ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 2 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የኢየሱስ መወለድ

1. በዚያን ዘመን፣ የዓለሙ ሁሉ ሕዝብ እንዲቈጠርና እንዲመዘገብ ከአውግስጦስ ቄሳር ትእዛዝ ወጣ።

2. ይህም ቄሬኔዎስ የሶርያ ገዢ በነበረበት ጊዜ የተደረገ የመጀመሪያው የሕዝብ ቈጠራ ነበር።

3. ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው ለመመዝገብ ወደየራሱ ከተማ ሄደ።

4. ዮሴፍም ከዳዊት ቤትና ወገን ስለ ነበረ፣ በገሊላ አውራጃ ከምትገኘው ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ የዳዊት ከተማ ወደሆነችው፣ ቤተ ልሔም ወደምትባል ከተማ ወደ ይሁዳ ወጣ።

5. ወደዚያም ለመመዝገብ የተጓዘው፣ የመውለጃ ጊዜዋ ከተቃረበው ከእጮኛው ከማርያም ጋር ነበር።

6. በዚያም እንዳሉ የምትወልድበት ጊዜ ደረሰ፤

7. የበኵር ልጇ የሆነውን ወንድ ልጅ ወለደች፤ በጨርቅም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማረፊያ ቦታ ስላላገኙ በግርግም አስተኛችው።

እረኞችና መላእክት

8. በዚያው አገር በሌሊት መንጋቸውን ሲጠብቁ በሜዳ የሚያድሩ እረኞች ነበሩ።

9. የጌታም መልአክ ድንገት መጥቶ በአጠገባቸው ቆመ፤ የጌታም ክብር በዙሪያቸው አበራ፤ ታላቅም ፍርሀት ያዛቸው።

10. መልአኩ ግን እንዲህ አላቸው፤ “አትፍሩ፤ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች አምጥቼላችኋለሁና።

11. ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኀን ተወልዶላችኋልና፤ እርሱም ጌታ ክርስቶስ ነው።

12. ይህ ምልክት ይሁናችሁ፤ ሕፃን ልጅ በጨርቅ ተጠቅልሎ በግርግም ተኝቶ ታገኛላችሁ።”

13. ድንገትም ብዙ የሰማይ ሰራዊት ከመልአኩ ጋር ታዩ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፣ እንዲህ አሉ፤

14. “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም፣ ሰላምም እርሱለሚወዳቸው ሰዎች በምድር ይሁን!”

15. መላእክቱ ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ ከወጡ በኋላ እረኞቹ፣ “ጌታ የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንድናይ ወደ ቤተ ልሔም እንሂድ” ተባባሉ።

16. እነርሱም ፈጥነው ሄዱ፤ ማርያምንና ዮሴፍን፣ ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ።

17. ካዩም በኋላ፣ ስለ ሕፃኑ የተነገራቸውን ገልጠው አወሩ።

18. ይህንንም የሰሙ ሁሉ እረኞቹ በነገሯቸው ነገር ተደነቁ፤

19. ማርያም ግን ይህንን ሁሉ በልቧ ይዛ ታሰላስል ነበር።

20. እረኞቹም ሁሉም ነገር እንደ ተነገራቸው ሆኖ በማግኘታቸው፣ ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያከበሩና እያመሰገኑ ተመለሱ።

ሕፃኑን ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ወሰዱት

21. ስምንት ቀን ሆኖት የመገረዣ ጊዜው ሲደርስ፣ ከመፀነሱ በፊት መልአኩ ባወጣለት ስም ኢየሱስ ተባለ።

22. በሙሴ ሕግ መሠረት፣ የመንጻታቸው ወቅት በተፈፀመ ጊዜ፣ ዮሴፍና ማርያም ሕፃኑን ለጌታ ለማቅረብ ወደ ኢየሩሳሌም ይዘውት ወጡ፤

23. ይኸውም በጌታ ሕግ፣ “ተባዕት የሆነ በኵር ሁሉ ለጌታ የተቀደሰ ይሆናል” ተብሎ እንደ ተጻፈ ለመፈጸምና

24. ደግሞም በጌታ ሕግ፣ “ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች እንደ ተባለ፣” መሥዋዕት ለማቅረብ ነበር።

25. በዚያን ጊዜ ጻድቅና ትጒሕ የሆነ ስምዖን የሚባል አንድ ሰው በኢየሩሳሌም ይኖር ነበር፤ እርሱም የእስራኤልን መጽናናት የሚጠባበቅና መንፈስ ቅዱስ በላዩ ያደረሰው ነበር።

26. ደግሞም የጌታን መሲሕ ሳያይ እንደማይሞት በመንፈስ ቅዱስ ተገልጦለት ነበር፤

27. እርሱም በዚህ ጊዜ በመንፈስ ተመርቶ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ የልጁም ወላጆች በሕጉ ልማድ መሠረት ተገቢውን ሊፈጽሙለት ሕፃኑን ኢየሱስን ይዘው በገቡ ጊዜ፣

28. ስምዖን ተቀብሎ ዐቀፈው፤ እግዚአብሔርን እያመሰገነ እንዲህ አለ፤

29. “ጌታ ሆይ፤ ቃል በገባኸው መሠረት፣አሁን ባሪያህን በሰላም አሰናብተው፤

30. ዐይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን፣

31. ማዳንህን አይተዋልና።

32. ይህም ለአሕዛብ መገለጥን የሚሰጥ ብርሃን፣ለሕዝብህ ለእስራኤልም ክብር ነው።”

33. አባቱና እናቱም ስለ እርሱ በተነገረው ነገር ተገረሙ።

34. ስምዖንም ባረካቸው፤ እናቱን ማርያምንም እንዲህ አላት፤ “ይህ ሕፃን በእስራኤል ለብዙዎች መነሣትና መውደቅ ምክንያት እንዲሆን፣ ደግሞም ክፉ ለሚያስወሩበት ምልክት እንዲሆን ተወስኖአል፤

35. የብዙዎችም የልብ ሐሳብ የተገለጠ እንዲሆን፣ የአንቺም ነፍስ ደግሞ በሰይፍ ይወጋል።”

36. ደግሞም ከአሴር ወገን የሆነች የፋኑኤል ልጅ፣ ሐና የምትባል ነቢይት በዚያ ነበረች፤ እርሷም በጣም አርጅታ ነበር፤ በድንግልናዋ ካገባችው ባሏም ጋር ሰባት ዓመት የኖረች ነበረች፤

37. ዕድሜዋም ሰማንያ አራት ዓመት እስኪሆናት ድረስ ቀንና ሌሊት ከቤተ መቅደስ ሳትለይ፣ በጾምና በጸሎት የምታገለግል መበለት ሆና ቈየች።

38. በዚያኑም ጊዜ ቀርባ እግዚአብሔርን አመሰገነች፤ የኢየሩሳሌምንም መቤዠት ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ ሕፃኑ ተናገረች።

39. ዮሴፍና ማርያም በጌታ ሕግ የታዘዘውን ሁሉ ከፈጸሙ በኋላ፣ በገሊላ አውራጃ ወዳለችው ከተማቸው ወደ ናዝሬት ተመለሱ።

40. ሕፃኑም እያደገና እየጠነከረ ሄደ፤ በጥበብ ተሞላ፤ የእግዚአብሔርም ጸጋ በእርሱ ላይ ነበረ።

ኢየሱስ በዐሥራ ሁለት ዓመቱ ወደ ቤተ መቅደስ ሄደ

41. ወላጆቹም በየዓመቱ ለፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ነበር።

42. ልጁም ዐሥራ ሁለት ዓመት በሆነው ጊዜ፣ እንደተለመደው ወደ በዓሉ ወጡ።

43. በዓሉን ከፈጸሙ በኋላ፣ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ፣ ብላቴናው ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀረ፤ ወላጆቹ ግን መቅረቱን አላወቁም ነበር።

44. አብሮአቸው ያለ መስሎአቸው፣ የአንድ ቀን መንገድ ተጓዙ፤ በኋላ ግን ከዘመዶቻቸውና ከወዳጆቻቸው ዘንድ ይፈልጉት ጀመር፤

45. ባጡትም ጊዜ እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።

46. ከሦስት ቀንም በኋላ፣ በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲያዳምጣቸውና ጥያቄ ሲያቀርብላቸው በቤተ መቅደስ ውስጥ አገኙት፤

47. የሰሙትም ሁሉ በማስተዋሉና በመልሱ ይደነቁ ነበር።

48. ወላጆቹም ባዩት ጊዜ ተገረሙ፤ እናቱም፣ “ልጄ ሆይ፤ ለምን እንዲህ አደረግኸን? አባትህና እኔኮ ተጨንቀን ስንፈልግህ ነበር” አለችው።

49. እርሱም፣ “ለምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት መገኘት እንደሚገባኝ አላወቃችሁምን?” አላቸው።

50. እነርሱ ግን የተናገራቸው ነገር አልገባቸውም።

51. ከዚያም አብሮአቸው ወደ ናዝሬት ወረደ፤ ይታዘዝላቸውም ነበር። እናቱም ይህን ሁሉ ነገር በልቧ ትጠብቀው ነበር።

52. ኢየሱስም በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት አደገ።