ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36
  37. 37
  38. 38
  39. 39
  40. 40

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 37 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የኪዳኑ ታቦት

1. ባስልኤል ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፣ ወርዱ አንድ ክንድ ተኩል፣ ከፍታው አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ታቦት ከግራር ዕንጨት ሠራ።

2. በውስጥና በውጭ በንጹሕ ወርቅ ለበጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ አበጀለት።

3. አራት የወርቅ ቀለበቶችን ሠርቶ ሁለት ቀለበቶችን በአንድ በኩል፣ ሁለት ቀለበቶችንም በሌላ በኩል አድርጎ ከአራቱ እግሮቹ ጋር አያያዛቸው።

4. ከዚያም መሎጊያዎችን ከግራር ዕንጨት ሠርቶ በወርቅ ለበጣቸው።

5. መሎጊያዎቹንም መሸከሚያ እንዲሆኑ በታቦቱ ጐንና ጐን ባሉት ቀለበቶች ውስጥ አስገባቸው።

6. ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፣ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ከንጹሕ ወርቅ የስርየት መክደኛ ሠራ።

7. ከዚያም ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሁለት ኪሩቤልን ከመክደኛው ጫፎች ላይ ሠራ።

8. አንዱን ኪሩብ በአንዱ ጫፍ ላይ፣ ሁለተኛውንም ኪሩብ በሌላው ጫፍ ላይ ሠራ፤ ከሁለቱ ጫፎች ላይ ከክዳኑ ጋር አንድ ወጥ አድርጎ ሠራቸው፤

9. ኪሩቤልም የስርየት ክዳኑን በመሸፈን ክንፋቸውን ወደ ላይ ዘርግተው ነበር፤ ኪሩቤል ወደ ስርየት መክደኛው እየተመለከቱ እርስ በርሳቸው ገጽ ለገጽ ነበሩ።

የኅብስት ማስቀመጫው ጠረጴዛ

10. ርዝመቱ ሁለት ክንድ፣ ወርዱ አንድ ክንድ፣ ከፍታውም አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ጠረጴዛ ከግራር ዕንጨት ሠሩ።

11. ከዚያም በንጹህ ወርቅ በመለበጥ በዙሪያው የወርቅ ክፈፍ አበጁለት።

12. በዙሪያውም ስፋቱ አንድ ስንዝር የሆነ ጠርዝ በማበጀት በጠርዙ ላይ የወርቅ ክፈፍ አደረጉበት።

13. ለጠረጴዛው አራት የወርቅ ቀለበቶች አበጅተው አራቱ እግሮች ካሉበት ከአራቱ ማእዘኖች ጋር አያያዟቸው።

14. ጠረጴዛውን ለመሸከም የሚያገለግሉትን መሎጊያዎች እንዲይዙ ቀለበቶቹ ከጠርዙ አጠገብ ሆኑ።

15. ጠረጴዛውን ለመሸከም የሚያገለግሉት መሎጊያዎች ከግራር ዕንጨት የተሠሩና በወርቅ የተለበጡ ነበሩ።

16. የጠረጴዛውን ዕቃዎች ይኸውም ዝርግ ሳሕኖችን፣ ድስቶችንና ጐድጓዳ ሳሕኖችን እንዲሁም የመጠጥ መሥዋዕቱ ማፍሰሻ የሆኑትን ማንቈርቈሪያዎች ከንጹሕ ወርቅ ሠሯቸው።

መቅረዙ

17. መቅረዙን ከንጹሕ ወርቅ ሠሩት፤ መቆሚያውንና ዘንጉን ቀጥቅጠው አበጁት፤ የአበባ ቅርጽ ያላቸው ጽዋዎች፣ እንቡጦችና የፈኩ አበቦች ከእርሱ ጋር አንድ ወጥ ሆነው ተሠርተው ነበር።

18. ሦስቱ በአንድ በኩል ሦስቱ በሌላ በኩል በመሆን ስድስት ቅርንጫፎች ከመቅረዙ ጐኖች ተሠርተው ነበር።

19. ከእንቡጦችና ከፈኩ አበቦች ጋር የለውዝ አበባ የሚመስሉ ሦስት ጽዋዎች በአንዱ ቅርንጫፍ ላይ፣ ሦስቱ ደግሞ በሚቀጥለው ቅርንጫፍ ላይ ነበሩ፤ ከመቅረዙ ለወጡት ለስድስቱም ቅርንጫፎች ሁሉ እንዲሁ ነበር።

20. እንቡጦችና የፈኩ አበቦች ያሉባቸው የለውዝ አበባ የሚመስሉ አራት ጽዋዎች በመቅረዙ ላይ ነበሩ።

21. አንደኛው እንቡጥ ከመቅረዙ ወጣ ብለው በሚገኙት በመጀመሪያው ጥንድ ቅርንጫፎች ሥር ሁለተኛውም እምቡጥ በሁለተኛው ጥንድ ሥር እንዲሁም ሦስተኛው እንቡጥ በሦስተኛው ጥንድ ሥር ነበር፣ በስድስቱም ቅርንጫፎች እንዲሁ ነበር።

22. እንቡጦቹና ቅርንጫፎቹ ሁሉ ከንጹሕ ወርቅ ተሠርተው ከመቅረዙ ጋር አንድ ወጥ ነበሩ።

23. የመቅረዙን ሰባት መብራቶች፣ እንዲሁም መኮስተሪያዎችንና የኵስታሪ ማስቀ መጫዎችን ከንጹሕ ወርቅ ሠሩ።

24. መቅረዙንና ዕቃዎቹን ሁሉ ከአንድ መክሊት ንጹሕ ወርቅ ሠሩ።

የዕጣን መሠዊያው

25. የዕጣን መሠዊያውን ከግራር ዕንጨት ሠሩ፤ ርዝመቱ አንድ ክንድ፣ ወርዱ፣ አንድ ክንድ፣ ከፍታው ሁለት ክንድ ነበር፤ ቀንዶቹም ከእርሱ ጋር አንድ ወጥ ሆነው ተሠርተው ነበር።

26. ላዩን፣ ጐኖቹን ሁሉና ቀንዶቹን በንጹሕ ወርቅ ለበጧቸው፤ በዙሪያው የወርቅ ክፈፍ አበጁ።

27. ለሸክም የሚሆኑትን መሎጊያዎች ለመያዝ ትይዩ የሆኑ ከክፈፉ ሥር ሁለት የወርቅ ቀለበቶችን ሠሩ።

28. መሎጊያዎቹን ከግራር ዕንጨት ሠሩ፤ በወርቅም ለበጧቸው።

29. እንዲሁም የተቀደሰውን ቅብዐ ዘይትና የሽቶ ቀማሚ ሥራ የሆነውን፣ ንጹሕና መልካም መዐዛ ያለውን ዕጣን ሠሩ።