ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36
  37. 37
  38. 38
  39. 39
  40. 40
  41. 41
  42. 42
  43. 43
  44. 44
  45. 45
  46. 46
  47. 47
  48. 48
  49. 49
  50. 50

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የአብራምና የሎጥ መለያየት

1. አብራም ሚስቱንና ንብረቱን ሁሉ ይዞ ከግብፅ ወደ ኔጌብ ሄደ፤ ሎጥም አብሮት ነበረ።

2. አብራም በከብት፣ በብርና በወርቅ እጅግ በልጽጎ ነበር።

3. አብራም ከኔጌብ ተነሥቶ እስከ ቤቴል ተጓዘ፤ ቀድሞ በቤቴልና በጋይ መካከል ድንኳኑን ከተከለበት፣

4. ለመጀመሪያ ጊዜም መሠዊያ ካቆመበት ስፍራ ደረሰ፤ በዚያም የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ስም ጠራ።

5. ከአብራም ጋር አብሮት ይጓዝ የነበረው ሎጥ በጎች፣ ከብቶችና ድንኳኖች ነበሩት።

6. ሆኖም ሁለቱ አንድ ላይ ሲኖሩ ስፍራው አልበቃቸውም፤ ንብረታቸው እጅግ ብዙ ስለ ነበር፣ አብረው መኖር አልቻሉም።

7. ይህም በመሆኑ በአብራምና በሎጥ እረኞች መካከል ጠብ ተፈጠረ። በዚያን ዘመን ከነዓናውያንና ፌርዛውያን በዚያው አገር ይኖሩ ነበር።

8. አብራምም ሎጥን እንዲህ አለው፤ “እኛ ወንድማማቾች ነንና በአንተና በእኔ ወይም በእረኞቻችን መካከል ጠብ ሊኖር አይገባም።

9. ይኸው እንደምታየው አገሩ ሰፊ ነው፤ ብንለያይ ይሻላል። አንተ ግራውን ብትመርጥ፣ እኔ ወደ ቀኝ እሄዳለሁ፤ አንተ ቀኙን ብትመርጥ፣ እኔ ወደ ግራ አመራለሁ።”

10. ሎጥ ዐይኑን አቅንቶ ሲመለከት፣ የዮርዳኖስ ረባዳ ሜዳ እንደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ገነት፣ በዞዓር አቅጣጫ እንዳለው እንደ ግብፅ ምድር ውሃማ ቦታ ሆኖ አገኘው። እንዲህም የነበረው እግዚአብሔር (ያህዌ) የሰዶምንና የገሞራን ከተሞች ከማጥፋቱ በፊት ነው።

11. ሎጥ የዮርዳኖስን ረባዳ ሜዳ በሙሉ መርጦ ወደ ምሥራቅ አመራ፤ ሁለቱ ሰዎች በዚሁ ተለያዩ።

12. አብራም መኖሪያውን በከነዓን ምድር አደረገ፤ ሎጥ ግን በረባዳው ሜዳ ውስጥ ባሉት ከተሞች መካከል በሰዶም አቅራቢያ ድንኳኑን ተከለ።

13. የሰዶም ሰዎች ግን ክፉዎችና በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት እጅግ ኃጥኣን ነበሩ።

14. ሎጥ ከተለየው በኋላ እግዚአብሔር (ያህዌ) አብራምን እንዲህ አለው፤ ካለህበት ስፍራ ቀና ብለህ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ፣ ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ ተመልከት፤

15. ዐይንህ የሚያየውን ምድር ሁሉ ለአንተና ለዘርህ ለዘላለም እሰጣለሁ።

16. ዘርህን እንደ ምድር ትቢያ አበዛዋለሁ፤ ማንም የምድርን ትቢያ ሊቈጥር እንደማይችል ሁሉ የአንተም ዘር የማይቈጠር ይሆናል።

17. እንግዲህ ምድሪቱን ስለምሰጥህ ተነሣ፤ በርዝመቷም፣ በስፋቷም ተመላለስባት።”

18. አብራምም ድንኳኑን ነቀለ፤ ሄዶም ኬብሮን በሚገኙት ትልልቅ የመምሬ ዛፎች አጠገብ ተቀመጠ፤ በዚያም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሠዊያ ሠራ።