ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36
  37. 37
  38. 38
  39. 39
  40. 40

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 8 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የጓጒንቸር መቅሠፍት

1. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ “ወደ ፈርዖን ዘንድ ሄደህ፣ እንዲህ በለው፤ ‘እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚለው ይህ ነው፤ “እኔን ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ።

2. እነርሱን ለመልቀቅ እምቢ ብትል አገርህን ሁሉ በጓጒንቸር መቅሠፍት እመታዋለሁ።

3. አባይ በጓጒንቸሮች ይሞላል፤ ወጥተውም ወደ ቤተ መንግሥትህና ወደ መኝታ ክፍልህ፣ ወደ አልጋህም ወደ ሹማምቶችህና ወደ ሕዝብህ ቤቶች፣ ወደ ምድጆችህና ወደ ቡሃቃዎችህ ይገባሉ።

4. ጓጒንቸሮቹ ወደ አንተና ወደ ሕዝብህ ወደ ሹማምቶችህም ሁሉ ይመጡባችኋል።’ ”

5. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፣ “አሮንን፣ ‘በትርህን ይዘህ በምንጮች፣ በቦዮችና በኩሬዎች ላይ እጅህን ዘርጋ፤ ጓጒንቸሮችም በግብፅ ምድር ላይ እንዲወጡ አድርግ’ ” በለው።

6. አሮንም በግብፅ ውሆች ላይ እጁን ዘረጋ፤ ጓጒንቸሮችም ወጥተው ምድሪቱን ሸፈኑ።

7. ሆኖም ግን አስማተኞቹ በድብቅ ጥበባቸው ተመሳሳይ ነገር ሠሩ፤ እነርሱም በግብፅ ምድር ላይ ጓጒንቸሮች እንዲወጡ አደረጉ።

8. ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ ጓጒንቸሮቹን ከእኔና ከሕዝቤ ያርቅ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጸልዩልኝ፤ ከዚያም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕትን ትሠዉ ዘንድ ሕዝቡ እንዲሄዱ እፈቅዳለሁ።

9. ሙሴም ፈርዖንን፣ “በአባይ ወንዝ ካሉት በቀር ከአንተና ከቤቶችህ ጓጒንቸሮቹ እንዲወገዱ ለአንተ፣ ለሹማምቶችህና ለሕዝብህ የምንፀልይበትን ጊዜ እንድትወስን ለአንተ ትቸዋለሁ” አለው።

10. ፈርዖንም፣ “ነገ ይሁን” አለው። ሙሴም እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “እንደ አምላካችን እንደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ያለ ማንም እንደሌለ ታውቅ ዘንድ አንተ እንዳልኸው ይሆናል።

11. ጓጒንቸሮቹም ከአንተና ከቤቶችህ፣ ከሹማምቶችህና ከሕዝብህ ተወግደው በዐባይ ወንዝ ብቻ ይወሰናሉ።”

12. ሙሴና አሮን ከፈርዖን ዘንድ ከተመለሱ በኋላ፣ በፈርዖን ላይ እግዚአብሔር (ያህዌ) ስላመጣቸው ጓጒንቸሮች ሙሴ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጮኸ።

13. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴ እንደ ለመነው አደረገ፤ ጓጒንቸሮቹም በየቤቱ ውስጥ፣ በየአጥር ግቢውና በየሜዳው ሞቱ።

14. በአንድ ላይ ሰብስበው ከመሯቸው፤ ምድሪቱም ከረፋች።

15. ፈርዖን ችግሩ ጋብ ማለቱን ባየ ጊዜ ግን ልክ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ተናገረው ልቡን በማደንደን ሙሴንና አሮንን አልሰማቸውም።

የተባይ መቅሠፍት

16. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “አሮንን ‘በትርህን ሰንዝረህ የምድርን ትቢያ ምታ’ በለው፤ ከዚያም በግብፅ ምድር ያለው ትቢያ ሁሉ ተናካሽ ትንኝ ይሆናል” አለው።

17. እነርሱም እንዲሁ አደረጉ፣ አሮን በትሩን እንደ ያዘ እጁን ሲዘረጋና የምድሩን ትቢያ ሲመታ፣ በግብፅ ምድር ያለው ትቢያ ሁሉ ተናካሽ ትንኝ ሆነ። ሰውንም ሆነ እንስሳውን ተናካሽ ትንኝ ወረረው።

18. ነገር ግን አስማተኞቹ በድብቅ ጥበባቸው ተናካሽ ትንኞችን ለመፍጠር ሲሞክሩ አልቻሉም። ተናካሽ ትንኞቹም ከሰውና ከእንስሳው ላይ አልወረዱም ነበር።

19. አስማተኞቹም ፈርዖንን፣ “ይህ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ጣት ነው” አሉት፤ ነገር ግን የፈርዖን ልብ ደንድኖ ስለ ነበር፣ ልክ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ተናገረው አልሰማቸው አለ።

20. ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በጧት ተነሥተህ ፈርዖን ወደ ውሃ በሚወርድበት ጊዜ ከፊቱ ቀርበህ እንዲህ በለው፤ ‘እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚለው ይህ ነው፤ ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ።

21. ሕዝቤ እንዲሄዱ ባትለቃቸው፣ በአንተና በሹማምትህ ላይ፣ በሕዝብህና በቤቶችህ ላይ የዝንብ መንጋ እሰዳለሁ። ያረፉበት መሬት እንኳ ሳይቀር፣ የግብፃውያን ቤቶች ሁሉ ዝንብ ብቻ ይሆናሉ።

22. “ ‘በዚያች ዕለት ግን ሕዝቤ የሚኖርባትን የጌሤምን ምድር የተለየች አደርጋታለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) በዚህች ምድር እንዳለሁ ታውቅ ዘንድ የዝንብ መንጋ በዚያ አይኖርም።

23. በሕዝቤና በሕዝብህ መካከል ልዩነት አደርጋለሁ፤ ይህ ታምራዊ ምልክት ነገ ይሆናል።’ ”

24. እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዲሁ አደረገ፤ አስጨናቂ የዝንብ መንጋ በፈርዖን ቤተ መንግሥትና በሹማምቶቹ ቤቶች ላይ ወረደ፤ መላው የግብፅ ምድር ከዝንቡ የተነሣ ተበላሽቶ ነበር።

25. ከዚያም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን አስጠርቶ፣ “ሂዱና በዚሁ ምድር ለአምላካችሁ ሠዉ” አላቸው።

26. ሙሴ ግን እንዲህ አለ፤ “ይህ ትክክል አይሆንም፤ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የምናቀርበው መሥዋዕት በግብፃውያን ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ ታዲያ በእነርሱ ዐይን አስጸያፊ የሆነውን መሥዋዕት ብናቀርብ አይወግሩንምን?

27. ለአምላካችን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) እርሱ እንዳዘዘን መሥዋዕት ለመሠዋት ወደ ምድረ በዳ የሦስት ቀን መንገድ መሄድ አለብን።

28. ፈርዖንም፣ “ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በምድረ በዳ መሥዋዕት እንድ ትሠዉ እፈቅድላችኋለሁ፤ ነገር ግን ርቃችሁ እንዳትሄዱ። ለእኔም ጸልዩልኝ” አላቸው።

29. ሙሴም እንዲህ አለ፤ “ከአንተ እንደ ተለየሁ ወዲያውኑ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) እጸልያለሁ፤ ነገም ዝንቡ ሁሉ ከፈርዖን፣ ከሹማምቶቹና ከሕዝቡ ይወገዳል። ብቻ ሕዝቡ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት እንዲሠዉ ባለመፍቀድ ከዚህ ቀደም ፈርዖን አታሎ እንዳደረገው አሁንም እንዳያደርግ ርግጠኛ ይሁን።”

30. ከዚያም ሙሴ ከፈርዖን ተለይቶ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጸለየ።

31. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴ የለመነውን አደረገ። የዝንቡም መንጋ ከፈርዖን፣ ከሹማምቶቹና ከሕዝቡ ተወገደ፤ አንድም ዝንብ እንኳ አልቀረም።

32. በዚህም ጊዜ እንኳን ፈርዖን ልቡን አደነደነ እንጂ፣ ሕዝቡን አለቀቀም።