ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. አግሪጳም ጳውሎስን፣ “ስለ ራስህ እንድትናገር ተፈቅዶልሃል” አለው። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ እጁን ዘርግቶ እንዲህ ሲል መከላከያውን አቀረበ፤

2. “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፤ አይሁድ በእኔ ላይ ላቀረቡት ክስ ሁሉ ዛሬ በፊትህ የመከላከያ መልስ ለማቅረብ በመቻሌ ራሴን እንደ ዕድለኛ እቈጥረዋለሁ፤

3. ይኸውም አንተ በተለይ የአይሁድን ልማድና ክርክር ሁሉ በሚገባ ስለምታውቅ ነው፤ ስለዚህ በትዕግሥት እንድታደምጠኝ እለምንሃለሁ።

4. “ገና ከልጅነቴ ጀምሮ፣ በአገሬም ሆነ በኢየሩሳሌም እንዴት እንደኖርሁ አይሁድ ሁሉ ያውቃሉ፤

5. ደግሞም ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ስለሚያውቁኝ ከሃይማኖታችን እጅግ ጥብቅ በሆነው ወገን ውስጥ ሆኜ እንደ አንድ ፈሪሳዊ መኖሬን ሊመሰክሩ ፈቃደኞች ከሆኑ ቃላቸውን ሊሰጡ ይችላሉ።

6. አሁንም ተከስሼ እዚህ የቀረብሁበት ምክንያት እግዚአብሔር ለአባቶቻችን ቃል የገባውን ነገር ተስፋ በማድረጌ ነው።

7. ዐሥራ ሁለቱ ነገዶቻችን ቀንና ሌሊት እግዚአብሔርን ከልብ እያገለገሉ፣ ሲፈጸም ለማየት የሚተጉለትም ተስፋ ይኸው ነው። ንጉሥ ሆይ፤ አይሁድም የሚከሱኝ ስለ ዚሁ ተስፋ ነው።

8. ለመሆኑ፣ እግዚአብሔር ሙታንን ማስነሣት እንደማይችል አድርጋችሁ የምትጥቈሩት ለምንድን ነው?

9. “እኔም ራሴ የናዝሬቱን የኢየሱስን ስም በምችለው መንገድ ሁሉ መቃወም እንዳለብኝ ወስኜ ነበር።

10. በኢየሩሳሌምም ያደረግሁት ይህንኑ ነበር፤ ከካህናት አለቆች ሥልጣን ተቀብዬ ብዙ ቅዱሳንን አሳስሬ አለሁ፤ በመገደላቸውም ተስማምቻለሁ፤

11. ላስቀጣቸውም ብዙ ጊዜ ከምኵራብ ምኵራብ እየተዘዋወርሁ፣ የስድብ ቃል እንዲናገሩ አስገድዳቸው ነበር፤ በቍጣም ተሞልቼ በውጭ አገር እስከሚገኙ ከተሞች ድረስ ተከታትዬ አሳደድኋቸው።

12. “በዚህ መሠረት አንድ ቀን ከካህናት አለቆች ሥልጣንና ትእዛዝ ተቀብዬ ወደ ደማስቆ በምጓዝበት ጊዜ፣

13. ንጉሥ ሆይ፤ እኵለ ቀን ላይ በመንገድ ሳለሁ፣ ብሩህነቱ ከፀሓይ የሚበልጥ ብርሃን በእኔና በባልንጀሮቼ ዙሪያ ከሰማይ ሲያበራ አየሁ፤

14. ሁላችንም በምድር ላይ ወደቅን፤ እኔም በዕብራይስጥ ቋንቋ፣ ‘ሳውል፤ ሳውል፤ ለምን ታሳድደኛለህ? መውጊያውን መጋፋት ጒዳቱ በአንተ ይብሳል’ የሚለኝን ድምፅ ሰማሁ።

15. “እኔም፣ ‘ጌታ ሆይ፤ አንተ ማን ነህ?’ ” አልሁ።“ጌታም እንዲህ አለኝ፤ ‘እኔ፣ አንተ የምታሳድደኝ ኢየሱስ ነኝ።

16. አሁንም፣ ተነሣና በእግርህ ቁም፤ ስለ እኔ ስላየኸውና ወደ ፊትም ስለማሳይህ ነገር አገልጋይና ምስክር እንድትሆን ልሾምህ ተገልጬልሃለሁ።

17. ከገዛ ሕዝብህና ወደ እነርሱ ከምልክህ ከአሕዛብ አድንሃለሁ፤

18. አንተም ዐይናቸውን ትከፍታለህ፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር ትመልሳቸዋለህ፤ እነርሱም የኀጢአትን ይቅርታ ይቀበላሉ፤ በእኔም በማመን በተቀደሱት መካከል ርስት ያገኛሉ።’

19. “እንግዲህ፣ ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፤ ከሰማይ ለታየኝ ራእይ አልታዘዝ አላልሁም፤

20. ነገር ግን በመጀመሪያ በደማስቆ ለሚኖሩ፣ ቀጥሎም በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላሉት ሁሉ፣ ከዚያም ለአሕዛብ፣ ንስሓ እንዲገቡና ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ፣ የንስሓም ፍሬ እንዲያሳዩ ገልጬ ተናገርሁ።

21. አይሁድም በመቅደስ ይዘው ሊገድሉኝ የሞከሩት በዚሁ ምክንያት ነው።

22. የእግዚአብሔር ርዳታ እስከ ዛሬ ስላልተለየኝ፣ እነሆ፤ እዚህ ቆሜ ለትንሹም ለትልቁም እመሰክራለሁ፤ ነቢያትና ሙሴ ይሆናል ይፈጸማል ካሉት በስተቀር አንዳች ነገር አልተናገርሁም፤

23. ይኸውም ክርስቶስ መከራን እንደሚቀበልና ከሙታን ቀዳሚ ሆኖ በመነሣት ለሕዝቡና ለአሕዛብ ብርሃንን እንደሚሰብክ ነው።”

24. ፊስጦስም የጳውሎስን ንግግር እዚህ ላይ በማቋረጥ ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “ጳውሎስ ሆይ፤ አእምሮህን ስተሃል፤ የትምህርትህም ብዛት አሳብዶሃል” አለው።

25. ጳውሎስ ግን እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ክቡር ፊስጦስ ሆይ፤ የምናገረው እውነተኛና ትክክለኛ ነገር እንጂ እብድስ አይደለሁም።

26. ይህን የምናገረውን ነገር ንጉሡ ያውቀዋልና፤ በፊቱ በልበ ሙሉነት እናገራለሁ፤ ደግሞም በድብቅ የተደረገ ነገር ባለመኖሩ፣ ከዚህ ነገር አንድም እንደማ ይሰወርበት ርግጠኛ ነኝ።

27. ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፤ ነቢያትን ታምን የለም ወይ? አዎን፤ እንደምታምን ዐውቃለሁ።”

28. አግሪጳም ጳውሎስን፣ “እንዲህ በቀላሉ ክርስቲያን የምታደርገኝ ይመስልሃልን?” አለው።

29. ጳውሎስም፣ “በቀላሉም ሆነ በብዙ፣ አንተ ብቻ ሳትሆን ዛሬ የሚሰሙኝ ሁሉ፣ ከዚህ ከታሰርሁበት ሰንሰለት በስተቀር፣ እንደ እኔ ይሆኑ ዘንድ እግዚአብሔርን እለምናለሁ” አለ።

30. ከዚህ በኋላ ንጉሡም፣ አገረ ገዡም፣ በርኒቄም፣ ከእነርሱ ጋር የተቀመጡትም ተነሡ፤

31. ወጥተውም ሲሄዱ፣ “ይህ ሰው እንኳን ለሞት ለእስራት የሚያበቃው ነገር አላደረገም” ተባባሉ።

32. አግሪጳም ፊስጦስን፣ “ይህ ሰው ወደ ቄሳር ይግባኝ ባይል ኖሮ መልቀቅ ይቻል ነበር” አለው።