ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ጳውሎስ በመርከብ ወደ ሮም ተወሰደ

1. ወደ ኢጣሊያ እንድንሄድ በተወሰነ ጊዜ፣ ጳውሎስንና ሌሎቹን እስረኞች የንጉሠ ነገሥቱ ክፍለ ጦር አባል ለሆነው፣ ዩልዮስ ለተባለ የመቶ አለቃ አስረከቧቸው።

2. ከአድራሚጢስ ተነሥቶ በእስያ አውራጃ ባሕር ዳርቻ ላይ ወዳሉት ወደቦች በሚሄደው መርከብ ተሳፍረን የባሕር ጒዞ ጀመርን፤ በተሰሎንቄ ይኖር የነበረው የመቄዶንያ ሰው፣ አርስጥሮኮስም ከእኛ ጋር ነበረ።

3. በሚቀጥለው ቀን ሲዶና ደረስን፤ ዩልዮስም ለጳውሎስ ደግነት በማሳየት ወደ ወዳጆቹ ሄዶ ርዳታ እንዲቀበል ፈቀደለት።

4. ከዚያም ተነሥተን በባሕር ተጓዝን፤ ነፋስ ከፊት ለፊት ስለገጠመን፣ የቆጵሮስን ደሴት ተገን አድርገን ዐለፍን።

5. በኪልቅያና በጵንፍልያ ዳርቻ ያለውን ባሕር ከተሻገርን በኋላ በሉቅያ አገር ሙራ የተባለ ቦታ ደረስን።

6. ከዚያም የመቶ አለቃው ወደ ኢጣሊያ የሚሄድ የእስክንድርያ መርከብ አግኝቶ አሳፈረን።

7. ብዙ ቀን በዝግታ እየተጓዝን ቀኒዶስ አካባቢ በጭንቅ ደረስን፤ ነፋሱም ወደ ፊት እንዳንሄድ በከለከለን ጊዜ፣ በሰልሙና አጠገብ አድርገን በቀርጤስ ተተግነን ሄድን፤

8. ጥግ ጥጉንም ይዘን፣ በላሲያ ከተማ አጠገብ ወዳለው፣ ‘መልካም ወደብ’ ወደተባለ ስፍራ በጭንቅ ደረስን።

9. ብዙ ጊዜ ባክኖ፤ የጾሙ ጊዜ ስላለፈ በመርከብ መጓዙ አደገኛ ሆኖ ነበርና ጳውሎስ፣

10. “እናንት ሰዎች፤ ጒዞው አደገኛ እንደሚሆን፣ በመርከቡና በጭነቱ እንዲሁም በእኛ በራሳችን ላይ እንኳ ትልቅ ጒዳት እንደሚደርስ ይታየኛል” ብሎ አስጠነቀቃቸው።

11. የመቶ አለቃው ግን ከጳውሎስ ምክር ይልቅ የመርከቡ መሪና የመርከቡ ባለቤት ያሉትን ይሰማ ነበር።

12. ክረምቱንም በዚያ ለማሳለፍ ወደቡ አመቺ ስላልነበረ፣ አብዛኛዎቹ ፍንቄ ወደተባለው ወደብ ደርሰው በዚያ ለመክረም ተስፋ በማድረግ ጒዞአችንን እንድንቀጥል ውሳኔ አስተላለፉ፤ ወደቡም በቀርጤስ ደቡብ ምዕራብና ሰሜን ምዕራብ ትይዩ የሚገኝ ነበር።

የባሕሩ ማዕበል

13. መጠነኛ የደቡብ ነፋስ በነፈሰ ጊዜም እንዳሰቡት የሆነላቸው መስሎአቸው መልሕቁን ነቅለው፣ የቀርጤስን ዳርቻ በመያዝ ተጓዙ።

14. ብዙም ሳይቈይ ግን፣ ‘ሰሜናዊ ምሥራቅ’ የሚሉት ኀይለኛ ዐውሎ ነፋስ ከደሴቲቱ ተነሥቶ ቍልቍል መጣባቸው።

15. መርከቢቱም በማዕበሉ ስለ ተያዘች፣ ወደ ነፋሱ ልትገፋ አልቻለችም፤ ስለዚህ መንገድ ለቀን በነፋሱ ተነዳን።

16. ቄዳ የተባለችውን ትንሽ ደሴት ተገን አድርገን በማለፍ፣ የመርከቧን ሕይወት አድን ጀልባ በብዙ ድካም ለማትረፍ ቻልን፤

17. ጀልባዋንም ወደ ላይ ጐትተው ካወጧት በኋላ መርከቧ እንዳትፈራርስ ዙሪያዋን በገመድ ጠምጥመው አሰሯት፤ ስርቲስ ከተባለው አሸዋማ ደለል ጋር ሄደው እንዳይላተሙ ስለ ፈሩም፣ የመርከቧን ሸራ አውርደው እንዲሁ በዘፈቀደ እንድትነዳ አደረጉ።

18. ማዕበሉም ክፉኛ ስላንገላታን፣ በማግስቱ ጭነቱን እያነሡ ወደ ባሕር ይጥሉ ጀመር፤

19. በሦስተኛውም ቀን፣ የመርከቧን ሸራ ማውጫና ማውረጃ መሣሪያ በገዛ እጃቸው ነቃቅለው ወደ ባሕር ጣሉት።

20. ብዙ ቀን፣ ፀሓይንም ከዋክብትንም ማየት ስላልተቻለና ነፋስ ስለ በረታብን፣ ለመትረፍ የነበረን ተስፋ ሁሉ ተሟጠጠ።

21. ሰዎቹ እህል ሳይቀምሱ ብዙ ቀን ከቈዩ በኋላ፣ ጳውሎስ በመካከላቸው ቆሞ እንዲህ አለ፤ “እናንት ሰዎች ሆይ፤ የነገርኋችሁን ሰምታችሁ ቢሆን ኖሮ፣ ከቀርጤስ ባልተነ ሣችሁና ይህ ጒዳትና ጥፋት ባልደረሰባችሁ ነበር።

22. አሁንም ቢሆን አይዟችሁ መርከቧ እንጂ ከእናንተ አንዲት ነፍስ እንኳ አትጠፋምና።

23. በትላንትናዋ ሌሊት፣ የእርሱ የሆንሁትና የማመልከው እግዚአብሔር የላከው መልአክ በአጠገቤ ቆሞ፣

24. ‘ጳውሎስ ሆይ፤ አትፍራ፤ በቄሳር ፊት መቆም ይገባሃል፤ ከአንተ ጋር የሚጓዙትንም ሰዎች ሕይወት እግዚአብሔር አትርፎልሃል’ አለኝ።

25. ስለዚህ፣ እናንት ሰዎች ሆይ፤ አይዞአችሁ እርሱ እንደ ነገረኝ እንደዚያው እንደሚሆን በእግዚአብሔር አምናለሁና።

26. ይሁን እንጂ፣ ወደ አንዲት ደሴት በነፋስ ተወስደን እዚያ መጣላችን አይቀርም።”

በመርከቡ አደጋ መድረሱ

27. በዐሥራ አራተኛው ሌሊት በአድርያ ባሕር ላይ ከወዲያ ወዲህ ስንገላታ፣ እኩለ ሌሊት ገደማ መርከበኞቹ ወደ መሬት የተቃረቡ መሰላቸው፤

28. የጥልቀት መለኪያውን ገመድ ወደ ታች ጥለው ሲመለከቱት የውሃው ጥልቀት አርባ ሜትር ያህል ሆኖ አገኙት፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላም ደግመው ሲጥሉ ጥልቀቱ፣ ሠላሳ ሜትር ያህል ሆነ።

29. ከቋጥኞቹም ጋር እንዳንላተም በመፍራት፣ አራት መልሕቆች ከመርከቡ በስተ ኋላ ጣሉ፤ ምነው በነጋ እያሉም ይለምኑ ነበር።

30. መርከበኞቹም ከመርከቡ በስተ ፊት መልሕቅ የሚጥሉ መስለው፣ ትንሿን ጀልባ በማውረድ ከመርከቧ ሊያመልጡ ሞከሩ።

31. ጳውሎስም የመቶ አለቃውንና ወታደሮቹን፣ “እነዚህ ሰዎች መርከቡ ላይ ካልቈዩ እናንተም ልትተርፉ አትችሉም” አላቸው።

32. በዚህ ጊዜ ወታደሮቹ ገመዶቹን ቈርጠው ትንሿ ጀልባ ባሕሩ ላይ ተንሳፋ እንድትቀር ለቀቋት።

33. ልክ ሊነጋጋ ሲል፣ ጳውሎስ ሁሉም ምግብ እንዲበሉ እንዲህ ሲል ለመናቸው፤ “ዐሥራ አራት ቀን ሙሉ ልባችሁ ተንጠልጥሎ ምንም ሳትቀምሱ ጦማችሁን ሰነበታችሁ፤

34. ስለዚህ ስለሚያበረታችሁ አሁን እህል እንድትቀምሱ እለምናችኋላሁ፤ ከእናንተ መካከል ከራሱ ጠጒር አንዲት እንኳ የሚነካበት ማንም የለምና።”

35. ይህን ካለ በኋላም፣ እንጀራ ይዞ በሁሉም ፊት እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ቈርሶም ይበላ ጀመር።

36. ሁሉም ተበራቱና እንጀራውን ራሳቸው ወስደው በሉ።

37. በመርከቡም ላይ በአጠቃላይ ሁለት መቶ ሰባ ስድስት ሰዎች ነበርን።

38. በልተውም ከጠገቡ በኋላ ስንዴውን ወደ ባሕር በመጣል የመርከቡን ክብደት አቃለሉ።

39. በነጋም ጊዜ፣ ወደ የብስ መቅረባቸውን አላወቁም ነበር፤ ነገር ግን ዳር ዳሩ አሸዋማ የሆነ የባሕር ሰርጥ አይተው፣ ቢቻላቸው መርከቡን ገፍተው ወደዚያ ለማድረስ ወሰኑ።

40. ከዚያም መልሕቆቹን ቈርጠው ባሕር ውስጥ ጥለው ሄዱ፤ የመቅዘፊያውንም ገመድ በዚያው ጊዜ ፈቱ፤ የፊተኛውንም ሸራ ለነፋስ ከፍ አድርገው ወደ ባሕሩ ዳርቻ አቀኑ።

41. ነገር ግን መርከቡ ከአሸዋ ቍልል ጋር ተላትሞ፤ መሬት ነካ፤ የፊተኛው ክፍሉም አሸዋው ውስጥ ተቀርቅሮ አልነቃነቅ አለ፤ የኋለኛው ክፍሉም በማዕበሉ ክፉኛ ስለ ተመታ ይሰባበር ጀመር።

42. ወታደሮቹም ከእስረኞች ማንም ዋኝቶ ለማምለጥ ቢሞክር ለመግደል ተስማሙ።

43. የመቶ አለቃው ግን ጳውሎስ እንዲተርፍ ስለ ፈለገ፣ ያሰቡትን እንዳይፈጽሙ ከለከላቸው፤ መዋኘት የሚችሉ ከመርከብ እየዘለሉ አስቀድመው ከባሕሩ ወደ ምድር እንዲወጡ፣

44. የተቀሩት ደግሞ በሳንቃዎች ወይም በመርከቡ ስብርባሪ እየተንጠላጠሉ እንዲወጡ አዘዘ። በዚህ መንገድ ሁሉም በደኅና ወደ ምድር ደረሱ።