ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 4 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የኢየሱስ መፈተን

1. ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ከዮርዳኖስ እንደ ተመለሰ መንፈስ ወደ በረሓ ወሰደው፤

2. በዚያም አርባ ቀን በዲያብሎስ ተፈተነ፤ በእነዚያም ቀናት ምንም ሳይበላ ቈይቶ በመጨረሻ ተራበ።

3. ዲያብሎስም፣ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፣ እስቲ ይህ ድንጋይ እንጀራ እንዲሆን እዘዘው” አለው።

4. ኢየሱስም፣ “ ‘ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፎአል” ብሎ መለሰለት።

5. ከዚያም ዲያብሎስ ወደ አንድ ከፍታ ቦታ አውጥቶት የዓለምን መንግሥታት ሁሉ በቅጽበት አሳየው፤

6. እንዲህም አለው፤ “የእነዚህ መንግሥታት ሥልጣንና ክብር ሁሉ ለእኔ ተሰጥቶአል፤ እኔም ለምወደው ስለምሰጥ፣ ለአንተ እሰጥሃለሁ፤

7. ስለዚህ ብትሰግድልኝ ይህ ሁሉ የአንተ ይሆናል።”

8. ኢየሱስም መልሶ፣ “ ‘ለጌታ ለአምላክህ ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ’ ተብሎ ተጽፎአል” አለው።

9. ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ወስዶ በቤተ መቅደስ ጒልላት ላይ አቆመውና እንዲህ አለው፤ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፣ እስቲ ራስህን ከዚህ ወደ ታች ወርውር፤

10. ምክንያቱም እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፤“ ‘ይጠብቁህ ዘንድ፣መላእክቱን ስለ አንተ ያዛቸዋል፤

11. እግርህም ከድንጋይ ጋር እንዳይጋጭ፣በእጆቻቸው ወደ ላይ አንሥተው ይይዙሃል።’ ”

12. ኢየሱስም፣ “ ‘ጌታ አምላክህን አትፈታተነው’ ተብሎአል” ብሎ መለሰለት።

13. ዲያብሎስም ፈተናውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ ሌላ አመቺ ጊዜ እስኪያገኝ ድረስ ከእርሱ ተለየ።

ኢየሱስ በናዝሬት ተቀባይነት ማጣቱ

14. ኢየሱስም በመንፈስ ኀይል ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ ዝናውም በአካባቢው ባለው አገር ሁሉ ወጣ።

15. እርሱም በምኵራባቸው ያስተምር ነበር፤ ሰውም ሁሉ ያመሰግነው ነበር።

16. ከዚያም ወዳደገበት ከተማ ወደ ናዝሬት መጣ፤ እንደ ልማዱም በሰንበት ወደ ምኵራብ ገባ፤ ሊያነብም ተነሥቶ ቆመ።

17. የነቢዩ ኢሳይያስ ጥቅልል መጽሐፍም ተሰጠው፤ ጥቅልሉንም መጽሐፍ በተረተረው ጊዜ እንዲህ ተብሎ የተጻፈበትን ክፍል አገኘ፤

18. “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኾች ወንጌልን እንድሰብክ፣ እርሱ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩት መፈታትን፣ ለታወሩትም ማየትን እንዳውጅ፣ የተጨቈኑትን ነጻ እንዳወጣ፣

19. የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እንዳውጅ ልኮኛል።”

20. ከዚያም መጽሐፉን ጠቅልሎ ለአገልጋዩ መልሶ ሰጠውና ተቀመጠ፤ በምኵራብ የነበሩትም ሁሉ ትኵር ብለው ይመለከቱት ነበር።

21. እርሱም፣ “ይህ በጆሮአችሁ የሰማችሁት የመጽሐፍ ቃል ዛሬ ተፈጸመ” ይላቸው ጀመር።

22. ሁሉም ስለ እርሱ በበጎ ይናገሩ ነበር፤ ደግሞም ከአንደበቱ በሚወጣ የጸጋ ቃል እየተገረሙ፣ “ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን?” ይሉ ነበር።

23. እርሱም፣ “ ‘ባለ መድኀኒት ሆይ፤ ራስህን ፈውስ፤ በቅፍርናሆም ስታደርግ የሰማነውን ነገር እዚህ በራስህ ከተማ ደግሞ አድርግ’ የሚለውን ምሳሌ እንደምትጠቅሱብኝ ጥርጥር የለውም” አላቸው።

24. ደግሞም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ነቢይ በገዛ አገሩ አይከበርም።

25. ነገር ግን እውነት እላችኋለሁ፤ ሰማይ ሦስት ዓመት ከመንፈቅ ተዘግቶ ጽኑ ራብ በምድሪቱ ሁሉ ላይ በነበረበት በኤልያስ ዘመን፣ ብዙ መበለቶች በእስራኤል ነበሩ፤

26. ኤልያስ ከእነዚህ መካከል ወደ አንዷም አልተላከም፤ ነገር ግን በሲዶና አገር በሰራፕታ ወደ ነበረችው መበለት ተላከ።

27. በነቢዩ በኤልሳዕ ዘመንም በእስራኤል ብዙ ለምጻሞች ነበሩ፤ ነገር ግን ከሶርያዊው ከንዕማን በቀር ከእነዚያ መካካል ማንም አልነጻም።”

28. በምኵራብ የነበሩ ሰዎች ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ በቍጣ ገነፈሉ፤

29. ከተቀመጡበትም ተነሥተው ከከተማው አስወጡት፤ ቊልቊል ሊጥሉትም ከተማቸው ወደ ተሠራች በት ኰረብታ አፋፍ ወሰዱት፤

30. እርሱ ግን በመካከላቸው ሰንጥቆ ሄደ።

ኢየሱስ ርኩስ መንፈስ አስወጣ

31. ከዚያም በገሊላ አውራጃ ወደምትገኘው ከተማ ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፤ በዚያም በሰንበት ዕለት ሕዝቡን ያስተምር ጀመር፤

32. የሚናገረው በሥልጣን ስለ ነበር በትምህርቱ ተደነቁ።

33. በምኵራብም የርኩስ ጋኔን መንፈስ ያደረበት ሰው ነበረ፤ እርሱም ከፍ ባለ ድምፅ ጮኾ፣

34. “ወዮ! የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፤ ምን የሚያገናኘን ጉዳይ አለ? የመጣኸው ልታጠፋን ነውን? አንተ ማን እንደሆንህ ዐውቃለሁ፤ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ!” አለው።

35. ኢየሱስም፣ “ጸጥ ብለህ ከዚህ ሰው ውጣ!” ብሎ ገሠጸው። ጋኔኑም ሰውየውን በሕዝቡ ሁሉ ፊት ጣለውና ምንም ጒዳት ሳያደርስበት ለቆት ወጣ።

36. ሰዎቹም ሁሉ ተገረሙ፤ እርስ በእርሳቸውም፣ “ለመሆኑ ይህ ትምህርት ምንድን ነው? በሥልጣንና በኀይል ርኩሳን መናፍስትን ያዛል፤ እነርሱምኮ ይወጣሉ” ተባባሉ።

37. የእርሱም ዝና በአካባቢው ወዳለው ስፍራ ሁሉ ወጣ።

ኢየሱስ ብዙ በሽተኞችን ፈወሰ

38. ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከምኵራብ ወጥቶ ወደ ስምዖን ቤት ገባ። የስምዖንም አማት ኀይለኛ ትኵሳት ይዞአት ታማ ነበር፤ እንዲፈውሳትም ስለ እርሷ ለመኑት።

39. እርሱም ወደ ተኛችበት ጠጋ ብሎ በማጐንበስ ትኵሳቱን ገሠጸው፤ ትኵሳቱም ለቀቃትና ወዲያው ተነሥታ አስተናገደቻቸው።

40. ፀሓይ መጥለቂያ ላይም፣ የተለያየ ሕመም ያደረባቸውን ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤ እርሱም በእያንዳንዳቸው ላይ እጁን ጭኖ ፈወሳቸው።

41. አጋንንትም ደግሞ፣ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ!” እያሉና እየጮኹ ከብዙ ሰዎች ወጡ። እርሱ ግን ገሠጻቸው፤ ክርስቶስ መሆኑንም ያውቁ ስለ ነበር፣ አንዳች እንዲናገሩ አልፈቀደላቸውም።

42. ሲነጋም ኢየሱስ ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ ሄደ፤ ሕዝቡም ይፈልጉት ነበር፤ እርሱ ወዳለበትም ቦታ መጡ፤ ከእነርሱ ተለይቶ እንዳይሄድ ሊከለክሉት ሞከሩ።

43. እርሱ ግን፣ “ወደ ሌሎቹም ከተሞች ሄጄ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል መስበክ ይገባኛል፤ የተላክሁት ለዚሁ ዐላማ ነውና” አላቸው።

44. በይሁዳ ምኵራቦችም መስበኩን ቀጠለ።