ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36
  37. 37
  38. 38
  39. 39
  40. 40
  41. 41
  42. 42
  43. 43
  44. 44
  45. 45
  46. 46
  47. 47
  48. 48
  49. 49
  50. 50

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 38 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ይሁዳና ትዕማር

1. በዚያም ወራት ይሁዳ ከወንድሞቹ ተለይቶ፣ ኤራስ ወደተባለ ዓዶሎማዊ ሰው ወረደ፤ እርሱም ዘንድ ለመኖር ቤቱ ገባ።

2. እዚያም ሳለ፣ ይሁዳ የከነዓናዊውን የሴዋን ሴት ልጅ አየ፤ እርሷንም አግብቶ አብሯት ተኛ፤

3. እርሷም ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙም ዔር ተባለ።

4. እንደ ገናም ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙን አውናን አለችው።

5. አሁንም ደግማ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሴሎም ብላ አወጣችለት፤ እርሱንም የወለደችው ክዚብ በተባለ ቦታ ነበር።

6. ይሁዳ የበኵር ልጁን ዔርን፣ ትዕማር የምትባል ሚስት አጋባው።

7. የይሁዳ የበኵር ልጅ ዔር ግን በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ፊት ክፉ ነበር፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ቀሠፈው።

8. በዚህ ጊዜ ይሁዳ አውናንን፣ “ዋርሳዋ እንደ መሆንህ ከወንድምህ ሚስት ጋር ሩካቤ ሥጋ በመፈጸም የወንድምህን ስም የሚያስጠራለት ዘር ተካለት” አለው።

9. አውናን ግን የሚወለደው ልጅ የእርሱን ስም የሚያስጠራ እንደማይሆን ስላወቀ፣ ከወንድሙ ሚስት ጋር ሩካቤ ሥጋ በፈጸመ ቍጥር የወንድሙንም ስም የሚያስጠራ ልጅ እንዳይወልድ ዘሩን በምድር ላይ ያፈስ ነበር።

10. ይህም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ክፉ አድራጎት ሆኖ ስለ ተገኘ፣ እርሱንም እግዚአብሔር (ያህዌ) በሞት ቀሠፈው።

11. ከዚያም ይሁዳ ምራቱን ትዕማርን፣ “ልጄ ሴሎም ለአካለ መጠን እስኪደርስ ድረስ ወደ አባትሽ ቤት ሄደሽ መበለት ሆነሽ ብትኖሪ ይሻላል” አላት፤ ይህን ያለውም፣ ሴሎም እንደ ወንድሞቹ ተቀሥፎ ይሞትብኛል ብሎ ስለሠጋ ነበር። ትዕማርም እንዳላት ሄደች፤ በአባቷም ቤት ተቀመጠች።

12. ከብዙ ጊዜ በኋላ የሹዓ ልጅ፣ የይሁዳ ሚስት ሞተች። ይሁዳ ከሐዘኑ ከተጽናና በኋላ ከዓዶላማዊው ከሒራ ጋር የበጎቹን ጠጒር የሚሸልቱ ሰዎች ወዳሉበት ወደ ተምና ሄደ።

13. ሰዎቹም ለትዕማር፣ “ዐማትሽ የበጎቹን ጠጒር ወደሚሸልቱ ሰዎች ዘንድ ወደ ተምና እየሄደ ነው” አሏት። ይህን እንደ ሰማች

14. የመበለትነት ልብሷን አውልቃ፣ ማንነቷ እንዳይታወቅ ፊቷን በሻሽ ተከናንባ ወደ ተምና በሚወስደው መንገድ ዳር ባለች ኤናይም በተባለች ከተማ መግቢያ ላይ ተቀመጠች፤ ይህን ያደረገችው፣ ሴሎም ለአካለ መጠን ቢደርስም፣ እርሷን እንዲያገባ አባቱ አለመፈለጉን ስላወቀች ነው።

15. ፊቷ በሻሽ ተሸፋፍኖ ሲያያት፣ ይሁዳ ዝሙት ዐዳሪ መሰለችው።

16. ምራቱ መሆኗን ባለማወቁ፣ እርሷ ወዳለችበት ወደ መንደሩ ዳር ጠጋ ብሎ፣ “እባክሽ አብሬሽ ልተኛ” አላት። እርሷም፣ “አብሬህ ብተኛ ምን ትሰጠኛለህ?” ብላ ጠየቀችው።

17. “ከመንጋዬ መካከል አንድ የፍየል ጠቦት እልክልሻለሁ” አላት። እርሷም መልሳ፣ “ጠቦቱን እስክትልክልኝ ድረስ ምን መያዣ ትሰጠኛለህ?” ብላ ጠየቀችው።

18. “ታዲያ ምን መያዣ ልስጥሽ?” አላት። እርሷም፣ “የማኅተም ቀለበትህን ከነማሰሪያው፣ እንደዚሁም ይህን በትርህን ስጠኝ” አለችው። የጠየቀችውን ሁሉ ሰጣትና አብሯት ተኛ፤ እርሷም ፀነሰች።

19. ከዚያም ወደ መኖሪያዋ ተመልሳ፣ ሻሽዋን አውልቃ እንደ ወትሮዋ የመበለት ልብሷን ለበሰች።

20. ይሁዳ በመያዣ ስም የሰጣትን ዕቃዎች ለማስመለስ የፍየሉን ጠቦት በዓዶሎማዊ ወዳጁ እጅ ላከላት፣ መልእክተኛው ግን ሴትየዋን ሊያገኛት አልቻለም።

21. “በኤናይም ከተማ መግቢያ ከመንገዱ ዳር የነበረች ያቺ ዝሙት ዐዳሪ የት ደረሰች?” ሲል ጠየቃቸው። ሰዎቹም፣ “በዚህ አካባቢ ኧረ ምንም ዝሙት ዐዳሪ ታይታ አትታወቅም” አሉት።

22. መልእክተኛውም ወደ ይሁዳ ተመልሶ፣ “ሴቲቱን ላገኛት አልቻልኩም፤ ነዋሪዎቹም ‘በዚህ አካባቢ እንደዚህች ያለች ዝሙት ዐዳሪ የለችም’ አሉኝ” ብሎ ነገረው።

23. ይሁዳም፣ “እንግዲህ መያዣውን እንደ ያዘች ትቅር፤ አለዚያ መሣቂያ እንሆናለን። ለነገሩማ ይህን ፍየል ላክሁ፤ አንተም ፈልገህ አላገኘሃትም” አለ።

24. ከሦስት ወር ያህል በኋላ፣ “ምራትህ ትዕማር ዘማዊ ሆናለች፤ ከዚህም የተነሣ አርግዛለች” ተብሎ ለይሁዳ ተነገረው።ይሁዳም፣ “አውጧትና በእሳት ተቃጥላ ትሙት” አለ።

25. እርሷም ተይዛ በምትወሰድበት ጊዜ ለዐማትዋ፣ “እኔ ያረገዝሁት የእነዚህ ዕቃዎች ባለቤት ከሆነ ሰው ነው” ስትል ላከችበት፤ ደግሞም፣ “የማኅተሙ ቀለበት ከነማንጠልጠያውና በትሩ የማን እንደሆነ እስቲ ተመልከት” አለችው።

26. ይሁዳም ዕቃዎቹን ዐውቆ፣ “ልጄ ሴሎም እንዲያገባት ባለማድረጌ፣ እርሷ ከእኔ ይልቅ ትክክል ናት” አለ። ከዚያም በኋላ ከእርሷ ጋር አልተኛም።

27. የመውለጃዋ ጊዜ እንደ ደረሰም ፅንሷ መንታ መሆኑ ታወቀ።

28. በምትወልድበትም ጊዜ አንደኛው እጁን አወጣ፤ አዋላጂቱም፣ “ይህኛው መጀመሪያ ወጣ” ስትል በእጁ ላይ ቀይ ክር አሰረችለት፤

29. ነገር ግን፣ እጁን መልሶ ሲያስገባ ወንድሙ ተወለደ። አዋላጂቱም “አንተ እንዴት ጥሰህ ወጣህ!” አለች፤ ከዚያም ስሙ ፋሬስ ተባለ።

30. ከዚያ በኋላ እጁ ላይ ቀይ ክር የታሰረለት ወንድሙ ተወለደ፣ ስሙም ዛራ ተባለ።