ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36
  37. 37
  38. 38
  39. 39
  40. 40
  41. 41
  42. 42
  43. 43
  44. 44
  45. 45
  46. 46
  47. 47
  48. 48

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 46 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ለምሥራቅ ትይዩ የሆነው የውስጠኛው አደባባይ በር በስድስቱ የሥራ ቀኖች ይዘጋ፤ ነገር ግን በሰንበት ቀንና በወር መባቻ ቀን ይከፈት።

2. ገዡ ከውጭ በኩል በመግቢያው መተላለፊያ በረንዳ በመግባት በበሩ መቃን አጠገብ ይቁም፤ ካህናቱም የእርሱን የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት ያቅርቡለት፤ በበሩ መግቢያ ደፍ ላይ ሆኖ ይስገድ፤ ከዚያም ይውጣ፤ በሩ ግን እስከ ምሽት ድረስ አይዘጋ።

3. የምድሪቱም ሕዝብ በሰንበታትና በወር መባቻ በዓላት በእግዚአብሔር ፊት በበሩ መግቢያ ላይ ይስገዱ።

4. ገዡ በሰንበት ቀን በእግዚአብሔር ፊት የሚያቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ስድስት የበግ ጠቦትና አንድ አውራ በግ ነው፤ ሁሉም እንከን የሌላቸው ይሁኑ።

5. ከአውራ በጉ ጋር የሚቀርበው የእህል ቍርባን አንድ የኢፍ መስፈሪያ ይሁን፤ ከበግ ጠቦቶቹ ጋር የሚቀርበውም የእህል ቍርባን ሰውየው የወደደውን ያህል ይሁን፤ እያንዳንዱም የኢፍ መስፈሪያ አንድ የኢን መስፈሪያ ዘይት ይኑረው።

6. በወር መባቻ በዓል አንድ ወይፈን፣ ስድስት የበግ ጠቦትና አንድ አውራ በግ ያቅርብ፤ ሁሉም እንከን የሌለባቸው ይሁኑ።

7. ከወይፈኑ ጋር አንድ የኢፍ መስፈሪያ፣ ከአውራው በግም ጋር አንድ የኢፍ መስፈሪያ የእህል ቍርባን ያቅርብ፤ ከበግ ጠቦቶቹ ጋር የሚቀርበው የእህል ቍርባን ደግሞ ሰውየው የወደደውን ያህል ይሁን፤ እያንዳንዱም የኢፍ መስፈሪያ የኢን መስፈሪያ ዘይት ይኑረው።

8. ገዡ ሲገባ፣ በመግቢያው በር መተላለፊያ በረንዳ ይግባ፤ ሲወጣም በዚያው ይውጣ።

9. “ ‘በተወሰኑት በዓላት የምድሪቱ ሕዝብ በእግዚአብሔር ፊት በሚቀርብበት ጊዜ፣ ይሰግድ ዘንድ በሰሜን በር የገባ ሁሉ በደቡብ በር ይውጣ፤ በደቡብ በር የገባም በሰሜኑ በር ይውጣ፤ በፊት ለፊቱ ባለው በር ይመለስ እንጂ ማንም በገባበት በር አይውጣ።

10. ገዡ በመካከላቸው በመሆን፣ ሲገቡ ይገባል፤ ሲወጡም ይወጣል።

11. “ ‘በበዓላትና በተወሰኑት በዓላት፣ ከወይፈኑ ጋር አንድ የኢፍ መስፈሪያ፣ ከአውራ በጉም ጋር አንድ የኢፍ መስፈሪያ የእህል ቍርባን ያቅርብ፤ ከበግ ጠቦቶቹ ጋር የሚያቀርበው የእህል ቍርባን ግን ሰውየው የወደደውን ያህል ይሁን፤ እያንዳንዱም የኢፍ መስፈሪያ አንድ የኢን መስፈሪያ ዘይት ይኑረው።

12. ገዡ በፈቃዱ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕትም ሆነ የኅብረት መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ፣ በምሥራቅ ትይዩ የሆነው በር ይከፈትለት፤ በሰንበት ቀን እንደሚያደርገው ሁሉ የሚቃጠል መሥዋዕቱንም ሆነ የኅብረት መሥዋዕቱን ያቅርብ፤ ከዚያ በኋላ ይወጣል፤ በሩም ይዘጋል።

13. “ ‘በየቀኑ እንከን የሌለበትን የአንድ ዓመት ጠቦት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ ለእግዚአብሔር አቅርብ፤ ይህንንም በየማለዳው ታቀርበዋለህ።

14. ከዚህም ጋር አንድ ስድስተኛ የኢፍ መስፈሪያ ዱቄት መለወሻም የሚሆን የኢን መስፈሪያ ሢሶ ዘይት አድርገህ በየማለዳው የእህል ቍርባን አቅርብ፤ ይህን የእህል ቍርባን ለእግዚአብሔር ማቅረብም የዘላለም ሥርዐት ነው።

15. ስለዚህ ዘወትር ለሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት በየማለዳው የበግ ጠቦት፣ የእህል ቍርባንና ዘይት ይቅረብ።

16. “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ገዡ ከርስቱ ላይ ከወንድ ልጆቹ ለአንዱ ስጦታ ቢያደርግ፣ ያ ስጦታ ለዘሩ የሚተላለፍ ነው፤ በውርስም ንብረታቸው ይሆናል።

17. ይሁን እንጂ ገዡ ከርስቱ ላይ ከባሪያዎቹ ለአንዱ ቢሰጥ፣ ባሪያው ነጻ እስከሚወጣበት ዓመት ድረስ የራሱ ሊያደርገው ይችላል፤ ከዚያም ርስቱ ለገዡ ይመለስለታል፤ ርስቱም ለወንድ ልጆቹ ብቻ የሚተላለፍ ይሆናል፤ የእነርሱም ነው።

18. ገዡ ከንብረታቸው በማፈናቀል፤ የትኛውንም የሕዝቡን ርስት መውሰድ አይገባውም፤ ለወንድ ልጆቹ ርስት መስጠት ያለበት ከራሱ ንብረት ነው፤ ይኸውም ከሕዝቤ ማንም ከርስቱ እንዳይነቀል ነው።’ ”

19. ከዚያም ያ ሰው በበሩ አጠገብ ባለው መግቢያ አድርጎ፣ ለሰሜን ትይዩ ወደሆኑት ወደ ካህናቱ የተቀደሱ ክፍሎች አመጣኝ፤ በምዕራቡም መዳረሻ ያለውን ቦታ አሳየኝ።

20. እርሱም፣ “ይህ ስፍራ ሕዝቡን ለመቀደስ መሥዋዕቱን ወደ ውጩ አደባባይ እንዳያወጡ፣ ካህናቱ የበደሉን መሥዋዕትና የኀጢአቱን መሥዋዕት የሚቀቅሉበት፣ የእህሉንም ቍርባን የሚጋግሩበት ቦታ ነው” አለኝ።

21. ከዚያም ወደ ውጩ አደባባይ አመጣኝ፤ በአራቱም ማእዘን ዙሪያ መራኝ፤ በእያንዳንዱም ማእዘን ሌላ አደባባይ አየሁ።

22. በውጩ አደባባይ ባለው በአራቱ ማእዘን የታጠሩ አደባባዮች አሉ፤ ርዝመታቸው አርባ ክንድ፣ ወርዳቸውም ሠላሳ ክንድ ነበር፤ በአራቱም ማእዘን ያሉት አደባባዮች እኩል ናቸው።

23. ከሥሩ ዙሪያውን ምድጃ የነበረበት፣ በአራቱም አደባባዮች ውስጥ ዙሪያ የድንጋይ ዕርከን ነበር።

24. እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “እነዚህ፣ በቤተ መቅደሱ የሚያገለግሉቱ፣ የሕዝቡን መሥዋዕት የሚቀቅሉባቸው ስፍራዎች ናቸው።”