ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36
  37. 37
  38. 38
  39. 39
  40. 40

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በበኵሮች ላይ የወረደ መቅሠፍት

1. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በፈርዖንና በግብፅ ላይ አንድ ሌላ መቅሠፍት አወርድባቸዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ ፈርዖን ይለቃችኋል፤ ሲለቃችሁም አንዳችሁን ሳያስቀር ያስወጣችኋል።

2. ለእስራኤል ሕዝብ ለወንዶቹም ሆነ ለሴቶቹ የብርና የወርቅ ዕቃዎች ከየጐረቤቶቻቸው ስጡን ብለው እንዲወስዱ ንገራቸው።

3. እግዚአብሔርም (ያህዌ) እስራኤላውያን በግብፃውያን ዘንድ ሞገስ እንዲያገኙ አደረጋቸው። ሙሴም በግብፅ ምድር በፈርዖን ሹማምትና በመላው ሕዝብ ዘንድ እጅግ የተከበረ ሰው ሆነ።

4. ከዚህ በኋላ ሙሴ እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚለው ይህ ነው፤ ‘እኩለ ሌሊት ሲሆን በመላው የግብፅ ምድር ላይ አልፋለሁ።

5. በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ከፈርዖን ልጅ አንሥቶ የወፍጮ መጅ ገፊ እስከ ሆነችው እስከ ባሪያይቱ ልጅ ድረስ በግብፅ ምድር በኵር ሆኖ የተወለደ ወንድ ልጅ ሁሉ ይሞታል፤ እንዲሁም የቀንድ ከብቱ በኵር በሙሉ ያልቃል።

6. በግብፅ ምድር ሁሉ ከዚህ በፊት ያልተሰማ ወደ ፊትም የማይሰማ ታላቅ ዋይታ ይሆናል።

7. በእስራኤላውያን ዘንድ ግን በሰውም ሆነ በእንስሳት ላይ ውሻ እንኳ አይጮኽባቸውም።’ በዚህም እግዚአብሔር (ያህዌ) በግብፃውያንና በእስራኤላውያን መካከል ልዩነት የሚያደርግ መሆኑን ታውቃላችሁ።

8. ሹማምትህ በሙሉ ወደ እኔ ይመጣሉ፤ እጅ እየነሡም ‘አንተም ሆንህ የምትመራቸው ሰዎች በሙሉ ውጡልን’ ብለው ይለምኑኛል፤ እኔም ከዚያ በኋላ እሄዳለሁ።” ከዚያም ሙሴ በታላቅ ቍጣ ከፈርዖን ዘንድ ወጣ።

9. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን “ድንቅ ሥራዎቼ በግብፅ ምድር በብዛት ይታዩ ዘንድ ፈርዖን እናንተን አይሰማችሁም” አለው።

10. ሙሴና አሮንም እነዚህን ድንቅ ታምራት በፈርዖን ፊት አደረጉ። ነገር ግን እግዚአብሔር (ያህዌ) የፈርዖንን ልብ አደነደነ፤ ፈርዖንም እስራኤላውያን ከአገሩ ለቀው እንዲሄዱ አልፈቀደም።