ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36
  37. 37
  38. 38
  39. 39
  40. 40

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የእንስሳት እልቂት

1. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ወደ ፈርዖን ሂድና እንዲህ በለው፤ ‘የዕብራውያን አምላክ (ኤሎሂም) እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚለው ይህ ነው፤ “ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ።”

2. አሁንም እንዳይሄዱ ብታደርግና ብትከለክላቸው፣

3. የእግዚአብሔር (ያህዌ) እጅ በመስክ ላይ ባሉት እንስሳት፣ በፈረሶችህና በአህዮችህ፣ በግመሎችህና በቀንድ ከብቶችህ፣ በበጎችህና በፍየሎችህ ላይ አስከፊ መቅሠፍት ያመጣብሃል።

4. ነገር ግን እግዚአብሔር (ያህዌ) በእስራኤልና በግብፅ እንስሳት መካከል ልዩነት ያደርጋል፤ ይኸውም የእስራኤል የሆነ ማንኛውም እንስሳ እንዳይሞት ነው።’ ”

5. እግዚአብሔር (ያህዌ) ጊዜን ወስኖ፣ እንዲህ አለ፤ “በነገው ዕለት እግዚአብሔር (ያህዌ) በምድሪቱ ላይ ይህን ያደርጋል።”

6. በማግሥቱም እግዚአብሔር (ያህዌ) ነገሩን ፈጸመው፤ የግብፃውያን እንስሳት በሙሉ አለቁ፤ ነገር ግን የእስራኤላውያን ከሆኑት እንስሳት አንድም አልሞተም።

7. ፈርዖን ያጣሩ ዘንድ ሰዎች ልኮ ከእስራኤላውያኑ እንስሳት አንድም እንኳን አለመሞቱን ተገነዘበ። ያም ሆኖ ልቡ እንደ ደነደነ ስለ ነበር፣ ሕዝቡን አልለቀቀም።

የእባጭ መቅሠፍት

8. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን አላቸው፤ “ከምድጃው እፍኝ ዐመድ ወስዳችሁ፣ ሙሴ በፈርዖን ፊት ወደ ሰማይ ይበትነው።

9. በግብፅ ምድር ሁሉ ትቢያ ይሆናል፤ በምድሪቱ ሁሉ በሚገኙት ሰዎችና እንስሳት ላይ መግል የያዘ እባጭ ይወጣል።”

10. ስለዚህ ከምድጃው ዐመድ ወስደው በፈርዖን ፊት ቆሙ፤ ሙሴም ወደ ሰማይ በተነው፤ መግል የያዘ እባጭም በሰዎችና በእንስሳት ላይ ወጣ።

11. በእነርሱና በግብፃውያን ሁሉ ላይ እባጭ ወጥቶ ስለ ነበር፣ አስማተኞቹ በሙሴ ፊት መቆም አልቻሉም።

12. እግዚአብሔር (ያህዌ) ግን የፈርዖንን ልብ አደነደነ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሙሴ እንደ ተናገረውም፣ ሙሴንና አሮንን መስማት አልፈለገም።

የበረዶ መቅሠፍት

13. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ማልደህ በጧት ተነሣ፤ ከፈርዖን ፊት ቀርበህ እንዲህ በለው፤ የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር (ያህዌ ኤሎሂም) የሚለው ይህ ነው፤ ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ፤

14. አለዚያ በአንተ በሹማምቶችህና በሕዝብህ ላይ የመቅሠፍቴን መዓት ሁሉ አሁን አወርድብሃለሁ፤ ይኸውም በምድር ሁሉ እንደ እኔ ያለ ማንም እንደሌለ ታውቅ ዘንድ ነው።

15. አሁን እጄን ዘርግቼ አንተንና ሕዝብህን ከገጸ ምድር ሊያጠፋችሁ በሚችል መቅሠፍት በመታኋችሁ ነበር።

16. ነገር ግን ኀይሌን እንዳሳይህና ስሜም በምድር ዙሪያ ሁሉ እንዲታወቅ ለዚህ አስነሥቼሃለሁ።

17. እስካሁንም በሕዝቤ ላይ እንደ ተነሣህ ነው፤ ይሄዱም ዘንድ አትለቃቸውም።

18. ስለዚህ ነገ በዚህ ጊዜ ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በግብፅ ላይ ወርዶ የማያውቅ አስከፊ የበረዶ ማዕበል እልካለሁ።

19. ከብቶችህና በመስክ ላይ ያለህ ማንኛውም ነገር ወደ መጠለያ ይገቡ ዘንድ አሁን ትእዛዝ ስጥ፤ ምክንያቱም በረዶው ወደ መጠለያ ባልገቡትና በመስክ ላይ በቀሩት በማንኛውም ሰውና እንስሳት ላይ ወርዶባቸው ስለሚሞቱ ነው።

20. የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ቃል የፈሩት የፈርዖን ሹማምቶች፣ ባሮቻቸውንና ከብቶቻቸውን ለማስገባት ተጣደፉ።

21. የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ቃል ችላ ያሉት ግን ባሮቻቸውንና ከብቶቻቸውን በመስክ ላይ እንደ ነበሩ ተዉአቸው።

22. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “በመላይቱ የግብፅ ምድር ባሉት ሰዎች፣ በእንስሳት እንዲሁም በምድሪቱ ላይ በሚበቅሉት ነገሮች ሁሉ ላይ በረዶ እንዲወርድ እጅህን ወደ ሰማይ አንሣ” አለው።

23. ሙሴ በትሩን ወደ ሰማይ ባነሣ ጊዜ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነጐድጓድና በረዶ አወረደ፤ መብረቅም በምድሪቱ ላይ ሆነ። እግዚአብሔር (ያህዌ) በግብፅ ምድር በረዶ አዘነበ፤

24. በረዶ ወረደ፤ መብረቅም አብረቀረቀ፤ ግብፅ ሐገር ከሆነችበት ዘመን አንሥቶ በምድሪቱ ሁሉ እንደዚህ ያለ አስከፊ ማዕበል ሆኖ አያውቅም።

25. በመላው ግብፅ በረዶ በመስክ ላይ ያለውን ሁሉ፣ ሰዎችንና እንስሳትንም መታ፤ በመስክ ላይ የበቀለውን ሁሉ አጠፋ፤ ዛፉን ሁሉ ባዶ አስቀረ።

26. በረዶ ያልወረደበት ቢኖር እስራኤላውያን የሚኖሩበት የጌሤም ምድር ብቻ ነበር።

27. ከዚያም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን አስጠራ፤ እንዲህም አላቸው፤ ‘አሁንስ በድያለሁ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ትክክል ነው፤ እኔና ሕዝቤ ግን ስተናል።

28. መብረቅና በረዶ በዝቶብናልና ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጸልዩልን፤ እንድትሄዱ እለቃችኋለሁ፤ ከዚህ በኋላ በዚህ የመኖር ግዴታ የለባችሁም።

29. ሙሴም መልሶ፣ “ከከተማዋ በወጣሁ ጊዜ፣ እጆቼን ለጸሎት ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) እዘረጋለሁ፤ አንተም ምድር የእግዚአብሔር (ያህዌ) እንደሆነች ታውቅ ዘንድ መብረቁ ያቆማል፤ ከእንግዲህ በኋላ በረዶ አይኖርም።

30. ሆኖም አንተና ሹማምትህ አሁንም ቢሆን እግዚአብሔር (ያህዌ) አምላክን እንደማትፈሩ ዐውቃለሁ።

31. ተልባው አብቦ፣ ገብሱም ፍሬ ይዞ ስለ ነበር፣ ተልባውና ገብሱ ከጥቅም ውጭ ሆኑ።

32. ስንዴውና አጃው ግን በዚያ ወቅት ባለማፍራቱ አልጠፋም ነበር።

33. ከዚያም ሙሴ ከፈርዖን ተለይቶ ከከተማው ወጣ። እጁን ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ዘረጋ፤ ነጎድጓዱና በረዶው ቆመ፤ ዝናቡም በምድሪቱ ላይ መዝነቡን አቆመ።

34. ፈርዖንም ዝናቡ፣ በረዶውና ነጎድጓዱ መቆሙን ባየ ጊዜ እንደ ገና በደለ፤ እርሱና ሹማምቶቹ ልባቸውን አደነደኑ።

35. ስለዚህ የፈርዖን ልብ ደነደነ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሙሴ እንደ ተናገረውም እስራኤላውያን ይሄዱ ዘንድ አልለቀቃቸውም።