ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36
  37. 37
  38. 38
  39. 39
  40. 40
  41. 41
  42. 42
  43. 43
  44. 44
  45. 45
  46. 46
  47. 47
  48. 48
  49. 49
  50. 50

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ያዕቆብ መስጴጦምያ ደረሰ

1. ያዕቆብም ጒዞውን ቀጠለ፤ የምሥራቅም ሰዎች ወደሚኖሩበት ምድር ደረሰ።

2. እዚያም በአንድ ሜዳ ላይ ሦስት የበግ መንጋዎች ተኝተው በነበሩበት አጠገብ የውሃ ጒድጓድ አየ። የበግ መንጋዎቹ የሚጠጡት ከዚሁ ጒድጓድ ሲሆን፣ የጒድጓዱም አፍ ትልቅ የድንጋይ መክደኛ ነበረው።

3. መንጎቹ ሁሉ በጒድጓዱ አጠገብ በሚሰበሰቡበት ጊዜ፣ እረኞች ድንጋዩን ያንከባልሉና በጎቹን ውሃ ያጠጣሉ፤ ከዚያም ድንጋዩን በቦታው መልሰው የጒድጓዱን አፍ ይገጥሙታል።

4. ያዕቆብም እረኞቹን፣ “ወንድሞቼ፤ ከየት ነው የመጣችሁት?” ብሎ ጠየቃቸው።እነርሱም፣ “ከካራን ነን” አሉት።

5. እርሱም፣ “የናኮርን የልጅ ልጅ ላባን ታውቁታላችሁ?” አላቸው።እነርሱም፣ “አዎን እናውቀዋለን” አሉት።

6. ያዕቆብም፣ “ለመሆኑ ደኅና ነው?” አላቸው።እነርሱም፣ “አዎን ደኅና ነው፤ ልጁም ራሔል እነሆ፤ በጎች እየነዳች በመምጣት ላይ ነች” አሉት።

7. ያዕቆብም፣ “እንደምታዩት ጊዜው ገና ነው፤ መንጎቹ የሚገቡበት ሰዓት አይደለም፤ ታዲያ፣ ለምን በጎቹን አጠጥታችሁ ወደ ግጦሽ አትመልሷቸውም?” አላቸው።

8. እነርሱም፣ “መንጎቹ ሁሉ ተሰብስበው ድንጋዩ ከጒድጓዱ አፍ ካልተንከባለለ በስተቀር አንችልም፤ ከዚያም በጎቹን እናጠጣቸዋለን” አሉ።

9. ያዕቆብ ከእረኞቹ ጋር በመነጋገር ላይ ሳለ፣ ራሔል፣ እረኛ ነበረችና የአባቷን በጎች እየነዳች መጣች።

10. ያዕቆብ የእናቱን ወንድም የላባን ልጅ ራሔልን፣ እንዲሁም የአጎቱን የላባን በጎች ሲያይ፣ ወደ ጒድጓዱ ሄዶ ድንጋዩን ከጒድጓዱ አፍ አንከባለለ፤ የአጎቱንም በጎች አጠጣ።

11. ከዚያም ያዕቆብ ራሔልን ሳማት፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ አለቀሰ።

12. ያዕቆብም የአባቷ ዘመድና የርብቃ ልጅ መሆኑን ለራሔል ነገራት፤ እርሷም ሮጣ ሄዳ ይህንኑ ለአባቷ ነገረችው።

13. ላባም የእኅቱ ልጅ ያዕቆብ መምጣቱን እንደ ሰማ፣ ሊቀበለው ፈጥኖ ወጣ። ዐቅፎ ከሳመውም በኋላ፣ ወደ ቤቱ ይዞት ሄደ። ያዕቆብም ሁኔታውን ሁሉ ለላባ ነገረው።

14. ላባም ያዕቆብን፣ “አንተማ የዐጥንቴ ፍላጭ የሥጋዬ ቊራጭ ነህ” አለው።ያዕቆብ አንድ ወር ሙሉ አብሮት ከተቀመጠ በኋላ፣

ያዕቆብ ልያንና ራሔልን አገባ

15. ላባ ያዕቆብን፣ “ዘመዴ በመሆንህ ብቻ በነጻ ልታገለግለን አይገባምና ደመወዝህ ምንድን ነው?” አለው።

16. ላባ ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ የታላቂቱ ስም ልያ የታናሺቱ ራሔል ነበር።

17. ልያ ዐይነ ልም ስትሆን ራሔል ግን ቁመናዋ ያማረ መልኳም የተዋበ ነበር።

18. ያዕቆብም ራሔልን ስለ ወደዳት፣ “ታናሺቱ ልጅህን ራሔልን የምትድርልኝ ከሆነ ሰባት ዓመት አገለግላለሁ” አለው።

19. ላባም መልሶ፣ “ለሌላ ሰው ከምድራት ላንተ ብድራት ይሻላል፤ እዚሁ አብረኸኝ ተቀመጥ” አለው።

20. ያዕቆብም ራሔልን ለማግኘት ሲል ሰባት ዓመት አገለገለ፤ አጥብቆ ይወዳትም ስለ ነበረ፣ ሰባት ዓመት እንደ ጥቂት ቀን ሆኖ ታየው።

21. ከዚያም ያዕቆብ ላባን፣ “እነሆ፤ የተባባልነው ጊዜ አብቅቶአል፤ ስለዚህ ሚስቴን አስረክበኝና የባልና የሚስት ወጋችንን እናድርስ” አለው።

22. ስለዚህ ላባ የአካባቢውን ሰዎች በሙሉ ጠርቶ ሰርግ አበላ።

23. ሲመሽ ግን ላባ ልጁን ልያን አምጥቶ ለያዕቆብ ሰጠው፤ ያዕቆብም አብሮአት ተኛ።

24. ላባም ዘለፋ የተባለች አገልጋዩን ለልጁ ለልያ ደንገጡር እንድትሆን ሰጣት።

25. ሲነጋም እነሆ፤ ልያ ሆና ተገኘች፤ ስለዚህም ያዕቆብ ላባን፣ “ምነው፣ እንዲህ ጒድ ሠራኸኝ? ያገለገልኹህ ለራሔል ብዬ አልነበረምን? ታዲያ ለምን ታታልለኛለህ?” አለው።

26. ላባም እንዲህ አለው፤ “በአገራችን ታላቋ እያለች ታናሿን መዳር የተለመደ አይደለም፤

27. ይህን የጫጒላ ሳምንት ፈጽምና፣ ሌላ ሰባት ዓመት የምታገለግለን ከሆነ፣ ታናሺቱን ደግሞ እንሰጥሃለን።

28. ያዕቆብም በነገሩ ተስማማ፤ ከልያ ጋር ተሞሽሮ ሰባት ቀን ከቈየ በኋላ፤ ላባ ልጁን ራሔልን ለያዕቆብ ዳረለት፤

29. ባላ የተባለች አገልጋዩንም ደንገጡር እንድትሆናት ለራሔል ሰጣት።

30. ያዕቆብ ከራሔልም ጋር ተኛ፤ ራሔልን ከልያ አብልጦ ወደዳት፤ ከዚያም የተነሣ ሌላ ሰባት ዓመት ላባን አገለገለው።

31. እግዚአብሔር (ያህዌ) ልያ እንዳልተወደደች ባየ ጊዜ ማሕፀኗን ከፈተላት፤ ራሔል ግን መካን ነበረች።

32. ልያ ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) መከራዬን ስለ ተመለከተልኝ፣ ከእንግዲህ ባሌ ይወደኛል” ስትል ስሙን ሮቤል አለችው።

33. እንደ ገናም ፀንሳ ወለደች፤ እርሷም “እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳልተወደድኩ ሰምቶ ይህን ልጅ በድጋሚ ሰጠኝ” አለች። ከዚያም የተነሣ ስምዖን ብላ ጠራችው።

34. አሁንም እንደ ገና ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደች፤ እርሷም፣ ሦስት ወንዶች ልጆች ስለ ወለድሁለት “ከእንግዲህ ባሌ ያቀርበኛል” አለች፤ ስለዚህ ሌዊ ብላ ጠራችው።

35. እንደ ገና ፀንሳ አሁንም ወንድ ልጅ ወለደች፤ እርሷም፣ “እንግዲህ እግዚአብሔርን (ያህዌ) አመሰግናለሁ” አለች፤ ስሙንም ይሁዳ ብላ ጠራችው። ከዚያም በኋላ መውለድ አቆመች።