ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 2 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በበዓለ ኀምሳ ቀን መንፈስ ቅዱስ ወረደ

1. የበዓለ ኀምሳ ቀን በደረሰ ጊዜ ሁሉም በአንድነት፣ በአንድ ስፍራ ተሰብስበው ነበር፤

2. ድንገትም እንደ ብርቱ ዐውሎ ነፋስ ያለ ድምፅ ከሰማይ መጥቶ ተቀምጠው የነበሩበትን ቤት እንዳለ ሞላው።

3. የእሳት ምላሶች የሚመስሉም ታዩአቸው፤ ተከፋፍለውም በእያንዳንዳቸው ላይ ዐረፉ።

4. ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ መንፈስም እንዲናገሩ በሰጣቸው መጠን በሌሎች ቋንቋዎች ይናገሩ ጀመር።

5. በዚህ ጊዜ ከሰማይ በታች ካለው ሕዝብ ሁሉ የመጡና እግዚአብሔርን የሚፈሩ አይሁድ በኢየሩሳሌም ነበሩ።

6. ይህን ድምፅ ሲሰሙ፣ ብዙ ሕዝብ በአንድነት ተሰበሰቡ፤ እያንዳንዱም ሰው፣ ሰዎቹ በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ በመስማቱ ግራ ተጋባ፤

7. በመገረምና በመደነቅም እንዲህ አሉ፤ “እነዚህ የሚነጋገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን?

8. ታዲያ፣ እያንዳንዳችን በተወለድን በት፣ በራሳችን ቋንቋ ሲናገሩ የምንሰማቸው እንዴት ቢሆን ነው?

9. እኛ የጳርቴና፣ የሜድ፣ የኢላሜጤም ሰዎች፣ በመስጴጦምያ፣ በይሁዳ፣ በቀጶዶቅያ፣ በጳንጦስ፣ በእስያ፣

10. በፍርግያ፣ በጵንፍልያ፣ በግብፅ፣ በቀሬና አጠገብ ባሉት በሊቢያ አውራጃዎች የምንኖር፣ ከሮም የመጣን

11. አይሁድና ወደ ይሁዲነት የገባን፣ የቀርጤስና የዐረብ ሰዎች ስንሆን፣ ሰዎቹ የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በየቋንቋችን ሲናገሩ እንሰማቸዋለን!”

12. ሁሉም በአድናቆትና ግራ በመጋባት፣ “ይህ ነገር ምን ይሆን?” ተባባሉ።

13. አንዳንዶቹ ደግሞ “ያልፈላ ብዙ የወይን ጠጅ ጠጥተዋል” በማለት አፌዙባቸው።

ጴጥሮስ ለሕዝቡ ንግግር አደረገ

14. በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ከዐሥራ አንዱ ጋር ተነሥቶ ቆመ፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ለሕዝቡ ተናገረ፤ “እናንት የይሁዳ ሰዎች፤ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁሉ፤ ይህን አንድ ነገር ዕወቁ፤ በጥሞናም አድምጡ።

15. ጊዜው ገና ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ስለ ሆነ፣ እናንተ እንደምታስቡት እነዚህ ሰዎች አልሰከሩም።

16. ነገር ግን ይህ በነቢዩ በኢዩኤል እንዲህ ተብሎ የተነገረ ነው፤

17. “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በመጨረሻው ቀን፣መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈሳለሁ፤ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤ጒልማሶቻችሁ ራእይ ያያሉ፤ሽማግሌዎቻችሁ ሕልም ያልማሉ።

18. በዚያ ጊዜ በወንዶችና በሴቶች አገልጋዮቼ ላይ፣መንፈሴን አፈሳለሁ፤እነርሱም ትንቢት ይናገራሉ።

19. በላይ በሰማያት ድንቅ ነገሮችን፣አሳያለሁ፤ በታች በምድርም ምልክቶችን እሰጣለሁ፤ደምና እሳት፣ የጢስም ጭጋግ ይሆናል።

20. ታላቅና ክቡር የሆነው የጌታ ቀን ከመምጣቱ በፊት፣ፀሓይ ወደ ጨለማ፣ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ።

21. የጌታን ስም፣የሚጠራ ሁሉ ይድናል።’

22. “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፤ ይህን ቃል ስሙ፤ እናንት ራሳችሁ እንደምታውቁት፣ እግዚአብሔር በመካከላችሁ ታምራትን፣ ድንቅ ነገሮችንና ምልክቶችን በእርሱ በኩል በማድረግ ለናዝሬቱ ኢየሱስ መስክሮለታል።

23. እግዚአብሔር በጥንት ውሳኔውና በቀደመው ዕውቀቱ ይህን ሰው አሳልፎ በእጃችሁ ሰጣችሁ፤ እናንተም በክፉ ሰዎች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት።

24. እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አስወግዶ አስነሣው፤ ሞት ይዞ ሊያስቀረው አልቻለምና።

25. ዳዊትም ስለ እርሱ እንዲህ ይላል፤“ ‘ጌታን ሁል ጊዜ በፊቴ አየዋለሁ፤እርሱ በቀኜ ነውና፣ከቶ አልታወክም።

26. ስለዚህ ልቤ ደስ አለው፤ አንደበቴም ሐሤት አደረገ፤ሥጋዬም በተስፋ ይኖራል።

27. ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፤ቅዱስህም መበስበስን እንዲያይ አታደርግም።

28. የሕይወትን መንገድ እንዳውቅ አደረግኸኝ፤በፊትህም በሐሤት ትሞላኛለህ።’

29. “ወንድሞች ሆይ፤ ከቀደምት አባቶች ዳዊት ሞቶ እንደ ተቀበረ፣ መቃብሩም እስከ ዛሬ ድረስ በመካከላችን እንደሚገኝ በድፍረት መናገር እችላለሁ።

30. ነቢይ በመሆኑም፣ እግዚአብሔር ከዘሮቹ አንዱን በዙፋኑ ላይ እንደሚያስቀምጥ በመሐላ ቃል የገባለት መሆኑን ዐወቀ።

31. ይህንን አስቀድሞ በማየቱ እርሱ በሲኦል እንደማይቀርና ሥጋውም እንደማይበሰብስ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ ተናገረ።

32. ይህን ኢየሱስ፣ እግዚአብሔር ከሞት አስነሣው፤ እኛም ሁላችን ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን።

33. ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ካለ በኋላ፣ የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ከአብ ተቀብሎ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው።

34. ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣም፤እርሱ ራሱ ግን እንዲህ ብሎአል፤“ ‘ጌታ ጌታዬን፣

35. “ጠላቶችህን ለእግርህ መረገጫ እስከማደርግልህ ድረስ፣በቀኜ ተቀመጥ” አለው።’

36. “እንግዲህ፣ እግዚአብሔር ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን፣ ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ ይረዳ!”

37. ሕዝቡም ይህን በሰሙ ጊዜ ልባቸው እጅግ ተነካ፤ ጴጥሮስንና ሌሎቹንም ሐዋርያት፣ “ወንድሞች ሆይ፤ ታዲያ ምን እናድርግ?” አሏቸው።

38. ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፤ “ንስሓ ግቡ፤ ኀጢአታችሁም እንዲሰረይላችሁ፣ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ።

39. የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ እንዲሁም ጌታ አምላካችን ወደ ራሱ ለሚጠራቸው፣ በሩቅ ላሉትም ሁሉ ነውና።”

40. በሌላ ብዙ ቃል እየመሰከረላቸው፣ “ከዚህ ጠማማ ትውልድ ራሳችሁን አድኑ” በማለት አስጠነቀቃቸው።

41. ቃሉን የተቀበሉትም ተጠመቁ፤ በዚያ ቀን ሦስት ሺህ ያህል ሰዎች በቍጥራቸው ላይ ተጨመሩ።

የአማኞች የኅብረት ኑሮ

42. እነርሱም በሐዋርያት ትምህርትና በኅብረት፣ እንጀራውንም በመቍረስና በጸሎት ይተጉ ነበር።

43. በሐዋርያት እጅ ብዙ ድንቅና ታምራት ይደረግ ስለ ነበር፣ ሰው ሁሉ ፍርሀት አደረበት።

44. ያመኑት ሁሉ በአንድነት ነበሩ፤ ያላቸውንም ሁሉ የጋራ አደረጉ።

45. ሀብታቸውንና ንብረታቸውንም እየሸጡ ለእያንዳንዱ ሰው የሚያስፈልገውን ያህል ይሰጡት ነበር።

46. በየዕለቱ በቤተ መቅደስ በአንድነት እየተገናኙ፣ በቤታቸውም እንጀራ እየቈረሱ በደስታና በቀና ልብ ይመገቡ ነበር፤

47. እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፣ በሕዝቡ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው፤ ጌታም የሚድኑትን በቍጥራቸው ላይ ዕለት በዕለት ይጨምር ነበር።