ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36
  37. 37
  38. 38
  39. 39
  40. 40
  41. 41
  42. 42
  43. 43
  44. 44
  45. 45
  46. 46
  47. 47
  48. 48
  49. 49
  50. 50

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 37 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የዮሴፍ ሕልሞች

1. ያዕቆብ አባቱ በኖረበት በከነዓን ምድር ተቀመጠ።

2. የያዕቆብ ትውልድ ታሪክ ይህ ነው።ዮሴፍ የዐሥራ ሰባት ዓመት ወጣት በነበረ ጊዜ፣ ከአባቱ ሚስቶች ከባላና ከዘለፋ ከተወለዱት ወንድሞቹ ጋር የአባቱን በጎችና ፍየሎች ይጠብቅ ነበር። እርሱም ስለ ወንድሞቹ ድርጊት ለአባቱ መጥፎ ወሬ ይዞለት መጣ።

3. እስራኤል ዮሴፍን በስተርጅናው ስለ ወለደው፣ ከልጆቹ ሁሉ አብልጦ ይወደው ነበር፤ በኅብረ ቀለማት ያጌጠ እጀ ጠባብም አደረገለት።

4. ወንድሞቹም፣ አባታቸው ከእነርሱ አብልጦ የሚወደው መሆኑን ሲያዩ፣ ዮሴፍን ጠሉት፤ በቅን አንደበትም ሊያናግሩት አልቻሉም።

5. ዮሴፍም ሕልም አለመ፤ ሕልሙንም ለወንድሞቹ ሲነግራቸው የባሰ ጠሉት።

6. እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ያየሁትን ሕልም ልንገራችሁ አድምጡኝ

7. እኛ ሁላችን በዕርሻ ውስጥ ነዶ እናስር ነበር፤ የእኔ ነዶ በድንገት ተነሥታ ቀጥ ብላ ቆመች፤ የእናንተም ነዶዎች ዙሪያዋን ከበው ለእኔ ነዶ ሰገዱላት።”

8. ወንድሞቹም፣ “ለካስ በላያችን ለመንገሥ ታስባለህና! ለመሆኑ አንተ እኛን ልትገዛ!” አሉት፤ ስለ ሕልሙና ስለ ተናገረው ቃል ከፊት ይልቅ ጠሉት።

9. እንደ ገናም ሌላ ሕልም አለመ፤ ለወንድሞቹም፣ “እነሆ፤ ሌላ ሕልም አለምሁ፤ ፀሓይና ጨረቃ፣ ዐሥራ አንድ ከዋክብትም ሲሰግዱልኝ አየሁ” ብሎ ነገራቸው።

10. ሕልሙን ለአባቱና ለወንድሞቹ በነገራቸው ጊዜ፣ አባቱ “ይህ ያየኸው ሕልም ምንድን ነው? እኔና እናትህ ወንድሞችህም በፊትህ ወደ ምድር ተጐንብሰን በእርግጥ ልንሰግድልህ ነው?” ሲል ገሠጸው።

11. ወንድሞቹ ቀኑበት፤ አባቱ ግን ነገሩን በልቡ ያዘው።

ወንድሞቹ ዮሴፍን ሸጡት

12. ከዚህም በኋላ የዮሴፍ ወንድሞች የአባታቸውን በጎችና ፍየሎች ለማሰማራት ወደ ሴኬም አካባቢ ሄዱ፤

13. እስራኤልም ዮሴፍን “እንደምታውቀው ወንድሞችህ መንጎቹን በሴኬም አካባቢ አሰማርተዋል፤ በል ተነሥ፣ ወደ እነርሱ ልላክህ።” አለው።ዮሴፍም “ይሁን እሺ” አለው።

14. ያዕቆብም፣ “ሄደህ ወንድሞችህም፣ መንጎቹም ደኅና መሆናቸውን አይተህ ወሬያቸውን አምጣልኝ” አለው፤ ከኬብሮንም ሸለቆ ወደ ሴኬም ላከው። ዮሴፍም ሴኬም በደረሰ ጊዜ፣

15. ሜዳ ላይ ወዲያ ወዲህ ሲባዝን አንድ ሰው አግኝቶት “ምን እየፈለግህ ነው?” ሲል ጠየቀው።

16. ዮሴፍም፣ “ወንድሞቼን እየፈለግኋቸው ነው፤ መንጎቻቸውን የት እንዳሰማሩ ልትነግረኝ ትችላለህ?” አለው።

17. ሰውየውም፣ “ከዚህ ሄደዋል፤ ደግሞም፣ ‘ወደ ዶታይን እንሂድ’ ሲሉ ሰምቻቸዋለሁ” አለው።ከዚያም ዮሴፍ ወንድሞቹን ፍለጋ ሄደ፣ ዶታይን አቅራቢያም አገኛቸው።

18. ወንድሞቹም ዮሴፍ ወደ እነርሱ ሲመጣ በሩቅ አዩት፤ ወደ ነበሩበትም ስፍራ ከመድረሱ በፊት ሊገድሉት ተማከሩ።

19. እነርሱም እንዲህ ተባባሉ፤ “ያ ሕልም ዐላሚ መጣ፤

20. ኑ እንግደለውና ከጒድጓዶቹ በአንዱ ውስጥ እንጣለው፤ ከዚያም፣ ‘ክፉ አውሬ ነጥቆ በላው’ እንላለን፤ እስቲ ሕልሞቹ ሲፈጸሙ እናያለን።”

21. ሮቤል ግን ይህን ምክር ሲሰማ ከእጃቸው ሊያድነው ፈለገ እንዲህም አለ፤ “ሕይወቱ በእጃችን አትለፍ፤

22. የሰው ደም አታፍስሱ፤ እዚህ ምድረ በዳ፣ ጒድጓድ ውስጥ ጣሉት እንጂ እጃችሁን አታንሡበት።” ሮቤል ይህን ያለው ሕይወቱን ከእጃቸው አትርፎ ወደ አባቱ ሊመልሰው አስቦ ነበር።

23. ዮሴፍ ወደ ወንድሞቹ እንደ ደረሰ፣ የለበሳትን በኅብረ ቀለማት ያጌጠች እጀ ጠባቡን ገፈፉት፤

24. ይዘውም ወደ ጒድጓድ ጣሉት፤ ጒድጓዱም ውሃ የሌለበት ደረቅ ነበር።

25. ምግባቸውን ለመብላት ተቀመጡ፤ አሻግረው ሲመለከቱም ከገለዓድ የሚመጡ እስማኤላውያን ነጋዴዎች የግመል ጓዝ አዩ። ነጋዴዎቹ ሽቶ፣ በለሳን ከርቤ በግመሎቻቸው ጭነው ወደ ግብፅ የሚወርዱ ነበሩ።

26. ይሁዳም ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፤ “ወንድማችንን መግደልና አሟሟቱን መደበቅ ምን ይጠቅመናል?

27. ከዚህ ይልቅ ለእስማኤላውያን ነጋዴዎች እንሽጠው፤ እጃችንን ግን በእርሱ ላይ አናንሣ። ምንም ቢሆንኮ ወንድማችን፣ ሥጋችን ነው” ወንድሞቹም በሐሳቡ ተስማሙ።

28. የምድያም ነጋዴዎችም እነርሱ ዘንድ እንደ ደረሱ፣ ወንድሞቹ ዮሴፍን ከጒድጓድ አውጥተው ለእስማኤላውያን በሃያ ጥሬ ብር ሸጡላቸው፤ እነርሱም ዮሴፍን ወደ ግብፅ ወሰዱት።

29. ሮቤል ወደ ጒድጓዱ ተመልሶ ሲያይ፣ ዮሴፍን በማጣቱ ልብሱን በሐዘን ቀደደ።

30. ወደ ወንድሞቹም ተመልሶ፣ “ብላቴናው ጒድጓድ ውስጥ የለም፤ የት አባቴ ልሂድ?” አለ።

31. ከዚያም የዮሴፍን እጀ ጠባብ ወሰዱ፤ አንድ ፍየልም ዐርደው እጀ ጠባቡን በደሙ ነከሩት።

32. በኅብረ ቀለማት ያጌጠችውን እጀ ጠባብ ወደ አባታቸው ወስደው፣ “ይህን ወድቆ አገኘነው፤ የልጅህ እጀ ጠባብ መሆን አለመሆኑን እስቲ እየው” አሉት።

33. እርሱም ልብሱን ዐውቆት፣ “ይህማ የልጄ እጀ ጠባብ ነው!፤ ክፉ አውሬ በልቶታል፣ በእርግጥም ዮሴፍ ተቦጫጭቈአል” አለ።

34. ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅም ለብሶ ስለ ልጁ ብዙ ቀን አለቀሰ፤

35. ወንዶችና ሴቶች ልጆቹም ሁሉ ሊያጽናኑት መጡ፤ እርሱ ግን ሊጽናና ባለመቻሉ “በሐዘን እንደ ተኰራመትሁ ልጄ ወዳለበት መቃብር እወርዳለሁ” አለ። ስለ ልጁም አለቀሰ።

36. በዚህ ጊዜ፣ የምድያም ነጋዴዎች ዮሴፍን፣ ወደ ግብፅ ወስደው፣ ከፈርዖን ሹማምት አንዱ ለነበረው ለዘበኞች አለቃ፣ ለጲጥፋራ ሸጡት።