ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36
  37. 37
  38. 38
  39. 39
  40. 40
  41. 41
  42. 42
  43. 43
  44. 44
  45. 45
  46. 46
  47. 47
  48. 48

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 7 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ፍጻሜው ደረሰ

1. የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

2. “አንተ የሰው ልጅ ሆይ፤ ጌታ እግዚአብሔር ለእስራኤል ምድር እንዲህ ይላል፤ ‘ፍጻሜ! በአራቱም የምድሪቱ ማእዘን ፍጻሜ መጥቶአል።

3. አሁንም መጨረሻሽ ደርሶአል፤ ቍጣዬን በአንቺ ላይ አፈሳለሁ፤ እንደ አካሄድሽ እፈርድብሻለሁ፤ ስለ ጸያፍ ተግባርሽ ሁሉ ተገቢውን ቅጣት እከፍልሻለሁ።

4. በርኅራኄ ዐይን አልመለከትሽም፤ ምሕረትም አላደርግልሽም፤ ስለ አካሄድሽና በመካከልሽ ስላለው ጸያፍ ተግባር ተገቢውን ቅጣት እከፍልሻለሁ፤ በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።”

5. “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘መዓት! ተሰምቶ የማይታወቅ መዓት ይመጣል።

6. ፍጻሜ መጥቶአል! ፍጻሜ መጥቶአል! በአንቺ ላይ ተነሣሥቶአል፤ እነሆ፤ ደርሶአል!

7. እናንት በምድሪቱ የምትኖሩ ሆይ፤ የጥፋት ፍርድ መጥቶባችኋል፤ ጊዜው ደርሶአል፤ በተራሮች ላይ እልልታ ሳይሆን ሽብር የሚሰማበት ቀን ቀርቦአል።

8. እነሆ፤ መዓቴን በቅርብ ቀን አፈስብሻለሁ፤ በአንቺ ላይ ቍጣዬን እፈጽምብሻለሁ፤ እንደ አካሄድሽ እፈርድብሻለሁ፤ ስለ ጸያፍ ተግባርሽም ሁሉ ተገቢውን ቅጣት እከፍልሻለሁ።

9. በርኅራኄ ዐይን አልመለከትሽም፤ ምሕረት አላደርግልሽም፤ ስለ አካሄድሽና በመካከልሽ ስላለው ጸያፍ ተግባር ተገቢውን ቅጣት እከፍልሻለሁ፤ በዚያ ጊዜ፣ የምቀሥፍ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።

10. “ ‘እነሆ ቀኑ ይኸው ደረሰ! የጥፋት ፍርድ ተገልጦአል፤ በትሩ አቈጥቍጦአል፤ ትዕቢት አብቦአል።

11. ዐመፅ አድጋ የክፋት በትር ሆነች፤ ከሕዝቡ አንድም አይተርፍም፤ ከሰዎቹ፣ ከሀብታቸውና እርባና ካለው ነገር አንዳች አይቀርም።

12. ጊዜው ደርሶአል፤ ቀኑም ይኸው! መዓት በሕዝቡ ሁሉ ላይ ስለ መጣ፣ የሚገዛ አይደሰት፤ የሚሸጥም አይዘን።

13. ሁለቱ በሕይወት እስካሉ ድረስ ሻጩ የሸጠውን መሬት አያስመልስም፤ ስለ መላው ሕዝብ የተነገረው ራእይ አይለወጥምና። ከኀጢአታቸው የተነሣ ሕይወቱን ማትረፍ የሚችል አንድም አይገኝም።

14. መለከት ቢነፉም፣ ሁሉንም ነገር ቢያዘጋጁም፣ ወደ ጦርነት የሚሄድ አንድ እንኳ አይኖርም፤ መዓቴ በሕዝብ ሁሉ ላይ መጥቶአልና።

15. “በውጭ ሰይፍ፣ በውስጥ ደግሞ ቸነፈርና ራብ አለ፤ በገጠር ያሉት በሰይፍ ይወድቃሉ፤ በከተማ ያሉትም በራብና በቸነፈር ያልቃሉ።

16. ተርፈው ያመለጡት ሁሉ በሸለቆ እንደሚኖሩ ርግቦች ስለ ኀጢአታቸው እያለቀሱ በተራራ ላይ ይሆናሉ።

17. እጅ ሁሉ ይዝላል፤ ጒልበት ሁሉ ውሃ ይሆናል።

18. ማቅ ይለብሳሉ፤ ሽብርም ይውጣቸዋል። ፊታቸው ኀፍረት ይለብሳል፤ ራሳቸውም ይላጫል።

19. ብራቸውን በየጐዳናው ይጥላሉ፤ ወርቃቸውም እንደ ርኵስ ነገር ይቈጠራል። በእግዚአብሔር የቍጣ ቀን ብራቸውና ወርቃቸው ሊያድናቸው አይችልም፤ በኀጢአት እንዲወድቁ ዕንቅፋት ሆኖባቸዋልና በልተው አይጠግቡበትም፤ ሆዳቸውንም አይሞሉበትም።

20. በውብ ዕንቋቸው ታብየዋል፤ ይህንም አስጸያፊ የጣዖት ምስሎቻቸውንና ርኵስ ቅርጻ ቅርጾችን ለመሥራት ተጠቅመውበታል። ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ወደ ርኵሰት እለውጥባቸዋለሁ።

21. ለባዕዳን ዝርፊያ፣ ለምድር ክፉዎችም ብዝበዛ አድርጌ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እነርሱም ያረክሱታል።

22. ፊቴን ከእነርሱ እመልሳለሁ፤ እነርሱም የከበረውን ቦታዬን ያረክሳሉ፤ ወንበዴዎች ይገቡበታል፤ ያረክሱታልም።

23. “ ‘ምድር በደም መፋሰስ፣ ከተማዪቱም በዐመፅ ተሞልታለችና ሰንሰለት አዘጋጅ።

24. እጅግ የከፉትን ከአሕዛብ አምጥቼ ቤቶቻቸውን እንዲነጥቁ አደርጋለሁ፣ የኀያላኑንም ትዕቢት አጠፋለሁ፤ መቅደሳቸውም ይረክሳል።

25. ሽብር በመጣ ጊዜ ሰላምን ይሻሉ፤ ነገር ግን አያገኟትም።

26. ጥፋት በጥፋት ላይ፣ ወሬም በወሬ ላይ ይመጣል። ራእይን ከነቢይ ለማግኘት ይጥራሉ፤ የሕግ ትምህርት ከካህኑ፣ ምክርም ከሽማግሌው ዘንድ ይጠፋል።

27. ንጉሡ ያለቅሳል፤ መስፍኑ ተስፋ መቍረጥን ይከናነባል፤ የምድሪቱም ሕዝብ እጅ ትንቀጠቀጣለች። የእጃቸውን እከፍላቸዋለሁ፤ ራሳቸው ባወጡት መስፈርት መሠረት እፈርድባቸዋለሁ። በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።’ ”