ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36
  37. 37
  38. 38
  39. 39
  40. 40

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የማደሪያው ድንኳን

1. “በቀጭኑ ከተፈተለ የበፍታ ድርና በሰማያዊ፣ በሐምራዊና በቀይ ማግ በተሠሩ ዐሥር መጋረጃዎች ማደሪያ ድንኳኑን ሥራ፤ እጀ ብልኅ ሠራተኛም ኪሩቤልን ይጥለፍባቸው።

2. መጋረጃዎች ሁሉ እኵል ይሁኑ፤ የእያንዳንዱ መጋረጃ ርዝመት ሃያ ስምንት ክንድ ወርዱም አራት ክንድ ይሁን።

3. አምስቱን መጋረጃዎች አገጣጥመህ ስፋ፤ የቀሩትንም አምስት መጋረጃዎች እንደዚሁ አገጣጥመህ ስፋቸው።

4. ከዳር በኩል ባለው መጋረጃ ጠርዝ ላይ፣ ከሰማያዊ ጨርቅ የተሠሩ ቀለበቶች አድርግ፤ በሌላውም የመጋረጃ ጠርዝ ላይ እንዲሁ አድርግ።

5. ቀለበቶችን ትይዩ በማድረግ አምሳ ቀለበቶችን በአንደኛው ጠርዝ መጋረጃ፣ አምሳ ቀለበቶችንም በሌላው ጠርዝ መጋረጃ አድርግ።

6. ከዚያም የመገናኛው ድንኳን አንድ ወጥ ይሆን ዘንድ መጋረጃዎቹን በአንድ ላይ ለማያያዝ አምሳ የወርቅ ማያያዣዎችን ሥራ።

7. “ማደሪያ ድንኳኑን ከላይ ሆነው የሚሸፍኑ ዐሥራ አንድ የፍየል ጠጒር መጋረጃዎች ሥራ።

8. ዐሥራ አንዱም መጋረጃዎች እኩል ይሁኑ፤ የእያንዳንዱ ርዝመት ሠላሳ ክንድ ወርዱም አራት ክንድ ይሁን።

9. አምስቱን መጋረጃዎች በአንድ ላይ፣ እንደዚሁም ስድስቱን መጋረጃዎች በአንድ ላይ አድርገህ ስፋቸው፤ ከማደሪያው ድንኳን ፊት ለፊት ስድስተኛውን መጋረጃ እጠፍና በላዩ ላይ ደርበው።

10. በአንድ በኩል ባለው መጨረሻ መጋረጃ ጠርዝ ላይ አምሳ ቀለበቶችን፣ እንዲሁም በሌላ በኩል ባለው መጨረሻ መጋረጃ ጠርዝ ላይ አምሳ ቀለበቶችን አድርግ።

11. ከዚያም አምሳ የናስ ማያያዣዎችን ሥራ፤ ድንኳኑን አንድ ወጥ አድርጎ ለማያያዝ በቀለበቶቹ ውስጥ ጨምራቸው።

12. ስለ ድንኳኑ መጋረጃዎች ትርፍ ቁመትም፣ ትርፍ ግማሽ መጋረጃ ከማደሪያው ድንኳን ጀርባ ላይ እንዲንጠለጠል ይሁን።

13. የድንኳኑ መጋረጃዎች በሁለቱም ጐኖች አንድ ክንድ ርዝመት ይኖራቸዋል፤ የተረፈውም የማደሪያውን ድንኳን ጎኖች እንዲሸፍን ሆኖ ይንጠለጠላል፤

14. ለድንኳኑ በቀይ የተነከረ የአውራ በግ ቆዳ ልብስ አብጅ፤ በላዩም ላይ የአቆስጣ ቆዳ ይሁን።

15. “ለማደሪያው ድንኳን ከግራር ዕንጨት ወጋግራዎችን አብጅ።

16. እያንዳንዱም ወጋግራ ርዝመቱ ዐሥር ክንድ ወርዱም አንድ ክንድ ተኵል ይሁን፤

17. ሁለት ጉጦችም ጎን ለጎን ይሁኑለት፤ የማደሪያውን ድንኳን ወጋግራዎች ሁሉ በዚሁ መልክ አብጅ

18. ለማደሪያው ድንኳን ክፍል ሃያ ወጋግራዎችን ሥራ።

19. ከሥራቸው የሚሆኑ አርባ የብር መቆሚያዎችን አብጅ፤ በእያንዳንዱ ጒጠት ሥር አንድ መቆሚያ ሲሆን፣ ለእያንዳንዱም ወጋግራ ሁለት መቆሚያዎች ይኑሩ።

20. በሌላው ጎን፣ ከማደሪያው ድንኳን በስተ ሰሜን በኩል ሃያ ወጋግራዎችን አብጅ፤

21. በእያንዳንዱም ወጋግራ ሥር ሁለት ሁለት መቆሚያ ሆኖ አርባ የብር መቆሚያዎችን አብጅ።

22. በዳር በኩል ለሚገኘው ይኸውም በምዕራብ ጠርዝ ላለው የማደሪያው ድንኳን ስድስት ወጋግራዎች አብጅ።

23. ዳርና ዳር ላሉት ማእዘኖች ሁለት ወጋግራዎች አብጅ።

24. በእነዚህ ሁለት ማእዘኖች ላይ ከታች እስከ ላይ ድረስ ድርብ ሲሆኑ በአንድ ቀለበት ውስጥ የሚገጥሙ መሆን አለባቸው፤ በሁለቱም ወገን እንዲሁ መሆን አለበት።

25. ስለዚህ ስምንት ወጋግራዎች አሉ፤ እንዲሁም ዐሥራ ስድስት የብር መቆሚያዎች ሲኖሩ፣ ለእያንዳንዱ ወጋግራ ሁለት ሁለት መቆሚያ ይሆናል።

26. “ደግሞም ከግራር ዕንጨት አግዳሚዎችን አብጅ፤ በአንድ በኩል ላሉት የማደሪያው ድንኳን ወጋግራዎች አምስት፣

27. በሌላው ጎን ላሉት አምስት፣ በማደሪያው ድንኳን ዳር በምዕራብ በኩል ባሉት ወጋግራዎች አምስት አብጅ።

28. መካከለኛው አግዳሚ በወጋግራዎቹ መካከል ከጫፍ እስከ ጫፍ ይተላለፍ።

29. ወጋግራዎቹን በወርቅ ለብጣቸው፤ አግዳሚዎቹን ለመያዝ የወርቅ ቀለበቶች አብጅ፤ አግዳሚዎቹንም በወርቅ ለብጣቸው።

30. “ማደሪያ ድንኳኑንም በተራራው ላይ ባየኸው ዕቅድ መሠረት ትከለው።

31. “ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ መጋረጃ አብጅ፤ እጀ ብልህ ሠራተኛም ኪሩቤልን ይጥለፍበት።

32. በወርቅ በተለበጡ ከግራር ዕንጨት በተሠሩና በአራቱ የብር መቆሚያዎች ላይ በቆሙት በአራቱ ምሰሶዎች፣ በወርቅ ኵላቦች ላይ አንጠልጥለው።

33. መጋረጃውን በማያያዣዎቹ ላይ ስቀለው፤ የምስክሩንም ታቦት ከመጋረጃው በስተ ኋላ አስቀምጠው፤ መጋረጃውም መቅደሱን ከቅድስተ ቅዱሳኑ ይለያል።

34. በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ በምስክሩ ታቦት ላይ የማስተስረያውን ክዳን አስቀምጥ።

35. ጠረጴዛውን ከመገናኛው ድንኳን በሰሜን በኩል ከመጋረጃው ውስጥ አስቀምጠው፤ መቅረዙንም ከእርሱ ትይዩ በማድረግ በደቡብ በኩል አድርገው።

36. “ለድንኳኑ ደጃፍ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ በጥልፍ ዐዋቂ የተጠለፈ መጋረጃ አብጅ።

37. ለዚህም መጋረጃ የወርቅ ኵላቦችንና ከግራር እንጨት የተሠሩ፣ በወርቅ የተለበጡ አምስት ምሰሶዎችን አብጅ፤ አምስት የናስ መቆሚያዎችንም አብጅላቸው።