ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36
  37. 37
  38. 38
  39. 39
  40. 40
  41. 41
  42. 42
  43. 43
  44. 44
  45. 45
  46. 46
  47. 47
  48. 48
  49. 49
  50. 50

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 34 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የያዕቆብ ልጅ ተደፈረች

1. ልያ ለያዕቆብ የወለደችለት ሴት ልጅ ዲና፣ አንድ ቀን የዚያን አገር ሴቶች ለማየት ወጣች።

2. ሴኬም የተባለው የአገሩ ገዢ የኤዊያዊ የኤሞር ልጅ ባያት ጊዜ ይዞ በማስገደድ ደፈራት።

3. ልቡ በያዕቆብ ልጅ በዲና ተማረከ፤ ልጂቷንም በጣም ወደዳት፤ በጣፈጠም አንደበት አናገራት።

4. ሴኬምም አባቱን ኤሞርን፣ “ይህችን ልጅ አጋባኝ” አለው።

5. ያዕቆብ፣ ልጁን ዲናን ሴኬም እንዳስነ ወራት ሰማ፤ በዚህ ጊዜ ወንዶች ልጆቹ ከብቶቹን በመስክ ያግዱ ነበር፤ ያዕቆብም ልጆቹ እስኪመለሱ ድረስ ታግሦ ቈየ።

6. ከዚያም የሴኬም አባት ኤሞር፣ ያዕቆብን ሊያነጋግረው ወጣ።

7. የያዕቆብ ወንዶች ልጆችም የተፈጸመውን ድርጊት እንደ ሰሙ ወዲያውኑ ከመስክ መጡ፤ ሴኬም መደረግ የማይገባውን አስነዋሪ ነገር በእስራኤል ላይ በመፈጸም፣ የያቆብን ልጅ ስለደፈረ ዐዘኑ፤ ክፉኛም ተቈጡ።

8. ኤሞር ግን እንዲህ አላቸው፤ “ልጄ ሴኬም ልቡ በልጃችሁ ፍቅር ተነድፎአል፤ እባካችሁ እንዲያገባት ፍቀዱለት።

9. በጋብቻ እንተሳሰር፣ ሴት ልጃችሁን ስጡን፣ የእኛንም ሴቶች አግቡ።

10. አብራችሁንም መኖር ትችላላችሁ፤ አገራችን አገራችሁ ናት፤ ኑሩባት፤ ነግዱባት፤ ሀብት ንብረትም አፍሩባት።”

11. ሴኬም ደግሞ የዲናን አባትና ወንድሞቿን እንዲህ አላቸው፤ “በእናንተ ዘንድ ሞገስ ላግኝ እንጂ የተጠየቅሁትን ሁሉ እሰጣለሁ፤

12. ጥሎሽ ብትሉኝ ጥሎሽ፣ ስጦታ ብትሉም የፈለጋችሁትን ያህል እሰጣለሁ፣ ብቻ ልጂቱን እንዳገባ ፍቀዱልኝ።”

13. የያዕቆብ ወንዶች ልጆችም፣ በእኅታቸው በዲና ላይ ስለ ተፈጸመው ነውር፣ የሆዳቸውን በሆዳቸው ይዘው፣ ለሴኬምና ለአባቱ ለኤሞር መልስ ሰጡ፤

14. እንዲህም አሉአቸው፤ “እኅታችንን ላልተገረዘ ሰው ብንሰጥ ውርደት ስለሚሆንብን፣ እንዲህ ያለውን ነገር አናደርገውም።

15. ሆኖም የምንስማማበት አንድ መንገድ ብቻ አለ፤ ይህም ወንዶቻችሁን ሁሉ ገርዛችሁ እኛን የመሰላችሁ እንደሆነ ነው።

16. ከዚያ በኋላ ሴቶች ልጆቻችንን እንድርላችኋለን፤ አብረን እንኖራለን፤ አንድ ሕዝብም እንሆናለን።

17. በመገረዙ የማትስማሙ ከሆነ ግን ልጃችንን ይዘን እንሄዳለን።”

18. ያቀረቡትም ሐሳብ ለኤሞርና ለልጁ ለሴኬም መልካም መስሎ ታያቸው።

19. ከአባቱ ቤተ ሰብ ሁሉ እጅግ የተከበረው ይህ ወጣት የያዕቆብን ልጅ እጅግ ወዶአት ስለ ነበር፣ ያሉትን ለማድረግ ጊዜ አልወሰደበትም።

20. ስለዚህ ኤሞርና ልጁ ሴኬም ይህንኑ ለወገኖቻቸው ለመንገር ወደ ከተማቸው በር ሄዱ፤

21. እንዲህም አሏቸው፤ “እነዚህ ሰዎች ወዳጆቻችን ናቸው፤ በአገራችን እንዲኖሩ፣ ተዘዋውረውም እንዲነግዱ እንፍቀድላቸው፤ ምድሪቱ እንደሆን ለእኛም ለእነርሱም ትበቃለች። ሴቶች ልጆቻቸውን እናገባለን፤ እነርሱም የእኛን ሴቶች ያገባሉ።

22. ሆኖም ሰዎቹ ከእኛ ጋር እንደ አንድ ሕዝብ ሆነው አብረውን ለመኖር ፈቃደኞች የሚሆኑት፣ የእኛ ወንዶች እንደ እነርሱ የተገረዙ እንደሆነ ብቻ ነው።

23. ታዲያ እንዲህ ብናደርግ ከብታቸው ንብረታቸው፣ እንስሶቻቸው ሁሉ የእኛው ይሆኑ የለምን? ስለዚህ ባሉት እንስማማ፤ እነርሱም አብረውን ይኑሩ።”

24. ከከተማዪቱ በር ውጪ የተሰበሰቡት ሁሉ በኤሞርና በልጁ በሴኬም ሐሳብ ተስማሙ፤ በከተማዪቱም ያሉት ወንዶች ሁሉ ተገረዙ።

25. በሦስተኛውም ቀን የሁሉም ቍስል ገና ትኵስ ሳለ ከያዕቆብ ልጆች ሁለቱ፣ የዲና ወንድሞች ስምዖንና ሌዊ፣ ሰይፋቸውን መዘው ሳይታሰብ ወደ ከተማዪቱ ገብተው ወንዶቹን በሙሉ ገደሏቸው።

26. ኤሞርንና ሴኬምንም በሰይፍ ገድለው፣ እኅታቸውን ዲናን ከሴኬም ቤት አውጥተው ይዘዋት ተመለሱ።

27. የያዕቆብ ልጆች ሁሉ በሬሳ ላይ እየተረማመዱ እኅታቸው የተደፈረችበትን ከተማ ዘረፉ።

28. የበግና የፍየል መንጎቻቸውን፣ ከብቶቻቸውንና አህዮቻቸውን እንዲሁም በከተማዪቱና በአካባቢው የሚገኘውን ንብረታቸውን ሁሉ ወሰዱባቸው፤

29. ሀብታቸውን ሁሉ ዘርፈው ሴቶቻቸውንና ሕፃኖቻቸውን ሁሉ ማርከው በየቤቱ ያገኙትን ሁሉ ይዘው ሄዱ።

30. ያዕቆብም ስምዖንና ሌዊን እንዲህ አላቸው፤ “በዚህ አገር በሚኖሩት በከነዓናውያንና በፌርዛውያን ዘንድ እንደ ጥምብ አስቈጠራችሁኝ፣ ጭንቀትም እንዲደርስብኝ አድርጋችኋል። እኛ በቍጥር አነስተኞች ነን፤ ተባብረው ቢነሡብኝና ቢያጠቁኝ እኔና ቤተ ሰቤ መጥፋታችን አይደለምን?”

31. እነርሱ ግን፣ “ታዲያ፤ እኅታችንን እንደ ዝሙት አዳሪ ይድፈራት?” አሉት።