ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ጴጥሮስ አሕዛብ ቤት ለምን እንደ ገባ አስረዳ

1. ሐዋርያትና በይሁዳ የነበሩት ወንድሞች አሕዛብ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ተቀበሉ ሰሙ።

2. ስለዚህ ጴጥሮስ ወደ ኢየሩሳሌም በወጣ ጊዜ፣ ከተገረዙት ወገን የነበሩ አማኞች ነቀፉት፤

3. እንዲህም አሉት፤ “ወዳልተገረዙ ሰዎች ገብተህ ከእነርሱ ጋር በላህ።”

4. ጴጥሮስ ግን እንዲህ ሲል ነገሩን በቅደም ተከተል ያስረዳቸው ጀመር፤

5. “በኢዮጴ ከተማ ስጸልይ በተመስጦ ውስጥ እያለሁ ራእይ አየሁ፤ ትልቅ ጨርቅ የሚመስል ነገር፣ በአራት ማእዘን ተይዞ ከሰማይ እኔ ወደ ነበርሁበት ቦታ ሲወርድ አየሁ።

6. አተኵሬም ይህን ነገር ስመለከት አራት እግር ያላቸው እንስሳት፣ የዱር አራዊት፣ በምድር የሚሳቡ ፍጥረታትና በሰማይ የሚበሩ አዕዋፍ አየሁ።

7. በዚህ ጊዜ፣ ‘ጴጥሮስ ሆይ፤ ተነሣና ዐርደህ ብላ’ የሚለኝን ድምፅ ሰማሁ።

8. “እኔም፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ይህማ አይሆንም፤ እኔ ርኩስ ወይም ያልተቀደሰ ነገር ፈጽሞ ወደ አፌ ገብቶ አያውቅም’ አልሁ።

9. “ያም ድምፅ ዳግመኛ፣ ‘እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገውን አንተ እንደ ርኩስ አትቍጠረው’ ሲል ከሰማይ ተናገረኝ።

10. ይህም ሦስት ጊዜ ተደጋገመ፤ ከዚያ ሁሉም እንደ ገና ወደ ሰማይ ተወሰደ።

11. “ልክ በዚያው ሰዓት፣ ሦስት ሰዎች ከቂሳርያ ወደ እኔ ተልከው መጥተው እኔ ባለሁበት ቤት ደጅ ላይ ቆሙ፤

12. መንፈስ ቅዱስም ምንም ሳላወላውል ከእነርሱ ጋር እንድሄድ ነገረኝ። እነዚህም ስድስት ወንድሞች ከእኔ ጋር ሄዱ፤ ወደ ሰውየውም ቤት ገባን።

13. እርሱም መልአክ በቤቱ ውስጥ ቆሞ እንደ ታየውና እንዲህ እንዳለው ነገረን፤ ‘ወደ ኢዮጴ ሰው ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስጠራ፤

14. እርሱም አንተና የቤትህ ሰዎች ሁሉ የምትድኑበትን ቃል ይነግርሃል።’

15. “እኔም ገና መናገር ስጀምር፣ መንፈስ ቅዱስ፣ በመጀመሪያ በእኛ ላይ እንደ ወረደ ሁሉ በእነርሱም ላይ ወረደ።

16. በዚህ ጊዜ፣ ‘ዮሐንስ በውሃ አጠመቀ፤ እናንተ ግን በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ’ ሲል ጌታ የተናገረው ቃል ትዝ አለኝ።

17. እንግዲህ እግዚአብሔር በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስናምን ለእኛ የሰጠንን ስጦታ ለእነርሱም ከሰጣቸው፣ ታዲያ፣ እግዚአብሔርን መቋቋም እችል ዘንድ እኔ ማን ነኝ?”

18. ይህን በሰሙ ጊዜም የሚሉትን አጥተው እንዲህ እያሉ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ “ይህማ ከሆነ፣ አሕዛብም ወደ ሕይወት ይመጡ ዘንድ፣ እግዚአብሔር ንስሓን ሰጥቷቸዋል ማለት ነዋ።”

በአንጾኪያ የነበረችው ቤተ ክርስቲያን

19. በእስጢፋኖስ ላይ በተነሣው ስደት ምክንያት የተበተኑት አማኞች ቃሉን ለአይሁድ ብቻ እየተናገሩ እስከ ፊንቄ፣ እስከ ቆጵሮስና እስከ አንጾኪያ ድረስ ዘለቁ።

20. ከቆጵሮስና ከቀሬና የመጡት አንዳንዶች ሰዎች ግን ወደ አንጾኪያ ሄደው ለግሪኮችም ጭምር በመንገር የጌታን የኢየሱስን ወንጌል ሰበኩላቸው።

21. የጌታም እጅ ከእነርሱ ጋር ነበረ፤ ቍጥራቸውም እጅግ ብዙ የሆኑ ሰዎች አምነው ወደ ጌታ ተመለሱ።

22. ወሬውም በኢየሩሳሌም ከነበረችው ቤተ ክርስቲያን ጆሮ ደረሰ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱም በርናባስን ወደ አንጾኪያ ላከችው።

23. እርሱም እዚያ ደርሶ እግዚአብሔር በጸጋው የሠራውን ባየ ጊዜ ደስ አለው፤ ሁሉም በፍጹም ልብ በጌታ በመታመን እንዲጸኑ መከራቸው።

24. እርሱም መንፈስ ቅዱስንና እምነትን የተሞላ ደግ ሰው ነበር፤ ቍጥሩ ብዙ የሆነ ሕዝብም ወደ ጌታ ተጨመረ።

25. ከዚህ በኋላ በርናባስ፣ ሳውልን ለመፈለግ ወደ ጠርሴስ ሄደ፤

26. ባገኘውም ጊዜ ወደ አንጾኪያ አመጣው። ሁለቱም እዚያ ካለችው ቤተ ክርስቲያን ጋር በመሆን አንድ ዓመት ሙሉ እጅግ ብዙ ሕዝብ አስተማሩ፤ ደቀ መዛሙርትም ለመጀመሪያ ጊዜ በአንጾኪያ ‘ክርስቲያን’ ተብለው ተጠሩ።

27. በዚህ ጊዜ አንዳንድ ነቢያት ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ወረዱ፤

28. ከእነርሱም አንዱ አጋቦስ የተባለው ተነሥቶ በዓለም ሁሉ ታላቅ ራብ እንደሚሆን መንፈስ ቅዱስ አስመልክቶት ተናገረ፤ ይህም በቀላውዴዎስ ቄሳር ዘመን ተፈጸመ።

29. ደቀ መዛሙርትም እያንዳንዳቸው ዐቅማቸው በፈቀደ መጠን አዋጥተው በይሁዳ የሚኖሩትን ወንድሞች ለመርዳት ወሰኑ፤

30. ርዳታውንም በበርናባስና በሳውል እጅ ለሽማግሌዎቹ በመላክ፣ ይህንኑ አደረጉ።