ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36
  37. 37
  38. 38
  39. 39
  40. 40
  41. 41
  42. 42
  43. 43
  44. 44
  45. 45
  46. 46
  47. 47
  48. 48
  49. 49
  50. 50

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ይስሐቅና አቢሜሌክ

1. ቀድሞ በአብርሃም ዘመን ከደረሰው ራብ ሌላ፣ በአገሩ ላይ ራብ ሆነ። ይስሐቅም የፍልስጥኤም ንጉሥ አቢሜሌክ ወደሚኖርበት ወደ ጌራራ ሄደ።

2. በዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ለይስሐቅ ተገልጦ እንዲህ አለው፤ “እኔ በምነግርህ ምድር ተቀመጥ እንጂ፣ ወደ ግብፅ አትውረድ፤

3. ለጥቂት ጊዜ እዚሁ አገር ተቀመጥ፤ እኔም ካንተ ጋር እሆናለሁ፤ እባርክሃለሁም፤ ይህን ምድር በሙሉ ለአንተና ለዘርህ በመስጠት ለአባትህ ለአብርሃም በመሐላ የገባሁለትን ቃል አጸናለሁ።

4. ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፤ ይህን ምድር በሙሉ ለዘርህ እሰጣለሁ፤ የምድር ሕዝቦችም ሁሉ በዘርህ አማካይነት ይባረካሉ፤

5. ይኸውም አብርሃም ቃሌን ሰምቶ፣ ድንጋጌዬን፣ ትእዛዜን፣ ሥርዐቴንና ሕጌን በመጠበቁ ነው።”

6. ስለዚህ ይስሐቅ በጌራራ ተቀመጠ።

7. የዚያም አገር ሰዎች ስለ ሚስቱ በጠየቁት ጊዜ፣ “እኅቴ ናት” አለ፤ ምክንያቱም፣ “ሚስቴ ናት ብል ርብቃ ቈንጆ ስለሆነች፣ ያገሬው ሰዎች በእርሷ ምክንያት ይገድሉኛል” በማለት ፈርቶ ነበር።

8. ይስሐቅ ብዙ ጊዜ በዚያ ከኖረ በኋላ፣ የፍልስጥኤም ንጉሥ አቢሜሌክ አንድ ቀን ወደ ውጭ ሲመለከት፣ ይስሐቅ ሚስቱን ርብቃን ሲዳራት አየ።

9. አቢሜሌክም ይስሐቅን ጠርቶ፣ “እርሷ ሚስትህ ሆና ሳለች፣ እንዴት እኅቴ ናት ትላለህ?” አለው።ይስሐቅም፣ “በእርሷ ሰበብ፣ ሕይወቴን እንዳላጣ ብዬ ነው” አለው።

10. አቢሜሌክም መልሶ፣ “እንዲህ ያለ ነገር ያደረግህብን ለምንድን ነው? ከሰዎቻችን አንዱ ሚስትህን ቢደፍራት ኖሮ በእኛ ላይ በደል አስከትለህብን ነበር እኮ!” አለው።

11. አቢሜሌክም፣ “ይህን ሰው ወይም ሚስቱን የነካ በሞት ይቀጣል” የሚል ትእዛዝ ለሕዝቡ ሁሉ አወጣ።

12. ይስሐቅም በዚያች ምድር ዘር ዘራ፣ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ባረከለትና በዚያኑ ዓመት መቶ ዕጥፍ አመረተ።

13. ሰውየውም እጅግ ባለጠጋ እስኪሆን ድረስ ሀብት በሀብት ላይ እየተጨመረለት ሄደ።

14. ብዙ የበግና የፍየል መንጋ፣ ብዙ ከብት፣ ብዙ አገልጋዮችም ስለ ነበሩት፣ ፍልስጥኤማውያን ተመቀኙት።

15. ከዚህ የተነሣ ፍልስጥኤማውያን፣ አባቱ አብርሃም በሕይወት በነበረበት ጊዜ፣ የአብርሃም አገልጋዮች የቈፈሩአቸውን የውሃ ጒድጓዶች በሙሉ ዐፈር ሞልተው ደፈኑዋቸው።

16. አቢሜሌክም ይስሐቅን፣ “ከእኛ ይልቅ ኀያል ሆነሃልና አገራችንን ልቀቅልን” አለው።

17. ይስሐቅም ያን ቦታ ትቶ ሄደ፤ በጌራራ ሸለቆም ተቀመጠ።

18. ይስሐቅም በአባቱ በአብርሃም ጊዜ ተቈፍረው የነበሩትን፣ አባቱ ከሞተ በኋላ ፍልስጥኤማውያን የደፈኑአቸውን የውሃ ጒድጓዶች እንደ ገና እንዲከፈቱ አደረገ፤ አባቱ ቀድሞ ባወጣላቸው ስምም መልሶ ጠራቸው።

19. የይስሐቅ አገልጋዮች በሸለቆው ውስጥ ሲቈፍሩ፣ ከጒድጓዱ የሚፈልቅ ውሃ አገኙ።

20. የጌራራ እረኞች ግን፣ “ውሃው የእኛ ነው” በማለት ከይስሐቅ እረኞች ጋር ጠብ አነሡ፤ ከዚህ የተነሣ ይስሐቅ ያን የውሃ ጒድጓድ ኤሴቅ ብሎ ጠራው፤ በጒድጓዱ ምክንያት ተጣልተውታልና።

21. አሁንም እንደ ገና ሌላ የውሃ ጒድጓድ ቈፈሩ፤ አሁንም ሌላ ግጭት ተፈጠረ፤ ስለዚህ የውሃ ጒድጓዱን ስጥና ብሎ ጠራው።

22. ይስሐቅም ያን ቦታ ትቶ ሌላ ስፍራ ላይ የውሃ ጒድጓድ አስቈፈረ፤ በዚህ ጊዜ ግን አንድም ሰው ጠብ አላነሣበትም፤ ስለዚህ ያን የውሃ ጒድጓድ፣ “አሁን እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰፊ ቦታ ሰጥቶናል፤ እኛም በምድር ላይ እንበዛለን” ሲል ርኆቦት ብሎ ጠራው።

23. ከዚያም ይስሐቅ ወደ ቤርሳቤህ ወጣ።

24. በዚያም ሌሊት እግዚአብሔር (ያህዌ) ተገለጠለትና፣ “እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ (ኤሎሂም) ነኝ፤ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እባርክሃለሁ፤ ስለ አገልጋዬም ስለ አብርሃም ስል ዘርህን አበዛለሁ” አለው።

25. ይስሐቅም በዚያ ስፍራ መሠዊያ ሠርቶ፣ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ስም ጠራ፤ ድንኳንም ተከለ፤ አገልጋዮቹም በዚያ የውሃ ጒድጓድ ቈፈሩ።

26. አቢሜሌክም ከአማካሪው ከአዘኮትና ከሰራዊቱ አዛዥ ከፊኮል ጋር ከጌራራ ተነሥቶ ይስሐቅ ወዳለበት ስፍራ መጣ።

27. ይስሐቅም፣ “ጠልታችሁኝ ካባረራችሁኝ በኋላ፣ አሁን ደግሞ ለምን መጣችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው።

28. እነርሱም እንዲህ አሉ፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ከአንተ ጋር መሆኑን በግልጽ ተረድተናል፤ ስለዚህም፣ ‘በመሐላ የጸና ውል በመካከላችን መኖር አለበት’ አልን፤ ይህም በእኛና በአንተ መካካል የሚጸናውል ነው፤ አሁንም ከአንተ ጋር ስምምነት እናድርግ፤

29. አንተን እንዳልጐዳንህ፣ ነገር ግን በጎነትን እንዳሳየንህና በሰላም እንደ ሸኘንህ ሁሉ፣ አንተም ክፉ እንዳታደርግብን በመካከላችን ውል ይደረግ፤ አንተን እንደሆን መቼም እግዚአብሔር (ያህዌ) ባርኮሃል።”

30. ይስሐቅም ድግስ ደግሶ፣ አበላቸው፤ አጠጣቸው።

31. በማግስቱም በማለዳ ተነሥተው፣ በመካከላቸው መሐላ ፈጸሙ። ይስሐቅም አሰናበታቸው፤ እነርሱም በሰላም ሄዱ።

32. በዚያኑ ዕለት፣ የይስሐቅ አገልጋዮች መጥተው ስለ ቈፈሩት የውሃ ጒድጓድ ነገሩት፤ “ውሃ እኮ አገኘን!” አሉት።

33. እርሱም የውሃውን ጒድጓድ ሳቤህ አለው፤ ከዚያም የተነሣ የከተማዪቱ ስም እስከ ዛሬ ድረስ ቤርሳቤህ ተብሎ ይጠራል።

34. ዔሳው አርባ ዓመት በሆነው ጊዜ፣ የኬጢያዊውን የብኤሪን ልጅ ዮዲትን እንዲሁም የኬጢያዊውን የኤሎንን ልጅ ቤሴሞትን አገባ፤

35. በእነዚህም ሴቶች ምክንያት የይስሐቅና የርብቃ ልብ ያዝን ነበር።