ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የኢየሩሳሌም ጉባኤ

1. አንዳንድ ሰዎችም ከይሁዳ ወደ አንጾኪያ ወርደው፣ “በሙሴ ሥርዐት መሠረት ካልተገረዛችሁ ልትድኑ አትችሉም” በማለት ወንድሞችን ማስተማር ጀመሩ።

2. ይህም ጳውሎስንና በርናባስን ከእነርሱ ጋር ወደ ከረረ ጠብና ክርክር ውስጥ ከተታቸው። ስለዚህ ጳውሎስና በርናባስ ከሌሎች አንዳንድ ምእምናን ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተው ስለ ዚሁ ጒዳይ ሐዋርያትንና ሽማግሌዎችን እንዲጠይቁ ተወሰነ።

3. ቤተ ክርስቲያኒቱም እግረ መንገዳቸውን በፊንቄና በሰማርያ በኩል እንዲያልፉ ላከቻቸው፤ እነርሱም በእነዚህ ቦታዎች ለነበሩት የአሕዛብን መመለስና ማመን ነገሯቸው፤ ወንድሞችም ሁሉ በዚህ እጅግ ደስ አላቸው።

4. ኢየሩሳሌም በደረሱ ጊዜም፣ ቤተ ክርስቲያንና ሐዋርያት እንዲሁም ሽማግሌዎች ተቀበሏቸው፤ የተላኩትም እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ሆኖ የሠራውን ሁሉ ነገሯቸው።

5. ከፈሪሳውያን ወገን ያመኑት አንዳንዶቹ ተነሥተው በመቆም፣ “አሕዛብ እንዲገረዙና የሙሴን ሕግ እንዲጠብቁ ማድረግ አስፈላጊ ነው” አሉ።

6. ሐዋርያትና ሽማግሌዎችም ይህንኑ ጒዳይ ለማጤን ተሰበሰቡ።

7. ከብዙ ክርክር በኋላ ጴጥሮስ ተነሥቶ እንዲህ አላቸው፤ “ወንድሞች ሆይ፤ እግዚአብሔር ከጥቂት ጊዜ በፊት በእናንተ መካከል እኔን መርጦ፣ አሕዛብ የወንጌልን ቃል ከእኔ አንደበት ሰምተው እንዲያምኑ ማድረጉን ታውቃላችሁ።

8. ልብን የሚያውቅ አምላክ ለእኛ እንደ ሰጠን ሁሉ፣ ለእነርሱም መንፈስ ቅዱስን በመስጠት የተቀበላቸው መሆኑን መሰከረላቸው፤

9. ልባቸውንም በእምነት በማንጻት በእኛና በእነርሱ መካከል ምንም ልዩነት አላደረገም።

10. እንግዲህ፣ አባቶቻችንም እኛም ልንሸከመው ያልቻልነውን ቀንበር በደቀ መዛሙርት ጫንቃ ላይ በመጫን ለምን አሁን እግዚአብሔርን ትፈታተኑታላችሁ?

11. እኛም የዳንነው ልክ እንደ እነርሱ በጌታ በኢየሱስ ጸጋ መሆኑን እናምናለን።”

12. ጉባኤውም በሙሉ ዝም ብሎ፣ በርናባስና ጳውሎስ እግዚአብሔር በእነርሱ አማካይነት በአሕዛብ መካከል ስላደረጋቸው ታምራዊ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች ሲናገሩ ያዳምጣቸው ነበር።

13. እነርሱም ተናግረው ሲጨርሱ፣ ያዕቆብ ተነሥቶ በመቆም እንዲህ አለ፤ “ወንድሞች ሆይ፤ ስሙኝ፤

14. እግዚአብሔር ከአሕዛብ ወገን ለእርሱ የሚሆነውን ሕዝብ አስቀድሞ እንዴት እንደ ጐበኘ ስምዖን አስረድቶናል።

15. እንዲህ ተብሎ የተጻፈው የነቢያቱም ቃል ከዚህ ጋር ይስማማል፤

16. “ ‘ከዚህ በኋላ እመለሳለሁ፤የፈረሰውን የዳዊትን ቤት እገነባለሁ።ፍርስራሹን መልሼ አቆማለሁ፤እንደ ገናም እሠራዋለሁ፤

17. ይኸውም የቀሩት ሰዎች ጌታን እንዲፈልጉ፣ስሜን የተሸከሙ አሕዛብም እንዲሹኝ ነው፤እነዚህን ያደረገ ጌታ እንዲህ ይላል፤’

18. እነርሱም ከጥንት ጀምሮ የታወቁ ናቸው።

19. “ስለዚህ ወደ እግዚአብሔር የተመለሱትን አሕዛብ እንዳናስጨንቃቸው ይህ የእኔ ብያኔ ነው።

20. ይልቁን በጣዖት ከረከሰ ነገር፣ ከዝሙት ርኵሰት፣ ታንቆ የሞተ እንስሳ ሥጋ ከመብላትና ደም ከመመገብ እንዲርቁ ልንጽፍላቸው ይገባል፤

21. የሙሴ ሕግማ ከጥንት ጀምሮ በየሰንበቱ በምኵራብ ሲነበብና በየከተማው ሲሰበክ ኖሮአልና።”

ላመኑት አሕዛብ ከጉባኤው የተላከ ደብዳቤ

22. በዚህ ጊዜ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ከመላው ቤተ ክርስቲያን ጋር ሆነው ከመካከላቸው አንዳንድ ሰዎችን መርጠው፣ ከጳውሎስና ከበርንባስ ጋር ወደ አንጾኪያ ለመላክ ወሰኑ፤ ከወንድሞችም መካከል ዋነኛ የነበሩትን በርስያን የተባለውን ይሁዳንና ሲላስን መረጡ፤

23. በእነርሱም እጅ ቀጥሎ ያለውን ደብዳቤ ላኩ፤ወንድሞቻችሁ ከሆኑት ከሐዋርያትና ከሽማግሌዎች፤ከአሕዛብ ወገን አምነው በአንጾኪያ፣ በሶሪያና በኪልቅያ ለሚገኙ ወንድሞች፤ሰላምታችን ይድረሳችሁ።

24. አንዳንድ ሰዎች ያለ እኛ ፈቃድ ከእኛ ዘንድ ወጥተው በንግግራቸው ልባችሁን እንዳወኩና እንዳናወጧችሁ ሰምተናል።

25. ስለዚህ ጥቂት ሰዎች መርጠን ከተወዳጆቹ ከበርናባስና ከጳውሎስ ጋር ወደ እናንተ ለመላክ ሁላችንም ተስማምተናል፤

26. በርናባስና ጳውሎስም ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሕይወታቸውን አሳልፈው የሰጡ ናቸው።

27. ስለዚህ እኛ የጻፍነውን በቃል እንዲያረጋግጡላችሁ፣ እነሆ፤ ይሁዳንና ሲላስን ልከናል።

28. ከእነዚህ አስፈላጊ ነገሮች በስተቀር ሌላ ተጨማሪ ሸክም እንዳ ንጭንባችሁ፣ ለመንፈስ ቅዱስም ለእኛም መልካም መስሎ ታይቶናል፤ ይኸውም፦

29. ለጣዖት ከተሠዋ ነገር፣ ከደም፣ ታንቆ ከሞተ እንስሳ ሥጋ እንዲሁም ከዝሙት ርኵሰት እንድትርቁ ነው። ከእነዚህ ዐይነት ነገሮች ብትርቁ ለእናንተ መልካም ነው።ደኅና ሁኑ።

30. የተላኩትም ሰዎች ከተሰናበቱ በኋላ ወደ አንጾኪያም ወረዱ፤ በዚያም የምእመናኑን ጉባኤ በአንድነት ሰብስበው ደብዳቤውን ሰጧቸው።

31. ሕዝቡም ካነበቡት በኋላ አበረታታች በሆነው ቃሉ ደስ ተሰኙ።

32. ይሁዳና ሲላስም ራሳቸው ነቢያት ስለ ነበሩ፣ ወንድሞችን ብዙ ንግግር በማድረግ መከሯቸው፤ አበረቷቸውም።

33. በዚያም ጥቂት ጊዜ ከቈዩ በኋላ፣ ከወንድሞች በሰላም ተሰናብተው ወደ ላኳቸው ሰዎች ተመለሱ።

34. ሲላስ ግን እዚያው ለመቅረት ወሰነ።

35. ጳውሎስና በርናባስም ከሌሎች ብዙ ሰዎች ጋር ሆነው የጌታን ቃል እያስተማሩና እየሰበኩ በአንጾኪያ ተቀመጡ።

ጳውሎስና በርናባስ በሐሳብ ተለያዩ

36. ጳውሎስ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በርናባስን፣ “ተነሣና የጌታን ቃል ወደ ሰበክንባቸው ከተሞች ሁሉ እንሂድ፤ በዚያ ያሉ ወንድሞችም በምን ሁኔታ እንዳሉ ለማወቅ እንጐብኛቸው” አለው።

37. በርናባስም ማርቆስ የተባለው ዮሐንስ አብሮአችው እንዲሄድ ፈለገ፤

38. ጳውሎስ ግን እርሱን ይዞ ለመሄድ አልፈለገም፤ ምክንያቱም፣ ቀደም ሲል ማርቆስ ከእነርሱ ተለይቶ በጵንፍልያ ስለ ቀረና ወደ ሥራ አብሮአቸው ስላልሄደ ነበር።

39. እንዲህ የከረረ አለመግባባት በመካከላቸው ስለ ተፈጠረ እርስ በርስ ተለያዩ፤ ስለዚህ በርናባስ ማርቆስን ይዞ በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄደ።

40. ጳውሎስ ግን ሲላስን መረጠ፤ ወንድሞችም ለጌታ ጸጋ ዐደራ ከሰጡት በኋላ ተለይቶአቸው ሄደ፤

41. አብያተ ክርስቲያናትንም እያበረታታ በሶርያና በኪልቅያ በኩል ዐለፈ።