ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ተግታ የለመነችው መበለት ምሳሌነት

1. ደቀ መዛሙርቱ ሳይታክቱ ሁል ጊዜ መጸለይ እንደሚገባቸው ለማሳየት ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤

2. እንዲህም አላቸው፤ “በአንዲት ከተማ የሚኖር እግዚአብሔርን የማይፈራና ሰውን የማያከብር አንድ ዳኛ ነበረ።

3. በዚያችው ከተማ የምትኖር አንዲት መበለት ነበረች፤ እርሷ፣ ‘ከባላጋራዬ ጋር ስላለብኝ ጒዳይ ፍረድልኝ’ እያለች ወደ እርሱ ትመላለስ ነበር።

4. “ዳኛውም ለተወሰነ ጊዜ አልተቀበላትም ነበር፤ በኋላ ግን በልቡ እንዲህ አለ፤ ‘ምንም እግዚአብሔርን ባልፈራ፣ ሰውንም ባላከብር፣

5. ይህች መበለት ስለ ምትጨቀጭቀኝ እፈር ድላታለሁ፤ አለበለዚያ ዘወትር እየተመላለሰች ታሰለቸኛለች።”

6. ጌታም እንዲህ አለ፤ “ዐመፀኛው ዳኛ ያለውን ስሙ።

7. እግዚአብሔርስ ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን? ከመጠን በላይስ ችላ ይላቸዋልን?

8. እላችኋለሁ፤ ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ በምድር ላይ እምነትን ያገኝ ይሆንን?”

የፈሪሳዊውና የቀረጥ ሰብሳቢው ምሳሌነት

9. ራሳቸውን እንደ ጻድቃን በመቊጠር ለሚመኩና ሌሎቹን በንቀት ዐይን ለሚመለከቱ ሰዎች እንዲህ ሲል ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤

10. “ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ ቤተ መቅደስ ወጡ፣ አንዱ ፈሪሳዊ፣ ሌላው ቀረጥ ሰብሳቢ ነበሩ።

11. ፈሪሳዊውም ቆሞ ስለ ራሱ እንዲህ ይጸልይ ነበር፤ “እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔ እንደ ሌላው ሰው ሁሉ ቀማኛ፣ ዐመፀኛ፣ አመንዝራ፣ ይልቁንም እንደዚህ ቀረጥ ሰብሳቢ ባለመሆኔ አመሰግንሃለሁ፤

12. በሳምንት ሁለት ጊዜ እጾማለሁ፤ ከማገኘውም ሁሉ ዐሥራት አወጣለሁ።”

13. “ቀረጥ ሰብሳቢው ግን በርቀት ቆሞ፣ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ ማየት እንኳ አልፈለገም፤ ነገር ግን ደረቱን እየደቃ፣ ‘እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔን ኀጢአተኛውን ማረኝ’ ይል ነበር።

14. “እላችኋለሁ፤ ከፈሪሳዊው ይልቅ ይኸኛው በእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ጻድቅ ተቈጥሮ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይላልና፤ ራሱን ዝቅ ዝቅ የሚያደርግ ግን ከፍ ይላል።”

ኢየሱስ ከሕፃናት ጋር

15. ኢየሱስ እንዲዳስሳቸው ሰዎች ሕፃናትን ወደ እርሱ ያመጡ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱም ይህን ባዩ ጊዜ ገሠጿቸው።

16. ኢየሱስ ግን ሕፃናቱን ወደ ራሱ ጠርቶ እንዲህ አለ፤ “ሕፃናት ወደ እኔ እንዲመጡ ፍቀዱላቸው፤ አትከልክሏቸው፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ናትና።

17. እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበል ሁሉ ከቶ አይገባባትም።”

ሀብታሙ የአይሁድ አለቃ

18. ከአይሁድ አለቆች አንዱ፣ “ቸር መምህር ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ ምን ላድርግ?” ሲል ጠየቀው።

19. ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም፤

20. ‘አታመንዝር፣ አትግደል፣ አትስረቅ፣ በሐሰት አትመስክር፣ አባትህንና እናትህን አክብር’ የሚለውን ትእዛዝ ታውቃለህ።”

21. ሰውየውም፣ “እነዚህንማ ከልጅነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ” አለው።

22. ኢየሱስም ይህን በሰማ ጊዜ፣ “እንግዲያውስ አንድ ነገር ይቀርሃል፤ ያለህን ሁሉ ሸጠህ ለድኾች ስጥ፤ በሰማይ መዝገብ ይኖርሃል፤ ከዚያም መጥተህ ተከተለኝ” አለው።

23. ሰውየው ግን ይህን ሲሰማ፣ ብዙ ሀብት ስለ ነበረው በጣም ዐዘነ።

24. ኢየሱስም ሰውየውን ተመልክቶ እንዲህ አለ፤ “ብዙ ሀብት ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው?

25. ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀላል።”

26. ይህን የሰሙ ሰዎችም፣ “ታዲያ፣ ማን ሊድን ይችላል?” አሉ።

27. ኢየሱስም፣ “በሰው ዘንድ የማይቻል በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል” አለ።

28. ጴጥሮስም፣ “እነሆ፤ እኛ ያለንን ሁሉ ትተን ተከትለንሃል” አለው።

29. ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ለእግዚአብሔር መንግሥት ብሎ ቤቱን ወይም ሚስቱን ወይም ወንድሞቹን ወይም ወላጆቹን ወይም ልጆቹን የተወ፣

30. በዚህ ዘመን ብዙ ዕጥፍ፣ በሚመጣውም ዘመን የዘላለምን ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም።”

ኢየሱስ ስለ ሞቱ ዳግመኛ ተናገረ

31. ኢየሱስም ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ለብቻ ወስዶ እንዲህ አላቸው፤ “እንግዲህ ወደ ኢየሩሳሌም ልንወጣ ነው፤ ነቢያት ስለ ሰው ልጅ የጻፉትም ሁሉ ይፈጸማል።

32. ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤ እነርሱም ያፌዙበታል፤ ያንገላቱታል፤ ይተፉበታል፤ ይገርፉታል፤ ከዚያም ይገድሉታል።

33. እርሱም በሦስተኛው ቀን ከሙታን ይነሣል።”

34. ደቀ መዛሙርቱ ግን ከዚህ ሁሉ የተረዱት አንድም ነገር አልነበረም፤ አባባሉም ተሰውሮባቸው ነበር፤ ስለ ምን እንደ ተናገረም አላወቁም።

የዐይነ ስውሩ መፈወስ

35. ኢየሱስ ወደ ኢያሪኮ በቀረበ ጊዜ፣ አንድ ዐይነ ስውር መንገድ ዳር ተቀምጦ ይለምን ነበር።

36. ዐይነ ስውሩም ሕዝቡ በዚያ ሲያልፍ ሰምቶ ስለ ሁኔታው ጠየቃቸው።

37. እነርሱም፣ “የናዝሬቱ ኢየሱስ በዚህ እያለፈ ነው” ብለው ነገሩት።

38. እርሱም፣ “የዳዊት ልጅ፣ ኢየሱስ ሆይ፤ ማረኝ!” እያለ ጮኸ።

39. ከፊት የሚሄዱ ሰዎችም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን፣ “የዳዊት ልጅ ሆይ፤ ማረኝ!” እያለ አብዝቶ ጮኸ።

40. ኢየሱስም ቆም ብሎ ሰውየውን ወደ እርሱ እንዲያመጡት አዘዘ፤ ወደ እርሱም በቀረበ ጊዜ፣

41. “ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” ብሎ ጠየቀው።ዐይነ ስውሩም፣ “ጌታ ሆይ፤ ማየት እፈልጋለሁ” አለው።

42. ኢየሱስም፣ “እይ፤ እምነትህ አድኖሃል” አለው።

43. ሰውየውም ወዲያውኑ ማየት ቻለ፤ እግዚአብሔርንም እያከበረ ኢየሱስን ተከተለው። ሕዝቡም ሁሉ ይህን ሲያዩ እግዚአብሔርን አመሰገኑ።