠባቂ የኤፌሶን ከተማ ሕዝብ መሆኑን የማያውቅ ማን አለ?

36. ስለዚህ፣ ይህ ሐቅ የማይካድ እንደ መሆኑ መጠን፣ ልትረጋጉና አንዳች ነገር በጥድፊያ ከመፈጸም ልትጠቡ ይገባችኋል።

37. እነዚህን ሰዎች ቤተ መቅደስን ሳይዘርፉ ወይም አምላካችን በሆነችው ላይ የስድብ ቃል ሳይሰነዝሩ ይዛችሁ እዚህ ድረስ እንዲያው አምጥታችኋቸዋል።

38. እንግዲህ፣ ድሜጥሮስና ከእርሱ ጋር ያሉት አንጥረኞች በማንም ላይ አቤቱታ ካላቸው፣ ፍርድ ቤቱ ክፍት ነው፤ ዳኞችም አሉ፤ ክስ ማቅረብ ይችላሉ።

39. ከዚህ ሌላ ልታቀርቡ የፈለጋችሁት ነገር ካለ፣ በሕጋዊ ጉባኤ ይታያል።

40. አለበለዚያ ዛሬ ስለ ሆነው ነገር፣ በሁከት አነሣሽነት እንዳንከሰስ ያሠጋናል፤ አጥጋቢ ምክንያት ስለሌለንም፣ ስለ ሁከቱ ብንጠየቅበት መልስ መስጠት አንችልም።”

41. ይህን ከተናገረ በኋላም ጉባኤው እንዲበተን አደረገ።