ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36
  37. 37
  38. 38
  39. 39
  40. 40
  41. 41
  42. 42
  43. 43
  44. 44
  45. 45
  46. 46
  47. 47
  48. 48

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የሐሰተኛ ነቢያት መወገዝ

1. የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

2. “የሰው ልጅ ሆይ፤ ትንቢት በሚናገሩት በእስራኤል ነቢያት ላይ ትንቢት ተናገር፤ ከገዛ ራሳቸው ትንቢት የሚናገሩትን እንዲህ በላቸው፤ ‘የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤

3. ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “አንዳች ነገር ሳያዩ የራሳቸውን መንፈስ ለሚከተሉ ሞኞች ነቢያት ወዮላቸው!

4. እስራኤል ሆይ፤ ነቢያትሽ በፍርስራሽ መካከል እንደሚኖሩ ቀበሮዎች ናቸው።

5. በእግዚአብሔር ቀን በሚሆነው ጦርነት ጸንቶ መቆም እንዲችል፣ የተሰነጠቀውን ቅጥር ለእስራኤል ቤት ለመጠገን ወደዚያ አልወጣችሁም።

6. ራእያቸው ሐሰት፣ ትንቢታቸው ውሸት ነው፤ እግዚአብሔር ሳይልካቸው፣ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል’ ይላሉ፤ ይህም ሆኖ የተናገሩት ይፈጸማል ብለው ይጠብቃሉ።

7. እኔ ሳልናገር፣ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል’ ስትሉ ሐሰተኛ ራእይ ማየታችሁ፣ ውሸተኛስ ትንቢት መናገራችሁ አይደለምን?”

8. “ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ቃላችሁ ሐሰት፣ ራእያችሁም ውሸት ስለ ሆነ እኔ በእናንተ ላይ ተነሥቻለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

9. እጄ የሐሰት ራእይ በሚያዩና በሚያሟርቱ ነቢያት ላይ ተነሥቶአል። የሕዝቤ ጉባኤ ተካፋይ አይሆኑም፤ በእስራኤል ቤት መዝገብ አይጻፉም፤ ወደ እስራኤልም ምድር አይገቡም። በዚያ ጊዜ እኔ ጌታ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።

10. “ሰላም ሳይኖር፣ ‘ሰላም አለ’ እያሉ ሕዝቤን ያስታሉ፤ ሕዝቡ ካብ ሲሠራ እነርሱ በኖራ ይለስናሉ፤

11. ስለዚህ በኖራ ለሚለስኑት ካቡ እንደሚወድቅ ንገራቸው። ዶፍ ይወርዳል፤ ታላቅ የበረዶ ድንጋይ እሰዳለሁ፤ ዐውሎ ነፋስም ይነሣል።

12. እነሆ ካቡ ሲፈርስ ሕዝቡ ‘የለሰናችሁበት ኖራው ወዴት ሄደ?’ ብለው አይጠይቋችሁምን?”

13. “ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በመዓቴ ዐውሎ ነፋስ እሰዳለሁ፣ በቍጣዬ የበረዶ ድንጋይ እልካለሁ፤ ዶፍም ከታላቅ ጥፋት ጋር ይወርዳል።

14. በኖራ የለሰናችሁትን ካብ አፈርሳለሁ፤ መሠረቱም ተገልጦ እስኪታይ ድረስ ከምድር ጋር አደባልቀዋለሁ። ቅጥሩ በሚወድቅበት ጊዜ፣ እናንተም በውስጡ ታልቃላችሁ። በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።

15. መዓቴንም በቅጥሩና ኖራ በለሰኑት ሰዎች ላይ እሰዳለሁ፤ እናንተንም እንዲህ እላችኋለሁ፤ ‘ቅጥሩና ቅጥሩን በኖራ የለሰኑት የሉም፤

16. ኢየሩሳሌም ትንቢት የተናገሩላትና ሰላም ሳይኖር የሰላም ራእይ ያዩላት የእስራኤል ነቢያት ጠፍተዋል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”

17. “አሁንም የሰው ልጅ ሆይ፤ ከራሳቸው አመንጭተው ትንቢት ወደሚናገሩ ወደ ሕዝብህ ሴቶች ልጆች ፊትህን መልስ፤ ትንቢትም ተናገርባቸው፤

18. እንዲህም በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የሕዝብን ነፍስ ለማጥመድ፣ ለአስማታቸው ለእጃቸው አንጓ ሁሉ አሸንክታብ ለሚያሰፉና፣ የተለያየ መጠን ያለውን የራስ መሸፈኛ ለሚያበጁ ሴቶች ወዮላቸው! በውኑ የሕዝቤን ነፍስ እያጠመዳችሁ የራሳችሁን ነፍስ ታድናላችሁን?

19. ዕፍኝ ለማይሞላ ገብስና ለቍራሽ እንጀራ ስትሉ ሐሰትን የሚያደምጥ ሕዝቤን እየዋሻችሁ መሞት የማይገባውን በመግደል፣ መኖር የማይገባውንም በማትረፍ በሕዝቤ መካከል አርክሳችሁኛል።

20. “ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ የሕዝብን ነፍስ እንደ ወፍ በምታጠምዱበት አሸንክታብ ላይ ተነሥቻለሁ፤ ከክንዳችሁ ላይ እቀዳድደዋለሁ፤ እንደ ወፍ የምታጠምዱትንም ሕዝብ ነጻ አወጣዋለሁ።

21. መሸፈኛችሁን ቀድጄ ሕዝቤን ከእጃችሁ አድናለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲህ በቍጥጥራችሁ ሥር አይሆኑም፤ በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።

22. እኔ ያላሳዘንሁትን ጻድቅ በውሸት ስላሳዘናችሁ፣ ኀጢአተኛም ከክፉ መንገዱ ተመልሶ ሕይወቱን እንዳያድን በኀጢአቱ ስላበረታታችሁት፣

23. ከእንግዲህ የሐሰት ራእይ አታዩም፣ ሟርትም አታሟርቱም፤ ሕዝቤን ከእጃችሁ አድናለሁ፤ በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።’ ”