ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የጠፋው በግ ምሳሌ

1. አንድ ቀን፣ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና “ኀጢአተኞች” ሁሉ ሊሰሙት በዙሪያው ተሰበሰቡ።

2. ፈሪሳውያንና ጸሐፍትም፣ “ይህ ሰው ኀጢአተኞችን ይቀበላል፤ ከእነርሱም ጋር ይበላል” እያሉ አጒረመረሙ።

3. ኢየሱስም እንዲህ ሲል ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤

4. “ከእናንተ መካከል አንዱ መቶ በጎች ቢኖሩትና ከእነርሱ አንዱ ቢጠፋበት፣ ዘጠና ዘጠኙን በሜዳ ላይ ጥሎ የጠፋውን እስኪያገኝ ድረስ ሊፈልገው የማይሄድ ማን ነው?

5. ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ተሸክሞ፣

6. ወደ ቤቱ ይመለሳል፤ ወዳጆቹንና ጎረቤቶቹንም በአንድነት ጠርቶ፣ ‘የጠፋውን በጌን አግኝቻለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ’ ይላቸዋል።

7. እላችኋለሁ፤ እንደዚሁም ንስሓ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ፣ ንስሓ በሚገባ በአንድ ኀጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል።

የጠፋው ሳንቲም ምሳሌ

8. “ወይም ዐሥር የብር ሳንቲሞች ያላት ሴት ከዐሥሩ አንዱ ቢጠፋባት፣ እስክታገኘው ድረስ መብራት አብርታ፣ ቤቷን ጠርጋ፣ አጥብቃ የማትፈልግ ሴት ማን ናት?

9. ባገኘችውም ጊዜ ወዳጆቿንና ጐረቤቶቿን፣ በአንድነት ጠርታ፣ ‘የጠፋብኝን የብር ሳንቲም አግኝቻለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ’ ትላቸዋለች።

10. እላችኋለሁ፤ እንደዚሁም ንስሓ በሚገባ በአንድ ኀጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል።

ጠፍቶ የተገኘው ልጅ ምሳሌነት

11. ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት።

12. ከእነርሱም ታናሹ ልጅ አባቱን፣ ‘አባቴ ሆይ፤ ከሀብትህ ድርሻዬን ስጠኝ’ አለው፤ አባትየውም ሀብቱን ለልጆቹ አካፈላቸው።

13. “ብዙም ቀን ሳይቈይ፣ ታናሹ ልጅ ድርሻውን ሁሉ ጠቅልሎ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፤ በዚያም በማጋጣነት ንብረቱን አባከነ።

14. እርሱም ያለውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ፣ በዚያ አገር ሁሉ ጽኑ ራብ ሆነ፤ ይቸገርም ጀመር።

15. ስለዚህ ከዚያ አገር ነዋሪዎች አንዱን ተጠጋ፤ ሰውየውም ዐሣማ እንዲቀልብለት ወደ ዕርሻው ላከው።

16. ዐሣማዎቹ የሚመገቡትን ዐሠር እንኳ ለመብላት ይመኝ ነበር፤ ነገር ግን ይህን እንኳ የሚሰጠው ሰው አልነበረም።

17. “ልብ በገዛ ጊዜ ግን እንዲህ አለ፤ ‘ስንቱ የአባቴ ሠራተኛ ምግብ ተርፎታል፤ እኔ ግን እዚህ በራብ ልሞት ተቃርቤአለሁ

18. ተነሥቼ ወደ አባቴ ልሂድና፣ እንዲህ ልበለው፤ “አባቴ ሆይ፤ በሰማይና በአንተ ፊት በድያለሁ፤

19. ከእንግዲህ ልጅህ ተብዬ ልጠራ አይገባኝም፤ ከተቀጠሩት አገልጋዮችህ እንደ አንዱ ቍጠረኝ።’

20. ስለዚህም ተነሥቶ ወደ አባቱ ሄደ። “ነገር ግን፣ እርሱ ገና ሩቅ ሳለ፣ አባቱ አይቶት ራራለት፤ ወደ እርሱም እየሮጠ ሄዶ ዐቅፎ ሳመው።

21. “ልጁም፣ ‘አባቴ ሆይ፤ በሰማይና በአንተ ፊት በድያለሁ፤ ከእንግዲህ ልጅህ ተብዬ ልጠራ አይገባኝም’ አለው።

22. “አባቱ ግን አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፤ ‘ፈጥናችሁ ከሁሉ ምርጥ የሆነውን ልብስ አምጡና አልብሱት፤ ለጣቱቀለበት፣ ለእግሩም ጫማ አድርጉለት፤

23. የሰባውንም ፍሪዳ አምጡና ዕረዱ፤ እንብላ፤ እንደሰት፤

24. ይህ ልጄ ሞቶ ነበር፤ አሁን ግን ሕያው ሆኖአል፤ ጠፍቶም ነበር፤ ተገኝቶአል።” ከዚያም ይደሰቱ ጀመር።

25. “በዚህ ጊዜ ታላቁ ልጅ በዕርሻ ቦታ ነበረ፤ ከዚያም ተመልሶ ወደ ቤት በተቃረበ ጊዜ፣ የሙዚቃና የጭፈራ ድምፅ ሰማ፤

26. እርሱም ከአገልጋዮቹ አንዱን ጠርቶ ነገሩ ምን እንደሆነ ጠየቀው።

27. አገልጋዩም፣ ‘ወንድምህ መጥቶአል፤ በሰላም በጤና ስለ መጣም አባትህ የሰባውን ፍሪዳ ዐርዶለታል’ አለው።

28. “ታላቅ ወንድሙም ተቈጣ፤ ወደ ቤትም መግባት አልፈለገም፤ አባቱም ወደ ውጭ ወጥቶ እንዲገባ ለመነው።

29. እርሱ ግን መልሶ አባቱን እንዲህ አለው፤ ‘እነሆ፤ ይህን ያህል ዘመን እንደ ባሪያ አገልግዬሃለሁ፤ ከትእዛዝህም አንዱን እንኳ አላጓደልሁም፤ አንተ ግን ከባልንጀሮቼ ጋር እንድደሰት አንዲት የፍየል ግልገል እንኳ አልሰጠኸኝም፤

30. ነገር ግን ይህ ልጅህ ንብረትህን ከጋለሞቶች ጋር አውድሞ ሲመጣ፣ የሰባውን ፍሪዳ አረድህለት።’

31. “አባቱም እንዲህ አለው፤ ‘ልጄ ሆይ፤ አንተ ሁል ጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፤ የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው፤

32. ይህ ወንድምህ ግን ሞቶ ነበር፤ ሕያው ሆነ፤ ጠፍቶ ነበር ተገኘ፤ ስለዚህ ደስ ሊለንና ፍሥሐ ልናደርግ ይገ ባናል።” ’