ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የኢየሱስ ትንሣኤ

1. በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን ሴቶቹ ያዘጋጁትን ሽቱ ይዘው እጅግ ማለዳ ሳለ ወደ መቃብሩ ሄዱ።

2. ድንጋዩም ከመቃብሩ ደጃፍ ተንከባሎ አገኙት፤

3. ወደ ውስጥ ዘልቀው በገቡ ጊዜ ግን የጌታ ኢየሱስን ሥጋ አላገኙም።

4. በሁኔታው ግራ ተጋብተው ሳሉ፣ እነሆ፤ እጅግ የሚያንጸባርቅ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች ድንገት አጠገባቸው ቆሙ።

5. ሴቶቹም ከመፍራታቸው የተነሣ ወደ ምድር አቀርቅረው ሳሉ፣ ሰዎቹ እንዲህ አሏቸው፤ “ሕያው የሆነውን እርሱን ለምን ከሙታን መካከል ትፈልጋላችሁ?

6. እርሱ ተነሥቶአል! እዚህ የለም፤ ደግሞም በገሊላ በነበረ ጊዜ ምን እንዳላችሁ አስታውሱ፤

7. ‘የሰው ልጅ በኀጢአተኞች እጅ አልፎ ሊሰጥ፣ ሊሰቀልና በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ይገባል’ ብሎ ነበርና።”

8. ሴቶቹም በዚህ ጊዜ ቃሉን አስታወሱ።

9. ሴቶቹ ከመቃብሩ ስፍራ ተመልሰው ይህን ሁሉ ነገር ለዐሥራ አንዱና ለተቀሩት ሁሉ ነገሯቸው።

10. ይህን ለሐዋርያት የነገሯቸውም፣ መግደላዊት ማርያም፣ ዮሐና፣ የያዕቆብ እናት ማርያምና ከእነርሱ ጋር የነበሩት ሌሎች ሴቶች ነበሩ።

11. እነርሱ ግን ሴቶቹ የተናገሩት ቃል መቀባዠር ስለ መሰላቸው አላመኗቸውም።

12. ጴጥሮስ ግን ተነሥቶ ወደ መቃብሩ ሮጠ፤ እዚያ ደርሶም ጐንበስ ብሎ ወደ ውስጥ ሲመለከት፣ በፍታው እንዳለ ለብቻው ተቀምጦ አየ፤ በሆነውም ነገር እየተገረመ ወደ ቤቱ ተመለሰ።

በኤማሁስ መንገድ ላይ

13. በዚሁ ቀን ከደቀ መዛሙርት ሁለቱ፣ ከኢየሩሳሌም ዐሥራ አንድ ኪሎ ሜትር ያህል ወደሚርቅ፣ ኤማሁስ ወደሚባል መንደር ይሄዱ ነበር፤

14. እነርሱም ስለ ሆነው ነገር ሁሉ እርስ በርስ ይነጋገሩ ነበር።

15. እየተነጋገሩና እየተወያዩ ሳሉም ኢየሱስ ራሱ ቀርቦ ከእነርሱ ጋር ይሄድ ጀመር፤

16. ነገር ግን እንዳያውቁት ዐይናቸው ተይዞ ነበር።

17. እርሱም፣ “እየሄዳችሁ፣ መንገድ ላይ እርስ በርስ እንዲህ የምትወያዩት ምንድን ነው?” አላቸው።እነርሱም በሐዘን ክው ብለው ቆሙ።

18. ከእነርሱም አንዱ፣ ቀለዮጳ የተባለው፣ “በእነዚህ ቀናት እዚህ በኢየሩሳሌም የሆነውን ነገር የማታውቅ፣ አንተ ብቻ ለአገሩ እንግዳ ነህን?” ሲል መለሰለት።

19. እርሱም፣ “የሆነው ነገር ምንድን ነው?” አላቸው።እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “በእግዚአብሔርና በሰው ሁሉ ፊት በተግባርና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ ነው፤

20. እርሱን የካህናት አለቆችና ገዦቻችን ለሞት ፍርድ አሳልፈው ሰጡት፤ ሰቀሉትም።

21. እኛ ግን እስራኤልን ይቤዣል ብለን ተስፋ ያደረግነው እርሱን ነበር፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ ይህ ከሆነ ዛሬ ሦስተኛው ቀን ነው።

22. ደግሞም ከእኛው መካከል አንዳንድ ሴቶች አስገረሙን፤ እነርሱም ማልደው ወደ መቃብሩ ሄደው ነበር፤

23. ሥጋውንም ባጡ ጊዜ መጥተው እርሱ በሕይወት እንዳለ የነገሯቸውን መላእክት በራእይ እንዳዩ አወሩልን።

24. ከእኛም መካከል አንዳንዶች ወደ መቃብሩ ሄደው፣ ልክ ሴቶቹ እንዳሉት ሆኖ አገኙት፤ እርሱን ግን አላዩትም።”

25. እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የማታስተውሉ ሰዎች፣ ልባችሁም ነቢያት የተናገሩትን ሁሉ ከማመን የዘገየ፣

26. ክርስቶስ ይህን መከራ መቀበልና ወደ ክብሩም መግባት አይገባውምን?”

27. ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ በቅዱሳት መጻሕፍት ስለ እርሱ የተጻፈውን አስረዳቸው።

28. ወደሚሄዱበትም መንደር በተቃረቡ ጊዜ፣ ኢየሱስ አልፎ የሚሄድ መሰለ።

29. እነርሱ ግን፣ “ምሽት እየተቃረበ፣ ቀኑም እየመሸ ስለ ሆነ ከእኛ ጋር እደር” ብለው አጥብቀው ለመኑት፤ ስለዚህ ከእነርሱ ጋር ለማደር ገባ።

30. አብሮአቸውም በማእድ በተቀመጠ ጊዜ እንጀራውን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ሰጣቸው።

31. በዚህ ጊዜ ዐይናቸው ተከፈተ፤ ዐወቁትም፤ እርሱም ከእነርሱ ተሰወረ።

32. እነርሱም፣ “በመንገድ ሳለን፣ እያነጋገረን ቅዱሳት መጻሕፍትንም ገልጦ ሲያስረዳን፣ ልባችን እንደ እሳት ይቃጠልብን አልነበረምን?” ተባባሉ።

33. በዚያኑም ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ዐሥራ አንዱና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም በዚያ በአንድነት ተሰብስበው አገኟቸው፤

34. “እነርሱም ጌታ በእርግጥ ተነሥቶአል! ለስምዖንም ታይቶአል” ይባባሉ ነበር።

35. ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም በመንገድ ላይ የሆነውንና ኢየሱስ እንጀራውን በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንዳወቁት ተረኩላቸው።

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርት ተገለጠ

36. ይህን እየተነጋገሩ ሳሉ፣ ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ቆሞ፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው።

37. እነርሱ ግን ደንግጠው በፍርሀት ተዋጡ፤ መንፈስም ያዩ መሰላቸው።

38. እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ለምን ትጨነቃላችሁ? ለምንስ ጥርጣሬ በልባችሁ ይገባል?

39. እጆቼንና እግሮቼን ተመልከቱ፤ እኔው ራሴ ነኝ። ደግሞም ንኩኝና እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት መንፈስ ሥጋና ዐጥንት የለውምና።”

40. ይህንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው።

41. እነርሱም ከመደሰትና ከመገረም የተነሣ ገና ሳያምኑ፣ “በዚያ ቦታ አንዳች የሚበላ ነገር አላችሁን?” አላቸው።

42. እነርሱም ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቁራሽ ሰጡት፤

43. እርሱም ተቀብሎ በፊታቸው በላ።

44. እርሱም፣ “ከእናንተ ጋር በነበርሁበት ጊዜ፣ ‘በሙሴ ሕግ፣ በነቢያትና በመዝሙር መጻሕፍት ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል’ ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው” አላቸው።

45. በዚህ ጊዜ ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዲያስተውሉ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፤

46. እንዲህም አላቸው፤ “ ‘እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፤ ክርስቶስ መከራን ይቀበላል፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፤

47. ከኢየሩሳሌም ጀምሮ ለሕዝቦች ሁሉ ንስሓና የኀጢአት ስርየት በስሙ ይሰበካል፤’

48. እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ።

49. እኔም አባቴ የሰጠውን ተስፋ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኀይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቈዩ።”

የኢየሱስ ዕርገት

50. ከዚህ በኋላ እስከ ቢታንያ ይዞአቸው ወጣ፤ እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው።

51. እየባረካቸውም ሳለ፣ ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ሰማይ ዐረገ።

52. እነርሱም ሰገዱለት፤ በታላቅ ደስታም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤

53. እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ ዘወትር በቤተ መቅደስ ነበሩ።