ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 7 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የመቶ አለቃው እምነት

1. ኢየሱስ ይህን ሁሉ በሕዝቡ ፊት ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ገባ።

2. በዚያም አንድ የመቶ አለቃ ነበረ፤ እጅግ የሚወደው አገልጋዩም ታሞበት ለሞት ተቃርቦ ነበር።

3. እርሱም ስለ ኢየሱስ በሰማ ጊዜ አገልጋዩን እንዲፈውስለት ይለምኑት ዘንድ አንዳንድ የአይሁድ ሽማግሌዎችን ላከበት።

4. መልእክተኞቹም ወደ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ እንዲህ ብለው አጥብቀው ለመኑት፤ “ይህን ልታደርግለት ይገባዋል፤

5. ምክንያቱም ይህ ሰው ሕዝባችንን ይወዳል፤ ምኵራባችንንም ያሠራልን እርሱ ነው።”

6. ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ሄደ።እርሱም ወደ ቤቱ በተቃረበ ጊዜ፣ የመቶ አለቃው ወዳጆቹን ልኮ እንዲህ አለው፤ “ጌታ ሆይ፤ ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ የሚገባኝ ሰው አይደለሁምና አትድከም፤

7. ከዚህም የተነሣ በአንተ ፊት ለመቅረብ እንኳ እንደሚገባኝ ራሴን አልቈጠርሁም፤ ብቻ አንድ ቃል ተናገር፤ አገልጋዬ ይፈወሳል።

8. እኔ ራሴ የበላይ አለቃ አለኝ፤ ከበታቼም የማዛቸው ወታደሮች አሉኝ፤ አንዱን፣ ‘ሂድ’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውን፣ ‘ና’ ስለው ይመጣል፤ አገልጋዬንም፣ ‘ይህን አድርግ’ ስለው የታዘዘውን ያደርጋል።”

9. ኢየሱስም ይህን ሲሰማ በእርሱ ተደነቀ፤ ዘወር ብሎም ይከተለው ለነበረው ሕዝብ፣ “እላችኋለሁ፤ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት በእስራኤል እንኳ አላገኘሁም” አላቸው።

10. የተላኩት ሰዎችም ወደ ቤት በተመለሱ ጊዜ፣ አገልጋዩን ድኖ አገኙት።

ኢየሱስ የመበለቲቱን ልጅ ከሞት አስነሣው

11. ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ብዙ ሳይቈይ፣ ናይን ወደምትባል ከተማ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱና ብዙ ሕዝብም አብረውት ሄዱ።

12. ወደ ከተማዋ መግቢያ በር ሲደርስም፣ እነሆ፤ ሰዎች የአንድ ሰው አስከሬን ተሸክመው ከከተማዋ ወጡ፤ ሟቹም ለእናቱ አንድ ልጅ ብቻ ነበር፤ እናቱም መበለት ነበረች፤ ብዙ የከተማውም ሕዝብ ከእርሷ ጋር ነበረ።

13. ጌታም ባያት ጊዜ ራራላትና፣ “አይዞሽ፤ አታልቅሺ” አላት።

14. ቀረብ ብሎም ቃሬዛውን ነካ፤ የተሸከሙትም ሰዎች ቀጥ ብለው ቆሙ፤ ኢየሱስም፣ “አንተ ጐበዝ፤ ተነሥ እልሃለሁ” አለው።

15. የሞተውም ሰው ቀና ብሎ ተቀመጠ፤ መናገርም ጀመረ። ኢየሱስም ወስዶ ለእናቱ ሰጣት።

16. ሁሉም በፍርሀት ተውጠው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ፣ “ታላቅ ነቢይ በመካከላችን ተነሥቶአል፤ እግዚአብሔርም ሕዝቡን ጐብኝቶአል” አሉ።

17. ይህም የኢየሱስ ዝና በመላው ይሁዳና በአካባቢው ባለው አገር ሁሉ ወጣ።

ኢየሱስና መጥምቁ ዮሐንስ

18. የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም ይህንን ሁሉ ለዮሐንስ ነገሩት። እርሱም ከመካከላቸው ሁለቱን ጠርቶ፣

19. “ይመጣል የተባለልህ አንተ ነህ? ወይስ ሌላ እንጠብቅ? በሉት” ብሎ ወደ ጌታ ላካቸው።

20. ሰዎቹም ወደ ኢየሱስ መጥተው፣ “መጥምቁ ዮሐንስ፣ ‘ይመጣል የተባለልህ አንተ ነህ? ወይስ ሌላ እንጠብቅ? ብሎ ወደ አንተ ልኮናል’ አሉት።

21. በዚያኑ ጊዜ ኢየሱስ ብዙ ሰዎችን ከበሽታ፣ ከደዌና ከርኩሳን መናፍስት ፈወሳቸው፤ የብዙ ዐይነ ስውራንንም ዐይን አበራ።

22. ከዮሐንስ ተልከው የመጡትንም እንዲህ አላቸው፤ “ሄዳችሁ ያያችሁትንና የሰማችሁትን ለዮሐንስ ንገሩት፤ ዐይነ ስውራን ያያሉ፤ ዐንካሶች በትክክል ይራመዳሉ፤ ለምጻሞች ነጽተዋል፤ ደንቈሮዎች ይሰማሉ፤ ሙታን ተነሥተዋል፤ ለድኾችም ወንጌል ይሰበካል፤

23. በእኔ የማይሰናከል ሰው ሁሉ የተባረከ ነው።”

24. የዮሐንስ መልእክተኞች ከሄዱ በኋላ፣ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ይናገር ጀመር፤ እንዲህም አለ፤ “ወደ በረሓ የወጣችሁት ምን ልታዩ ነው? ነፋስ የሚያወዛውዘውን ሸምበቆ?

25. እኮ! ምን ልታዩ ወጣችሁ? ያማረ ልብስ የለበሰውን ሰው ነውን? ባማረ ልብስ የሚሽሞነሞኑና በድሎት የሚኖሩ በቤተ መንግሥት አሉላችሁ።

26. እኮ! ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን ለማየት ይሆን? አዎን፣ እላችኋለሁ፤ ለማየት የወጣችሁት ከነቢይም የሚበልጠውን ነው።

27. እንዲህ ተብሎ የተጻፈለትም እርሱ ነው፤ “ ‘መንገድህን በፊትህ የሚያስተካክል፣ መልእክተኛዬን ከአንተ አስቀድሜ እልካለሁ።’

28. እላችኋለሁ፤ ከሴት ከተወለዱት መካከል ከዮሐንስ የሚበልጥ የለም፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል።”

29. ቀረጥ ሰብሳቢዎች እንኳ ሳይቀሩ፣ ይህን የሰሙ ሁሉ፣ የዮሐንስን ጥምቀት በመጠመቅ ለእግዚአብሔር ተገቢውን ክብር ሰጡት፤

30. ፈሪሳውያንና ሕግ ዐዋቂዎች ግን በዮሐንስ እጅ ባለ መጠመቃቸው፣ እግዚአብሔር ለእነርሱ ያለውን ዐላማ አቃለሉ።

31. ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ የዚህን ትውልድ ሰዎች በምን ልመስላቸው? ምንስ ይመስላሉ?

32. በገበያ ቦታ ተቀምጠው እርስ በርሳቸው እየተጠራሩ እንዲህ የሚባባሉ ልጆችን ይመስላሉ፤ “ ‘ዋሽንት ነፋንላችሁ፤ አልጨፈራችሁም፤ ሙሾ አወረድንላችሁ፤ አላለቀሳችሁም።’

33. ምክንያቱም መጥምቁ ዮሐንስ እህል ሳይ በላና የወይን ጠጅ ሳይጠጣ ቢመጣ፣ ጋኔን አለበት አላችሁት፤

34. የሰው ልጅ ደግሞ እየበላና እየጠጣ ቢመጣ፣ ‘በላተኛና ጠጪ፣ የቀረጥ ሰብሳቢዎችና “የኀጢአተኞች” ወዳጅ’ አላችሁት።

35. እንግዲህ የጥበብ ትክክለኛነት በልጆቿ ሁሉ ዘንድ ተረጋገጠ።”

አንዲት ሴት ኢየሱስን ሽቶ ቀባች

36. ከዚህ በኋላ ከፈሪሳውያን አንዱ ምግብ አብሮት እንዲበላ ኢየሱስን ጋበዘው፤ እርሱም ወደ ፈሪሳዊው ቤት ሄዶ በማእድ ተቀመጠ።

37. በዚያ ከተማ የምትኖር አንዲት ኀጢአተኛ ሴት፣ ኢየሱስ በፈሪሳዊው ቤት በማእድ መቀመጡን በሰማች ጊዜ አንድ የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ሽቶ ይዛ መጣች፤

38. ከበስተ ኋላው እግሩ አጠገብ ቆማ እያለቀሰች እግሩን በእንባዋ ታርስ፣ በራሷም ጠጒር ታብሰው ጀመር፤ እግሩንም እየሳመች ሽቱውን ቀባችው።

39. የጋበዘውም ፈሪሳዊ ይህን ባየ ጊዜ፣ “ይህ ሰው ነቢይ ቢሆን ኖሮ፣ የነካችው ሴት ማን እንደሆነች፣ ደግሞም ምን ዐይነት ሰው እንደሆነች ባወቀ ነበር፤ ኀጢአተኛ ናትና” ብሎ በልቡ አሰበ።

40. ኢየሱስም፣ “ስምዖን ሆይ፤ የምነግርህ ነገር አለኝ” አለው።እርሱም፣ “መምህር ሆይ፤ ንገረኝ” አለው።

41. ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “ከአንድ አበዳሪ ገንዘብ የተበደሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ አንደኛው አምስት መቶ ዲናር፣ ሁለተኛው ደግሞ አምሳ ዲናር ነበረበት።

42. የሚከፍሉትም ቢያጡ ዕዳቸውን ለሁለቱም ተወላቸው። እንግዲህ ከሁለቱ አበዳሪውን አብልጦ የሚወደው የትኛው ነው?”

43. ስምዖንም፣ “ብዙው ዕዳ የተተወለት ይመስለኛል” ሲል መለሰ።ኢየሱስም፣ “ትክክል ፈርደሃል” አለው።

44. ወደ ሴቲቱም ዘወር ብሎ ስምዖንን እንዲህ አለው፤ “ይህቺን ሴት ታያታለህን? እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ፤ አንተ ለእግሬ ውሃ እንኳ አላቀረብህልኝም፤ እርሷ ግን እግሬን በእንባዋ እያራሰች በጠጒሯ አበሰች።

45. አንተ ከቶ አልሳምኸኝም፤ እርሷ ግን ከገባሁ ጀምራ እግሬን ከመሳም አላቋረጠችም።

46. አንተ ራሴን ዘይት አልቀባህም፤ እርሷ ግን እግሬን ሽቶ ቀባች።

47. ስለዚህ እልሃለሁ፤ እጅግ ወዳለችና ብዙው ኀጢአቷ ተሰርዮላታል፤ በትንሹ የተሰረየለት ግን የሚወደው በትንሹ ነው።”

48. ኢየሱስም ሴቲቱን፣ “ኀጢአትሽ ተሰርዮልሻል” አላት።

49. አብረውት በማእድ ተቀምጠው የነበሩ እንግዶችም፣ “ይህ ኀጢአትን እንኳ የሚያስተስረይ እርሱ ማን ነው?” ብለው በልባቸው አሰቡ።

50. ኢየሱስም ሴቲቱን፣ “እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ” አላት።