ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 5 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ሐናንያና ሰጲራ

1. ሐናንያ የተባለ ሰው፣ ከሚስቱ ከሰጲራ ጋር መሬት ሸጠ፤

2. ሚስቱም በሚገባ እያወቀች ከሽያጩ የተወሰነ ገንዘብ በማስቀረት የተረፈውን አምጥቶ በሐዋርያት እግር ሥር አስቀመጠ።

3. ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለ፤ “ሐናንያ ሆይ፤ መንፈስ ቅዱስን ትዋሽና ከመሬቱ ሽያጭ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን ልብህን ለምን ሞላው?

4. ሳትሸጠው በፊት የአንተው አልነበረምን? ከሸጥኸውስ በኋላ ቢሆን ገንዘቡ በእጅህ አልነበረምን? ለመሆኑ ይህን ነገር እንዴት በልብህ አሰብህ? የዋሸኸው እኮ እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አይደለም።”

5. ሐናንያም ይህን እንደ ሰማ ወድቆ ሞተ፤ ይህን የሰሙትም ሁሉ ታላቅ ፍርሀት ያዛቸው።

6. ጒልማሶችም ተነሥተው አስከሬኑን ገነዙት፤ ወስደውም ቀበሩት።

7. ሦስት ሰዓት ያህልም ካለፈ በኋላ፣ ሚስቱ የሆነውን ሳታውቅ መጥታ ገባች።

8. ጴጥሮስም፣ “እስቲ ንገሪኝ፤ መሬታችሁን የሸጣችሁት በዚህ ዋጋ ነውን?” አላት።እርሷም፣ “አዎን፤ በዚሁ ዋጋ ነው” አለች።

9. ጴጥሮስም፣ “የጌታን መንፈስ ትፈታተኑ ዘንድ እንዴት እንዲህ ተስማማችሁ? እነሆ፤ ባልሽን የቀበሩት ሰዎች ተመልሰው እግራቸው ደጃፍ ላይ ነው፤ አንቺንም ይዘው ይወጣሉ” አላት።

10. እርሷም ወዲያውኑ እግሩ ሥር ወድቃ ሞተች፤ ጒልማሶቹም ሲገቡ ሞታ አገኟት፤ አውጥተውም በባሏ አጠገብ ቀበሯት።

11. መላዪቱን ቤተ ክርስቲያንና ይህን የሰሙትን ሁሉ፣ ታላቅ ፍርሀት ያዛቸው።

በሐዋርያት እጅ ብዙ ሰው ተፈወሰ

12. ሐዋርያትም በሕዝቡ መካከል ብዙ ታምራዊ ምልክቶችንና ድንቅ ሥራዎችን አደረጉ፤ አማኞቹም ሁሉ ‘የሰሎሞን ደጅ’ በተባለው መመላለሻ ይሰበሰቡ ነበር።

13. ከእነርሱ ጋር ሊቀላቀል የደፈረ ማንም አልነበረም፤ ሆኖም ሕዝቡ እጅግ ያከብሯቸው ነበር፤

14. ብዙ ወንዶችና ሴቶችም ከጊዜ ወደ ጊዜ በጌታ እያመኑ ወደ እነርሱ ይጨመሩ ነበር።

15. ከዚህም የተነሣ፣ ጴጥሮስ በዚያ ሲያልፍ፣ ቢያንስ ጥላው እንኳ በጥቂቶች ላይ እንዲያርፍባቸው በማለት ሕመምተኞችን ወደ ውጭ እያወጡ በዐልጋና በቃሬዛ በመንገድ ላይ ያስተኙ ነበር።

16. በኢየሩሳሌም አካባቢ ከሚገኙ ከተሞች፣ ሕመምተኞችንና በርኵሳን መናፍስት የሚሠቃዩትን ይዘው የሚመጡት ሰዎች አካባቢውን ያጨናንቁት ነበር፤ የመጡትም ሁሉ ይፈወሱ ነበር።

ሐዋርያት መከራና ስደት ደረሰባቸው

17. ከዚህም የተነሣ ሊቀ ካህናቱና አብረውት የነበሩት የሰዱቃውያን ወገን ሁሉ በቅናት ተሞሉ፤

18. ሐዋርያትንም ይዘው ማረፊያ ቤት ከተቷቸው።

19. ይሁን እንጂ የጌታ መልአክ በሌሊት የእስር ቤቱን ደጆች ከፍቶ አወጣቸውና፣

20. “ሂዱ፤ በቤተ መቅደሱም አደባባይ ቁሙ፤ የዚህንም ሕይወት ቃል ሁሉ ለሕዝብ ንገሩ” አላቸው።

21. እንደ ነጋም፣ በተነገራቸው መሠረት፣ ወደ ቤተ መቅደሱ አደባባይ ገብተው ሕዝቡን ማስተማር ጀመሩ።ሊቀ ካህናቱና ከእርሱ ጋር የነበሩት መጥተው የአይሁድን ሸንጎና የእስራኤልን ሽማግሌዎች ጉባኤ በሙሉ በአንድነት ሰበሰቡ፤ ሐዋርያትንም እንዲያመጡ ሰዎችን ወደ እስር ቤት ላኩ።

22. የተላኩትም ወደ እስር ቤቱ ሄደው በዚያ አላገኟቸውም፤ ተመልሰውም እንዲህ አሏቸው፤

23. “እስር ቤቱ በሚገባ ተልፎ፣ ጠባቂዎቹም በበሩ ላይ ቆመው አገኘን፤ ከፍተን ስንገባ ግን በውስጡ ማንም አልነበረም።”

24. የቤተ መቅደሱ ጥበቃ ሹምና የካህናት አለቆችም ይህን በሰሙ ጊዜ በነገሩ ተገረሙ፤ ግራም ተጋቡ።

25. በዚህ ጊዜ አንድ ሰው መጥቶ፣ “እነሆ፤ እስር ቤት ያስገባችኋቸው ሰዎች በቤተ መቅደሱ አደባባይ ቆመው ሕዝቡን እያስ ተማሩ ናቸው” አላቸው።

26. የጥበቃ ሹሙም ከወታደሮቹ ጋር ሄዶ፣ ይዞ አመጣቸው፤ ያመጧቸው ግን ሕዝቡ በድንጋይ እንዳይወግሯቸው ስለ ፈሩ በኀይል ሳያስገድዱ ነበር።

27. ሐዋርያትንም አምጥተው በሸንጎው ፊት አቆሟቸው፤ ሊቀ ካህናቱም እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፤

28. “በዚህ ስም እንዳታስተምሩ በጥብቅ አስጠንቅቀናችሁ ነበር፤ እናንተ ግን ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞላችኋት፤ ደግሞም እኛን ለዚህ ሰው ደም ተጠያቂዎች ልታደርጉን ቈርጣችሁ ተነሣችሁ።”

29. ጴጥሮስና ሌሎች ሐዋርያትም መልሰው እንዲህ አሉ፤ “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል!

30. እናንተ በዕንጨት ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን፣ የአባቶቻችን አምላክ ከሙታን አስነሣው፤

31. እርሱም ለእስራኤል ንስሓንና የኀጢአትን ስርየት ይሰጥ ዘንድ፣ እግዚአብሔር የሁሉ ራስና አዳኝ አድርጎ በቀኙ ከፍ ከፍ አደረገው።

32. እኛም ለእነዚህ ነገሮች ምስክር ነን፤ ደግሞም እግዚአብሔር ለሚታዘዙት የሰጠው መንፈስ ቅዱስ ምስክር ነው።”

33. ሰዎቹም ይህን በሰሙ ጊዜ ክፉኛ ተቈጡ፤ ሊገድሏቸውም ፈለጉ።

34. ነገር ግን በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ የተከበረ አንድ የሕግ መምህር፣ እርሱም ገማልያል የሚሉት ፈሪሳዊ ተነሥቶ በሸንጎው መካከል ቆመና ሐዋርያትን ወደ ውጭ አውጥተው ለጥቂት ጊዜ እንዲያዩአቸው አዘዘ፤

35. ለሸንጎውም እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፤ በእነዚህ ሰዎች ላይ ልታደርጉ ስላሰባችሁት ነገር በጥንቃቄ ልታጤኑ ይገባችኋል።

36. ከዚህ ቀደም፣ ቴዎዳስ ራሱን ትልቅ አድርጎ በመቍጠር ተነሥቶ፣ አራት መቶ ያህል ሰዎች ተባበሩት፤ ነገር ግን እርሱም ተገደለ፤ ተከታዮቹም ሁሉ ተበታተኑ፤ ነገሩም እንዳልነበር ሆነ።

37. ከእርሱም በኋላ፣ በሕዝብ ቈጠራው ወቅት ገሊላዊው ይሁዳ ተነሥቶ ብዙ ሕዝብ አሸፈተ፤ ተከታይም አግኝቶ ነበር፤ እርሱም ጠፋ፤ ተከታዮቹም ተበተኑ።

38. ስለዚህ አሁንም የምላችሁ፦ እነዚህን ሰዎች ተዉአቸው፤ አትንኳቸው፤ ሐሳባቸው ወይም አድራጎታቸው ከሰው ከሆነ ይጠፋልና፤

39. ከእግዚአብሔር ከሆነ ግን ልትገቷቸው አትችሉም፤ እንዲያውም ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ትገኙ ይሆናል።”

40. እነርሱም ምክሩን ተቀብለው፤ ሐዋርያትን አስጠርተው አስገረፏቸው፤ ዳግመኛም በኢየሱስ ስም እንዳይናገሩ አዘው ለቀቋቸው።

41. ሐዋርያትም፣ ስለ ስሙ ውርደትን ለመቀበል በመብቃታቸው ደስ እያላቸው ከሸንጎው ወጥተው ሄዱ፤

42. በየዕለቱም፣ በቤተ መቅደስም ሆነ በየቤቱ፣ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ከማስተማርና ከመስበክ ከቶ ወደ ኋላ አላሉም ነበር።