ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36
  37. 37
  38. 38
  39. 39
  40. 40

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 32 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የወርቅ ጥጃ

1. ሕዝቡ ሙሴ ከተራራው ላይ ሳይ ወርድ ብዙ እንደ ቆየ ባዩ ጊዜ፣ ወደ አሮን ተሰብስበው፣ “ናና በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን፤ ያ ከግብፅ ያወጣን ሙሴ ምን እንዳገኘው አናውቅም” አሉት።

2. አሮንም፣ “የሚስቶቻችሁን፣ የወንድና የሴት ልጆቻችሁን የጆሮ ወርቅ አውልቃችሁ ወደ እኔ አምጡ” ብሎ መለሰላቸው።

3. ሕዝቡም ሁሉ የጆሮ ወርቃቸውን አውልቀው ወደ አሮን አመጡ።

4. እርሱም የሰጡትን ወስዶ በመሣሪያ በመቅረጽ በጥጃ ምስል ጣዖት አድርጎ ሠራው፤ ከዚያም እነርሱ፣ “እስራኤል ሆይ፤ ከግብፅ ያወጡህ አማልክት እነዚህ ናቸው” አሉ።

5. አሮን ይህን ባየ ጊዜ በወርቅ ጥጃው ፊት ለፊት መሠዊያ ሠርቶ፣ “ነገ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በዓል ይሆናል” ብሎ ዐወጀ።

6. በማግሥቱ ሕዝቡ በማለዳ ተነሥተው የሚቃጠል መሥዋዕት ሠዉ፤ የኅብረት መሥዋዕት አቀረቡ፤ ከዚህም በኋላ ይበሉና ይጠጡ ዘንድ ተቀመጡ፤ ሊዘፍኑም ተነሡ።

7. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “ከግብፅ ያወጣኻቸው ሕዝብህ ስተዋልና ውረድ አለው፤

8. ካዘዝኋቸው ፈቀቅ ለማለት ፈጣኖች ሆኑ፤ ለራሳቸውም በጥጃ ምስል የተቀረጸ ጣዖትን ሠሩ፤ ለእርሱም ሰገዱለት፤ ሠዉለትም፤ እንዲሁም፣ ‘እስራኤል ሆይ፤ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ እነዚህ ናቸው’ ” አሉ።

9. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እነዚህን ሕዝብ አይቻቸዋለሁ፤ አንገተ ደንዳናዎችም ናቸው፤

10. አሁንም በእነርሱ ላይ፣ ቍጣዬ እንዲነድና እንዳጠፋቸው ተወኝ፤ ከዚያም አንተን ለታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ።”

11. ነገር ግን ሙሴ የአምላኩን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ቸርነት ፈለገ፤ እንዲህም አለ፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ በታላቅ ሥልጣንህና በኀያል ክንድህ ከግብፅ ባወጣኸው ሕዝብህ ላይ ቍጣህ ለምን ይነዳል?

12. ግብፃውያን፣ ‘በተራራዎቹ ላይ ሊገድላቸው ከገጸ ምድርም ሊያጠፋቸው ስለ ፈለገ ነው ያወጣቸው’ ለምን ይበሉ? ከክፉ ቍጣህ ተመለስ፤ ታገሥ፤ በሕዝብህም ላይ ጥፋት አታምጣ።

13. ለባሪያዎችህ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለእስራኤል፣ ‘ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛዋለሁ፤ ለዘርህም ተስፋ አድርጌ የሰጠኋቸውን ይህችን ምድር ሁሉ እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘላለምም ርስታቸው ትሆናለች’ በማለት በራስህ የማልኸውን አስታውስ።”

14. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ታገሠ፤ በሕዝቡም ላይ አመጣባቸዋለሁ ያለውን ጥፋት አላመጣባቸውም።

15. ሙሴም ሁለቱን የምስክር ጽላቶች በእጆቹ ይዞ ከተራራው ወረደ፤ ጽላቶቹም ከፊትና ከኋላ በሁለቱም ጎኖች ተጽፎባቸው ነበር።

16. ጽላቶቹ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሥራ ነበሩ፤ በጽላቶቹ ላይ የተቀረጸ ጽሕፈትም የእግዚአብሔር (ያህዌ) ጽሕፈት ነበር።

17. ኢያሱ የሕዝቡን የጩኸት ድምፅ በሰማ ጊዜ ሙሴን፣ “በሰፈሩ ውስጥ የጦርነት ድምፅ አለቃ አለው።

18. ሙሴም“የድል ድምፅ አይደለም፤የሽንፈትም ድምፅ አይደለም፤የምሰማው የዘፈን ድምፅ ነው” ብሎ መለሰለት።

19. ሙሴ ወደ ሰፈሩ ደርሶ ጥጃውንና ጭፈራውን ባየ ጊዜ ቍጣው ነደደ፤ ጽላቶቹን ከእጁ በመወርወር ከተራራው ግርጌ ሰባበራቸው።

20. የሠሩትን ጥጃ ወስዶ በእሳት አቃጠለው፤ ከዚያም ዱቄት እስኪሆን ፈጨው፤ በውሃ ላይ በተነው፤ እስራኤላውያንም እንዲጠጡት አደረገ።

21. አሮንንም፣ “ወደዚህ አስከፊ ኀጢአት ትመራቸው ዘንድ እነዚህ ሕዝብ ምን አደረጉህ?” አለው።

22. አሮንም መልሶ፣ “ጌታዬ ሆይ አትቈጣ ብሎ መለሰለት፤ ይህ ሕዝብ ሁል ጊዜ ለክፋት ያዘነበለ መሆኑን አንተ ታውቃለህ፤

23. እነርሱም ‘በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን፤ ይህ ከግብፅ ያወጣን ሙሴ ምን እንዳገኘው አናውቅም’ አሉኝ።

24. ስለዚህ፣ ‘ማንኛውም ዐይነት የወርቅ ጌጣጌጥ ያለው ሁሉ ያውልቀው አልኋቸው፤ ከዚያም ወርቁን ሰጡኝ፤ ወደ እሳቱ ጣልሁት፤ ይህም ጥጃ ወጣ።”

25. ሕዝቡ ከቍጥጥር ውጭ እንደሆኑ፣ አሮንም መረን እንደ ለቀቃቸውና በጠላቶቻቸውም ዘንድ መሳለቂያ እንደሆኑ ሙሴ አስተዋለ።

26. ስለዚህ በሰፈሩ መግቢያ ላይ ቆሞ፣ “የእግዚአብሔር (ያህዌ) የሆነ ሁሉ ወደ እኔ ይምጣ” አለ፤ ሌዋውያኑም ሁሉ ከእርሱ ጋር ሆኑ።

27. ከዚያም፣ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚለው ይህ ነው፤ ‘እያንዳንዱ ሰው በወገቡ ላይ ሰይፍ ይታጠቅ፤ በሰፈር ውስጥ ከዳር እዳር እየተመላለሰ እያንዳንዱ ወንድሙን፣ ጓደኛውንና ጎረቤቱን ይግደል’ ” አላቸው።

28. ሌዋውያኑ ሙሴ እንዳዘዛቸው ፈጸሙ፤ በዚያኑም ዕለት ከሕዝቡ ሦስት ሺህ ያህል አለቁ።

29. ከዚያም ሙሴ፣ “በራሳችሁ ወንዶች ልጆችና ወንድሞች ላይ በመነሣታችሁ፣ በዛሬዋ ቀን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተለያችሁ ሆናችኋል፤ በዛሬዋም ዕለት ባርኳችኋል” አለ።

30. በማግሥቱም ሙሴ ሕዝቡን፣ “እጅግ የከፋ ኀጢአት ሠርታችኋል፤ አሁን ግን ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) እወጣለሁ፤ ምናልባት ኀጢአታችሁን ማስተስረይ እችል ይሆናል” አላቸው።

31. ስለዚህ ሙሴ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ተመልሶ እንዲህ አለው፤ “ወዮ እነዚህ ሕዝብ የሠሩት ምን ዐይነት የከፋ ኀጢአት ነው! ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት ሠሩ።

32. አሁን ግን አቤቱ ኀጢአታቸውን ይቅር በል፤ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍ እኔን ደምስሰኝ።”

33. እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሙሴ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “የበደለኝን ሁሉ ከመጽሐፌ እደመስሰዋለሁ፤

34. አሁን ሂድ፤ ሕዝቡን ወደ ተናገርኩት ስፍራ ምራው፤ መልአኬም በፊትህ ይሄዳል፤ ሆኖም የምቀጣበት ጊዜ ሲደርስ፣ ስለ ኀጢአታቸው እቀጣቸዋለሁ።”

35. አሮን በሠራው ጥጃ ባደረጉት ነገር እግዚአብሔር (ያህዌ) ሕዝቡን በመቅሠፍት መታ።