ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 5 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት ተጠሩ

1. ሕዝቡ ዙሪያውን እያጨናነቁት የሚያስተምረውን የእግዚአብሔርን ቃል ሲሰሙ፣ ኢየሱስ በጌንሳሬጥ ሐይቅ አጠገብ ቆሞ ነበር፤

2. በዚህ ጊዜ ሁለት ጀልባዎች በሐይቁ ዳርቻ ቆመው አየ፤ ዓሣ አጥማጆቹ ግን ከጀልባዎቹ ወርደው መረባቸውን ያጥቡ ነበር።

3. ከጀልባዎቹም መካከል የስምዖን ወደ ነበረችው ገብቶ፣ ከምድር ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጋት ለመነው፤ ከዚያም ጀልባዋ ላይ ተቀምጦ ሕዝቡን ያስተምር ጀመር።

4. ንግግሩን በጨረሰ ጊዜ ስምዖንን፣ “ወደ ጥልቁ ውሃ ፈቀቅ በልና ዓሣ ለመያዝ መረባችሁን ጣሉ” አለው።

5. ስምዖንም መልሶ፣ “መምህር ሆይ፤ ሌሊቱን ሙሉ ስንደክም አድረን ምንም አልያዝንም፤ አንተ ካልህ ግን መረቦቹን እጥላለሁ” አለው።

6. እንደዚያም ባደረጉ ጊዜ እጅግ ብዙ ዓሣ ያዙ፤ መረባቸውም ይበጣጠስ ጀመር።

7. በሌላ ጀልባ የነበሩት ባልንጀሮቻቸው መጥተው እንዲያግዟቸውም በምልክት ጠሯቸው፤ እነርሱም መጥተው ሁለቱን ጀልባዎች በዓሣ ሞሏቸው፣ ጀልባዎቹም መስመጥ ጀመሩ።

8. ስምዖን ጴጥሮስም ይህን ባየ ጊዜ በኢየሱስ ጒልበት ላይ ወድቆ፣ “ጌታ ሆይ፤ እኔ ኀጢአተኛ ሰው ነኝና ከእኔ ተለይ” አለው።

9. ይህንን ያለው እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት በያዙት ዓሣ ብዛት ስለ ተደነቁ ነው፤

10. ደግሞም የስምዖን ባልንጀሮች የነበሩት የዘብዴዎስ ልጆች፣ ያዕቆብና ዮሐንስም ተደነቁ።ኢየሱስም ስምዖንን፣ “አትፍራ፤ ከእንግዲህ ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ” አለው።

11. እነርሱም ጀልባዎቹን ወደ ምድር ካስጠጉ በኋላ ሁሉን ትተው ተከተሉት።

ለምጻሙ ሰው

12. ኢየሱስ ከከተሞች በአንዱ በነበረበት ጊዜ፣ አንድ ለምጽ የወረሰው ሰው በዚያው ከተማ ነበር፤ ይህ ሰው ኢየሱስን ባየው ጊዜ በፊቱ ተደፋና፣ “ጌታ ሆይ፤ ብትፈቅድ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” ብሎ ለመነው።

13. ኢየሱስም እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና፣ “እፈቅዳለሁ፤ ንጻ!” አለው፤ ወዲያውም ለምጹ ጠፋለት።

14. ኢየሱስም፣ “ይህን ለማንም አትናገር፤ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ለእነርሱ ምስክር እንዲሆንም ስለ መንጻትህ ሙሴ ያዘዘውን መሥዋዕት አቅርብ” ሲል አዘዘው።

15. ይሁን እንጂ ስለ እርሱ የሚወራው ወሬ ይበልጥ እየሰፋ ሄደ፤ እጅግ ብዙ ሰዎችም እርሱ የሚናገረውን ለመስማትና ካለባቸው ደዌ ለመፈወስ ይሰበሰቡ ነበር።

16. ኢየሱስ ግን ብዙ ጊዜ ወደ ገለልተኛ ስፍራ ወጥቶ ይጸልይ ነበር።

ኢየሱስ ሽባውን ሰው ፈወሰ

17. አንድ ቀን ኢየሱስ እያስተማረ ነበር፤ በዚያም ከገሊላና ከይሁዳ መንደሮች ሁሉ እንዲሁም ከኢየሩሳሌም የመጡ ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን ተቀምጠው ነበር፤ ይፈውስም ዘንድ የጌታ ኀይል ከእርሱ ጋር ነበረ።

18. በዚያን ጊዜም፣ ሰዎች አንድ ሽባ በዐልጋ ተሸክመው አመጡ፤ ኢየሱስ ፊት ለማኖርም ወደ ቤት ሊያስገቡት ሞከሩ፤

19. ከሕዝቡም ብዛት የተነሣ ቤቱ ውስጥ ማስገባት ስላቃታቸው፣ ጣራው ላይ ወጥተው የቤቱን ክዳን በመንደል በሽተኛውን ከነዐልጋው በሕዝቡ መካካል ቀጥታ ኢየሱስ ፊት አወረዱት።

20. ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ፣ “አንተ ሰው፤ ኀጢአትህ ተሰርዮልሃል” አለው።

21. ጸሐፍትና ፈሪሳውያንም፣ “ይህ አምላክን በመዳፈር እንዲህ የሚናገር ማን ነው? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ኀጢአትን ሊያስተስረይ ማን ይችላል?” ብለው ያስቡ ጀመር።

22. ኢየሱስም ሐሳባቸውን ስለ ተረዳ እንዲህ አላቸው፤ “ለምን በልባችሁ እንዲህ ታስባላችሁ?

23. ‘ኀጢአትህ ተሰረየችልህ’ ከማለትና ‘ተነሥተህ ሂድ’ ከማለት የትኛው ይቀላል?

24. ነገር ግን ይህን ያልሁት የሰው ልጅ በምድር ላይ ኀጢአትን ለማስተስረይ ሥልጣን እንዳለው ታውቁ ዘንድ ነው።” ከዚያም ሽባውን ሰው፣ “ተነሥተህ ዐልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ እልሃለሁ” አለው።

25. እርሱም ወዲያው ተነሥቶ በፊታቸው ቆመ፤ ተኝቶበት የነበረውንም ተሸክሞ፣ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ወደ ቤቱ ሄደ።

26. በዚህ ጊዜ ሁሉንም መገረም ያዛቸው፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፣ “ዛሬኮ ድንቅ ነገር አየን” እያሉ በፍርሀት ተዋጡ።

የሌዊ መጠራት

27. ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ ሄደ፤ ሌዊ የተባለ አንድ ቀረጥ ሰብሳቢም በቀረጥ መቀበያው ቦታ ተቀምጦ አየውና፣ “ተከተለኝ” አለው፤

28. እርሱም ሁሉን ትቶ ተነሥቶ ተከተለው።

29. ሌዊም ለኢየሱስ በቤቱ ትልቅ ግብዣ አደረገ፤ ብዙ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ሌሎች ሰዎችም ከእነርሱ ጋር በማእድ ተቀምጠው ነበር።

30. ፈሪሳውያንና ጸሐፍታቸውም “ከቀረጥ ሰብሳቢዎችና ‘ከኀጢአተኞች’ ጋር የምትበሉትና የምትጠጡት ለምንድን ነው?” እያሉ በደቀ መዛሙርቱ ላይ አጒረመረሙ።

31. ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “በሽተኞች እንጂ ጤነኞች ሐኪም አያስፈልጋቸውም፤

32. እኔም ኀጢአተኞችን ወደ ንስሓ ልመልስ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም።”

ኢየሱስ ስለ ጾም ተጠየቀ

33. እነርሱም፣ “የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት አብዛኛውን ጊዜ ይጾማሉ፤ ይጸልያሉ፤ የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርትም እንደዚሁ ያደርጋሉ፤ የአንተዎቹ ግን ዘወትር ይበላሉ፤ ይጠጣሉ” አሉት።

34. ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ሙሽራው አብሮአቸው እያለ ዕድምተኞቹ እንዲጾሙ ማድረግ ይቻላልን?

35. ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ቀን ይመጣል፤ በዚያን ጊዜ ይጾማሉ።”

36. ደግሞም እንዲህ ሲል ምሳሌ ነገራቸው፤ “ከአዲስ ልብስ ላይ እራፊ ቀዶ በአሮጌ ልብስ ላይ የሚጥፍ ማንም የለም፤ እንዲህ ቢያደርግ አዲሱን ልብስ ይቀደዋል፤ አዲሱም እራፊ ለአሮጌው ልብስ አይስማማውም።

37. አዲስ የወይን ጠጅም በአሮጌ አቍማዳ ጨምሮ የሚያስቀምጥ ማንም የለም፤ እንዲህ ቢያደርግ አዲሱ የወይን ጠጅ አቍማዳውን ያፈነዳዋል፤ የወይን ጠጁም ይፈስሳል፤ አቍማዳውም ከጥቅም ውጭ ይሆናል።

38. ስለዚህ አዲስ የወይን ጠጅ በአዲስ አቍማዳ መጨመር አለበት፤

39. እንግዲህ፣ አሮጌ የወይን ጠጅ ከጠጣ በኋላ፣ አዲሱን የሚሻ ማንም የለም፤ ምክንያቱም፣ ‘አሮጌው የተሻለ ነው’ ስለሚል ነው።”