ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኀጢአት፣ እምነት፣ ኀላፊነት

1. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፤ “ሰዎችን የሚያሰናክል መምጣቱ አይቀርም፤ ነገር ግን ለመሰናክሉ መምጣት ምክንያት ለሚሆን ለዚያ ሰው ወዮለት።

2. ይህ ሰው ከእነዚህ ከታናናሾች አንዱን ከሚያሰናክል፣ የወፍጮ ድንጋይ በዐንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለው ነበር።

3. ስለዚህ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። “ወንድምህ ቢበድል ገሥጸው፤ ቢጸጸት ይቅር በለው።

4. በቀን ሰባት ጊዜ ቢበድልህና ሰባት ጊዜ፣ ‘ተጸጽቻለሁ’ እያለ ወደ አንተ ቢመለስ ይቅር በለው።”

5. ሐዋርያትም ጌታን፣ “እምነታችንን ጨምርልን” አሉት።

6. ጌታም፣ “የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል እምነት ቢኖራችሁ፣ ይህን ሾላ፣ ‘ተነቅለህ ባሕር ውስጥ ተተከል’ ብትሉት ይታዘዝላችኋል” አላቸው።

7. ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “ከእናንተ መካከል አንድ ሰው ዐራሽ ወይም በግ ጠባቂ የሆነ አገልጋይ ቢኖረው፣ ከዕርሻ የተመለሰውን አገልጋዩን፣ ‘ቶሎ ወደ ማእድ ቅረብ’ ይለዋልን?

8. ከዚህ ይልቅ፣ ‘እራቴን እንድበላ አዘጋጅልኝ፣ እኔ እስክበላና እስክ ጠጣ ድረስ ታጥቀህ አገልግለኝ፤ ከዚያ በኋላ አንተ ደግሞ ትበላለህ፤ ትጠጣለህ’ አይለው ምን?

9. እንግዲህ ይህ ሰው፣ አገልጋዩ የታዘዘውን በመፈጸሙ መልሶ ያመሰግነዋልን?

10. ስለዚህ እናንተም የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ፣ ‘ከቊጥር የማንገባ አገልጋዮች ነን፤ ልናደርገው የሚገባንን ተግባር ፈጽመናል በሉ።”

ከለምጽ የነጹ ዐሥር ሰዎች

11. ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ፣ በሰማርያና በገሊላ ድንበር በኵል ዐለፈ፤

12. ወደ አንድ መንደር እንደ ገባም ለምጽ የያዛቸው ዐሥር ሰዎች አገኙት፤ እነርሱም በርቀት ቆመው፣

13. በታላቅ ድምፅ፣ “ኢየሱስ፤ ጌታ ሆይ፤ ራራልን!” አሉት።

14. እርሱም ባያቸው ጊዜ፣ “ሂዱና ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ” አላቸው። እነርሱም ወደዚያው በመሄድ ላይ ሳሉ ነጹ።

15. ከእነርሱም አንዱ መፈወሱን ባየ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ፤

16. በኢየሱስም እግር ላይ በፊቱ ተደፍቶ አመሰገነው፤ ይህም ሰው ሳምራዊ ነበረ።

17. ኢየሱስም እንዲህ ሲል ጠየቀው፤ “የነጹት ዐሥር ሰዎች አልነበሩምን? ታዲያ፣ ዘጠኙ የት ደረሱ?

18. ከዚህ ከባዕድ ሰው በስተቀር ተመልሰው እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ የሉም ማለት ነውን?”።

19. ሰውየውንም፣ “ተነሥተህ ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል” አለው።

የእግዚአብሔር መንግሥት መምጣት

20. ፈሪሳውያን የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ እንደምትመጣ ኢየሱስን በጠየቁት ጊዜ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት በሚታዩ ምልክቶች አትመጣም፤

21. ሰዎችም፣ ‘እዚህ ነው’ ወይም ‘እዚያ ነው’ ማለት አይችሉም፤ እነሆ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና።”

22. ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አላቸው፤ “ከሰው ልጅ ቀኖች አንዱን ለማየት የምትመኙበት ጊዜ ይመጣል፤ ደግሞም አታዩትም።

23. ሰዎች፣ ‘እዚያ ነው’ ወይም ‘እዚህ ነው’ ይሏችኋል፤ ተከትላችኋቸውም አትሂዱ፤

24. ምክንያቱም መብረቅ በርቆ ሰማዩን ከዳር እስከ ዳር እንደሚያበራ፣ የሰው ልጅም በሚመጣበት ቀን ልክ እንደዚሁ ይሆናል።

25. ነገር ግን ይህ ከመሆኑ በፊት የሰው ልጅ ብዙ መሠቃየትና በዚህም ትውልድ መናቅ ይኖርበታል።

26. “በኖኅ ዘመን እንደሆነው ሁሉ፣ በሰው ልጅ ዘመንም እንደዚሁ ይሆናል።

27. ኖኅ ወደ መርከቡ እስከገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ይበሉና ይጠጡ፣ ያገቡና ይጋቡ ነበር፤ የጥፋትም ውሃ መጥቶ ሁሉንም አጠፋቸው።

28. “በሎጥ ዘመንም እንዲሁ ነበር፤ ሰዎች ይበሉና ይጠጡ፣ ይገዙና ይሸጡ፣ ተክል ይተክሉና ቤት ይሠሩ ነበር፤

29. ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ዕለት ግን እሳትና ዲን ከሰማይ ዘንቦ በሙሉ አጠፋቸው።

30. “የሰው ልጅ በሚገለጥበትም ቀን እንደዚሁ ይሆናል።

31. በዚያን ቀን በቤቱ ጣራ ላይ ያለ ማንም ሰው በቤቱ ውስጥ ያለውን ንብረት ለመውሰድ አይውረድ፤ እንዲሁም በዕርሻ ቦታ ያለ ሰው ወደ ኋላው አይመለስ።

32. የሎጥን ሚስት አስታውሱ።

33. ሕይወቱን ለማሰንበት የሚፈልግ ሁሉ ያጣታል፤ ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ግን ያቈያታል።

34. እላችኋለሁ፤ በዚያች ሌሊት ሁለት ሰዎች በአንድ ዐልጋ ይተኛሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው ይቀራል።

35. ሁለት ሴቶች አብረው ይፈጫሉ፤ አንዷ ትወሰዳለች፤ ሌላዋ ትቀራለች።

36. ሁለት ሰዎች በዕርሻ ቦታ አብረው ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው ይቀራል።”

37. እነርሱም መልሰው፣ “ጌታ ሆይ፤ የሚወሰዱት ወዴት ነው?” አሉት።እርሱም፣ “ጥንብ ባለበት አሞሮች ይሰበሰባሉ” አላቸው።